“የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብ ዳግም ወደ እልቂት ሲገባ ዝም ብሎ ሊመለከት አይገባም” ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ
አስተዳደሩ ፌደራል መንግስት አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርግም ጠይቋል
የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ዛሬ ረፋድ መግለጫ አውጥቷል። አስተዳደሩ የትግራይ ጦር አዛዦች ከተልኮ ወጭ የአንድ ጠባብ ቡድን የስልጣን ጥም ለማርካት በማለት ግልፅ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ቆይተዋል ያለ ሲሆን በዚህ ሳምንትም በተመሳሳይ በሰሜን ምስራቅና በደቡብ ግንባር አዛዦች እንቅስቃሴው በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል ማለቱን ዳጉ ጆርናል ከመግለጫው ተመልክቷል።
አስተዳደሩ በመግለጫው ይህንን አደገኛ እንቅስቃሴ እንዲያስቆም ለአጠቃላይ ጦር አዛዡ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ትእዛዝ ቢሰጥም የጥፋት ድርጊቱ ማስቆም እንዳልቻለ አስታውቋል።
የጥፋት ድርጊቶቹ ተባብሰው በቀጠሉበት በአሁኑ ሰዓት በስቪሎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑንና ከላይ እስከታች ያለውን የመንግስት መዋቅር የማፍረስ እንቅስቃሴዎች ቀጥለዋል ማለቱንም ታውቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው የትግራይ ጦር የበላይ አዛዦች የኃላ ቀሩን ቡዱን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ መንግስት እንዲፈርስ እንዲሁም የፕሪቶርያ ስምምነት በይፋ እንዲጣስ በማድረግ የትግራይን ህዝብ ዳግም ወደ ጦርነት እያስገቡት ነውም ብሏል።
አስተዳደሩ በመጨረሻም “ የፌደራል መንግስት በትግራይ የፀጥታ ሀይል ስም የሚንቀሳቀሱት አዛዦች የአንድ ኃላቀርና ወንጀለኛ ቡዱን ተላላኪዎች እንጂ የትግራይ ህዝብና ጊዜያዊ አስተዳደሩን እንደማይወክሉ በመረዳት አስፈላጊ እርዳት ማድረግ አለበት” ብሏል። ከዚህ ባሻገር የፕሪቶርያ ስምምነት እንዲ በይፋ ሲፈርስና የትግራይ ህዝብ ዳግም ወደ እልቂት ሲገባ ዝም ብሎ ሊመለከት አይገባም ሲል የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር ዛሬ ረፋድ ባወጣው መግለጫ አስታዉቋል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ” አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል“
የኤርትራን ጣልቃ ገብነት እና የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት የሚፃረሩ የውጭ አካላት ሚናን ለመግታት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አስታወቁ
👉 ፓርቲዎቹ በጦር በመታገዝ የሚደረግ ይስልጣን ንጥቅያ ይቁም ሲሉም ተደምጠዋል።
የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ፣ ባይቶናና ዓረና ትግራይ በጋራ ባወጡት መግለጫ የህወሓት ካድሬ ጄነራሎችና አጋሮቻቸው በህገወጥ መንገድ ስልጣን ለመንጠቅ እየሞከሩ ባሉበት ወቅት የክልሉ ሰላምና መረጋጋት መደ ቀወስ ውስጥ ከተውታል ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ህገወጥ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መንግስታዊ መዋቅር ከታች እስከላይ በማፍረስ ክልሉ ወደ ከፍተኛ አለመረጋጋት እስገብተዋል ያሉ ሲሆን ይህ በግዴሌሽነት እየተፈፀመ ያለው የስልጣን ወረራ የተናጠል ተግባር ሳይሆን ከኤርትራ መንግስት ጋር በመቀናደት የተሰራ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።
በዚህ መሰረትም አለም አቀፍ አካላትና ሁሉም የፕሪቶርያ ስምምነት ተዋናዮች በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ እንጠይቃለን ያሉ ሲሆን ተጨማሪ ትርምስ ለመከላከልና እስከፊ ክልላዊ ቀውስን ለመከላከል ሲበላል የህግ የበላይነት መከበር አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።
በመጨረሻም የኤርትራን ጣልቃ ገብነት እና የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት የሚፃረሩ የውጭ አካላት ሚናን ለመግታት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።