መግቢያ
በዚህ ባለንበት ዘመን በፍጥነት እያደገ የሚገኘው የዲጂታል ግንኙነት ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ እድሎችና ጠቀሜታዎችን እያስገኘ የሚገኝ የፈጠራ እድገት መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም መረጃዎች ቀድሞ ከነበሩበት እጅግ በላቀ ፍጥት እና ጥራት በቀላሉ ለመላው የዓለም ህዝብ ተደራሽ እየሆኑ የሚገኙበት የማይተነበይ የዲጂታል ዘመን ላይ እንገኛለን። ከዚህ በመነሳት ሀገራት ይህ ፈጣን የመረጃ ልውውጥ በዜጎች የግል ህይወትና በአገራዊ ደህንነት ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቆጣጠር ልዩ ልዩ የቁጥጥር ስርዓቶችን ተግባር ላይ ያውላሉ። እንደምሳሌ፣ በጋና የዳታ ጥበቃ ኮሚሽን (Data Protection Commission) የሚባል ተቋም በህግ የተቋቋመ ሲሆን አጠቃላይ የዳታ ምዝገባ፤ ማቀናበር፣ የማስተላለፍ ሂደትን መቆጣጠርና ከጥሰት ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ እርምጃዎችን የሚወስድ ተቋም ነው።
ከዚህ አንፃር በእኛም ሀገር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት በግልጽ ሰፍሮ እንደምናገኘው ዜጎች በአካላቸው ላይ እንዲሁም፣ በግል ባለቤትነት፣ አመንጭነት ወይም በተለየ መንገድ ግላዊ ይዘት ያላቸው መረጃዎችና ግንኙነቶች በህግ ጥበቃ ያላቸው የነፃነት መብቶች መሆናቸው ተመላክቷል። በአንፃሩ እነዚህ ጥብቅ ጥንቃቄ የሚሹ የግልና አገራዊ መረጃዎች በአልተገባ መንገድ በቀላሉ በሶስተኛ ወገን እጅ እየገቡ ብሎም የሚዲያ ፍጆታ ሆነው ሰፊ ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ጉዳት ሲያስከትሉ ማየት ውሎ አድሯል።
በአገራችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህንን የመብት ክፍል ለመጠበቅ የወጣ የተለየ ህግም ሆነ የተቋቋመ መስሪያ ቤት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እዚም አዛም ተበታትነው በሚገኙ ድንጋጌዎች፣ ወጥነት በሌለው የአሰራር ሂደትና በየተቋማቱ በሚወሰዱ ልዩ ልዩ እርምጃዎች ሲተዳደር ኖሯል። ይሁን እንጂ በ2016 ዓ.ም ይህንን ችግር ሊቀርፍ የሚችል“የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ” ‘’አዋጅ ቁጥር 1321/2016’’ የተሰኘ ህግ ጸድቆ በስራ ላይ ይገኛል። በዚህ ጽሁፍም በዚህ ህግ የተሸፈኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም፣ ስለ ግል ዳታ ምንነት፣ የጥበቃ ስርዓቱ፣ የሚተላለፍበት መንገድና ዝርዝር ግዴታዎችን መተላለፍ የሚያስከትለውን ህጋዊ ተጠያቂነት ለመዳሰስ ተሞክሯል። በመጨረሻም “ዳታ” የሚለው ቃል በአማርኛ መረጃ በተለይም የግል መረጃ የሚለውን አገላለጽ የሚተካ ቢሆንም በአዋጁ ጥቅም ላይ የዋለው የእንግሊዝኛው የግል ዳታ (Personal data) የሚለው ስለሆነ ለተሻለ ግልጽነት በዚህ ጽሁፍም ይኸው ቃል ጥቅም ላይ ውሏል።
ዳታና የግል ዳታ ምንነት
በአገራችን ያለው የዳታ ጥበቃ ስርዓት ገና በጅማሮ ላይ የሚገኝ ከመሆኑ የተነሳ የዳበረ ስርዓት ያለቸው አገራት ለጉዳዩ የሰጡትን ትርጉም መመልከት ተገቢ ይሆናል። በዚህም ለምሳሌ የኖርዋይ መንግስት ዳታ ጥበቃ ባለስልጣን የግል ዳታን ሲተረጉም፣ “Personal data is any kind of information that can be related to an identifiable person…. that may include information on name, address, e-mail address, personal identification number, registration number, photo, fingerprints, diagnostics, biological material, when it is possible to identify a person from the data or in combination with other data.” በማለት ይገልጸዋል። ይህም አባባል በአጭሩ “የግል ዳታ ማለት ከአንድ የታወቀ ግልሰብ ጋር የተቆራኙ ግላዊ መረጃዎችን የሚያመለክት ሆኖ እንደ ስም፣ አድራሻ፣ መለያ ቁጥር፣ የአሻራ መለያ፣ የምዝገባ ቁጥር፣ የጤና ምርመራ ውጤት፣ ፎቶ፣ ኢሜል፣ እና ስነ-ህይወታዊ መረጃዎችን (እንደ DNA) ሊይዝ ይችላል። ይህም መረጃ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ በራሱ ካልሆነም ከሌላ መሰል መረጃ ጋር በማነፃጸር የሰውየውን ማንነት ለመለየት ያገለግላል ማለት ነው።
በዚህ መነሻነት ወደ እኛ ህግ ስንመጣ የግል ዳታ ጥበቃን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1321/2016 ዓ.ም አንቀጽ 2(1) ላይ አስቀድሞ “ዳታ” ለሚለው ቃል እንደሚከተለው ራሱን የቻለ ፍች ሰጥቶታል። በዚህም ዳታ ማለት፣
ሀ) ለታቀደ ዓላማ አስቀድሞ በተሰጠው ትእዛዝ መሰረት ራስ አዘዝ በሆነ መሳሪያ በመቀናበር ሂደት ላይ ያለ፤ “ራስ አዘዝ መሳሪያን እንግሊዝኛው (Operating Automatically) ይለዋል።
ለ) በፊደል ተራ (ሀ) በተጠቀሰው መሳሪያ እንዲቀናበር ታሰቦ የተሰበሰበ፤
ሐ) በአንድ የመዝገብ ሥርዓት አካል እንዲሆን ወይም የመዝገብ ሥርዓቱ የተወሰነ ክፍልን ለማሟላት ታቅዶ የተመዘገበ፤ ወይም
መ) በፊደል ተራ (ሀ)፣ (ለ) እና (ሐ) ሥር የማይወድቅ ነገር ግን ሌላ ለሕዝብ ተደራሽና የመዝገብ አካል የሆነ፤ መረጃ ነው በሚል ተርጉሞታል። በሌላ በኩል ለግል ዳታ የሰጠውን ትርጉም ስንመለከት፣-
የግል ዳታ የሚለውን አገላለጽ በሚመለከት ከሞላ ጎደል ከላይ ከሰፈረው ትርጉም ጋር ተቀራራቢ የሆነ ትርጉም በአንቀጽ 2(2) ላይ እንደሚከተለው ሰፍሮ እናገኛለን፣ “የግል ዳታ” ማለት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ በተለይም ስምን፣ መለያ ቁጥር ፣ የስልክ ቁጥርን ፣ የኢንተርኔት መለያ አድራሻን ፣ የቦታ ዳታን ፣ የኦንላይን መለያን ወይም ከአንድ በላይ ከሆኑና ከአንድ የተፈጥሮ ሰው ጋር ተያያዥ ከሆኑ የአካላዊ ፣ የፊዚዎሎጂ ፣ የዘረ-መል፣ የአዕምሮ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ወይም የማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር ተያያዥ የሆኑ መለያዎችን በመጠቀም ተለይቶ ከሚታወቅ ወይም ተለይቶ ሊታወቅ ከሚችል የተፈጥሮ ሰው ጋር የተገናኘ ማንኛውም መረጃ ነው ሲል ያስቀምጣል።
እዚህ ላይ ከላይ ከተመለከትነው ትርጉም የሚለየው አዋጁ ጥበቃ የሰጠው በተፈጥሮ ሰው የተያዘ የግል ዳታ ብቻ መሆኑ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንቀጽ 2(9) የግል ዳታ ባለቤት-” ማለት በግል ዳታ ላይ ባለቤት የሆነ የተፈጥሮ ሰው ነው፤ የሚል ግልጽ ድንጋጌም ይገኛል። ይህ አገላለጽ የህግ ሰውነት ባላቸው ተቋማት የተያዙ ዳታዎችን በተለይም ከንግድ፣ ከውል፣ ከምዝገባና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሊኖሩ የሚችሉ ዳታዎችን ጥበቃ የሚያሳጣ ቢሆንም በሌላ በኩል በተለይም አርቲፊሻል ኢንተሊጀንት (AI)ን ጨምሮ በቴክኖሎጂ ቅንብር የሚፈጠሩ መረጃዎችን ከመከላከል አኳያ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።
አዋጁ ከዚህም በተጨማሪ በአንቀጽ 2(5) መሰረት ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል ዳታ ምን ምን እንደሚያካትት ዘርዝሮ አስቀምጧል፣ በዚህም፣ የአንድ የተፈጥሮ ሰው ዘርን ወይም ብሔርን፣ የዘረ-መል ወይም የማንነት አካላዊ ዳታን፣ የአካላዊ ወይም የአዕምሯዊ ጤንነት ወይም ሁኔታን፣ የፖለቲካ አመለካከትን፣ የሙያ ማኅበር አባልነትን፣ ሃይማኖትን ወይም ሌላ ሃይማኖት ነክ አስተሳሰብን፣ የተፈጸመ ወይም ተፈጸመ የተባለ ወንጀልን፤ የተፈጸመ ወይም ተፈጸመ የተባለ ወንጀልን አስመልክቶ የተካሄዱ ሂደቶችን፣ እነዚህ ሂደቶች የተጠናቀቁበት መደምደሚያን ወይም በሂደቶቹ ዙሪያ ፍርድ ቤቶች የሰጡት የቅጣት ውሳኔን፣ ይዘትንና ሜታ ዳታን ወይም ገላጭ ዳታን ጨምሮ ያሉ የመልዕክት ልውውጥ ዳታ ፣ወይም ባለሥልጣኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል ዳታ ነው በማለት የሚወስነው ሌላ የግል ዳታን የተመለከተ መረጃ ነው በማለት ያስቀምጣል። ይህ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የዳታ ክፍል በአዋጁ አንቀጽ 10(1) መሰረት ሚኒስቴሩ በሚያወጣው ደንብ ሌሎችንም ሊያካትት ይችላል።
የአዋጁ ተፈፃሚነት ወሰን
አዋጁ በአንቀጽ 3 ስር በግልፅ እንዳስቀመጠው “በሙሉ ወይም በከፊል ራስ አዘዝ በሆነ መሳሪያ፣ እንደዚሁም የመዝገብ ሥርዓት አካል የሆነ ወይም የመዝገብ ሥርዓት አካል እንዲሆን የታሰበና ራስ አዘዝ ባልሆነ መሳሪያ በሌላ መንገድ በሚደረግ የግል ዳታ ማቀናበር ላይ፣ ተፈፃሚ ይሆናል። ከቦታ አንፃር ስንመለከተው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በፌደራልና ክልል መንግስታት ውስጥ የግል ዳታ የማቀናበር ኃላፊነትና ተግባር ባላቸው የግል እና የመንግስት ተቋሞች ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። ይህም ማለት የትኛውም በዚህ አዋጅ መሰረት ፈቃድ ወስዶ የዳታ ማቀናበር ስራ የሚሰራ ድርጅትም ይሁን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስልጣን ያለው የመንግስት መስሪያ ቤት በህጉ የተካተቱ ዝርዝር ክልከላዎችን የማክብር ግዴታ ይኖርበታል ማለት ነው።
በሌላ በኩል አንድ ግለሰብ ለግሉ ወይም ለቤተሰቡ ግልጋሎት ለመስጠት በሚደረጉ፤ በመንግስት ተቋማት መካከል አንድን ጉዳይ ለማጣራት በሚደረጉ የመረጃ ልውውጦች ላይ የሚያተኩሩ፤ በዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት ላይ የተጣሉ ገደቦች ተብለው በተለዩ፣ እና ከውጭ አገራት በመነጩ እንዲሁም በኢትዮጵያ አልፈው ወደ ሶስተኛ አገራት የሚሻገሩ የግል ዳታ ማቀናበሮች ላይ ይህ አዋጅ ተፈፃሚ አይሆንም። አንቀጽ 3(2)
የግል ዳታ ጥበቃና የጥበቃ ጊዜ ርዝማኔ
አዋጁ ዝርዝር የግል ዳታ ጥበቃ ሂደቶችን ማለትም፣ ህጋዊና ህገ-ወጥ ዳታ ማቀናበርን፣ ከማስተላለፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እና መሰል ይዘቶችን አካቷል። ከዚህ አንፃር የሚከተሉትን ዋናዋና መብቶች ማንሳት ይቻላል፣
ሀ) መረጃ የማግኘት መብት፣ ማንኛውም የዳታ ተቆጣጣሪ ወይም አቀናባሪ የዳታ ባለቤቱን ማሳወቅና በግልጽ ካልተከለከለ በቀር ሙሉ ፈቃድ ማግኘት አለበት፣ አንቀጽ 24፣ 2(14)
ለ) የመረጃ ተደራሽነት መብት፣ ተቃራኒ ክልከላ ከሌለ በስተቀር የዳታው ባለቤት በራሱ ስም የተያዙ ዳታዎችን አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጠው ሲጠይቅ ይህንኑ የማግኘት መብት አለው።
ሐ) ዳታን የመደምሰስ መብት፣ የዳታው ባለቤት ዳታው ከአላማው አንፃር አስፈላጊ ካልሆነ፣ ዳታ እንዲቀናበር የሰጠው ፈቃድ ከተነሳ፣ ዳታ የተቀናበረበትን መሠረት ከተቃወመ እና ለማቀናበር ከፍ ያሉ ሕጋዊ ምክንያቶች የሌሉ ከሆነ፤ ወይም የግል ዳታ የተቀናበረው ሕጋዊ መሠረት ሳይኖረው ከሆነ የግል ዳታው ያለ ምንም ክፍያና ያላግባብ መዘግየት እንዲደመሰስ የማድረግ መብት አለው።
መ) የመቃወም መብት፣ የዳታ ተቆጣጣሪው ከዳታ ባለቤቱ ፍላጎቶች፣ መብቶች እና ነፃነቶች ከፍ ያሉ ወይም ሕጋዊ መብቱን ለማቋቋም፣ ለመተግበር ወይም ለመከላከል የሚያስችሉ ሕጋዊ ምክንያቶችን በጽሑፍ ዘርዝሮ ካላቀረበ በስተቀር፤ የዳታ ባለቤቱ የግል ዳታው እንዳይቀናበር በማንኛውም ጊዜ በጽሑፍ የመቃወም መብት አለው። (አንቀጽ 29)
ሰ) የማስተካከል መብት፣ የዳታ ባለቤት የግል ዳታው ትክክለኛ ያልሆነ ፣ ያልተሟላ ፣ አሳሳች፣ ወቅታዊ ያልሆነ፣ ወይም የሚቀናበረው ከዚህ አዋጅ በተቃራኒ ነው ብሎ በሚያምንበት ጊዜ፣ የዳታው ባለቤት ዳታው ያለምንም ክፍያና ያላግባብ መዘግየት የዳታ ተቆጣጣሪው እንዲያስተካክል የማድረግ መብት አለው። (አንቀጽ 27)
ረ) ማቀናበርን የመገደብ መብት፣ የዳታ ባለቤቱ በዳታው ትክክለኛነት ላይ ተቃውሞ ያቀረበና የዳታ ተቆጣጣሪው የዳታውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንዲችል ጊዜ የተሰጠው፣ የዳታ ተቆጣጣሪው ለማቀናበር የማይፈልገው፣ ነገር ግን የዳታው ባለቤት ሕጋዊ መብቱን ለማረጋገጥ፣ ለመተግበር ወይም ለመከላከል የሚፈልገው የግል ዳታ፣ የዳታ ማቀናበሩ ሕጋዊ መሠረት የሌለው፣ እና የዳታው ባለቤት የግል ዳታው እንዳይደመሰስ ተቃውሞ ያቀረበና በምትኩ ማቀናበሩ እንዲገደብ የሚል ጥያቄ ያቀረበ፣ ወይም ማቀናበሩ እንዲቆም ተቃውሞ አቅርቦ ከሆነና ዳታ ተቆጣጣሪው ያለው ሕጋዊ ምክንያቶች የዳታ ባለቤቱ ካለው መብት ከፍ ያሉ መሆኑን በማጣራት ሂደት ላይ ያለ ከሆነ የግል ዳታ ማቀናበር እንዲገደብ የመጠየቅ መብት አለው። (አንቀጽ 30)
ከዚህ በተጨማሪ በአዋጁ አንቀጽ 23 ስር የጥበቃ ጊዜን በተመለከተ የሚከተሉትን ተጨማሪ ጉዳዮች እናገኛለን፣
• የዳታ ባለቤት የግላዊነት መብት ከግለሰቡ የሕይወት ዘመን በኋላ ቀጣይነት ያለው መብት ነው፣ (Right of post-mortem protection) የምንለው ማለት ነው።
• የግላዊነት መብት የዳታ ባለቤቱ ከሞተ በኋላ ባሉ አስር ዓመታት ጭምር የጸኑ ናቸው።
• የዳታ ባለቤቱ ሕጋዊ ወራሽ የዳታ ባለቤቱ ከሞተ በኋላ ባሉ አሥር ዓመታት ውስጥ በማንኛውም ጊዜ መብቶቹን ማስከበር ይችላል።
ህጋዊ የዳታ ማስተላለፍ
የግል ዳታ በዋነኝነት በሶስት ዋና ዋና መንገዶች ሊተላለፍ ይችላል፣ የመጀመሪያው የዳታው ባለቤት ዳታው እንዲተላለፍ በጽሁፍ፣ በቃል ወይም በሌላ አውንታዊ ዘዴ ፈቃደኝነቱን ሲገልጽ ነው፣ አንቀጽ 2(14) ፣ አዋጁ በግልጽ የግል ዳታ እንዲቀናበር ወደ ሦስተኛ ወገን የሥልጣን ክልል የሚተላለፈው በዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች መሠረት እና ዳታው የሚተላለፍለት የሥልጣን ክልል ተገቢ የሆነ ጥበቃ የሚያደርግ መሆኑን በማረጋገጥ ነው የሚል መርህን አስቀምጧል። በአዋጁ መሰረት የምዝገባ ፈቃድ ለሌላቸው የዳታ አቀናባሪ ድርጅቶች ማስተላለፍ አይቻልም።
በተለይም ወደሌላ ሶስተኛ የስልጣን ክልል (Jurisdiction) በሚተላለፍበት ጊዜ ተመሳሳይ ጥበቃ መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ሁለተኛው የዳታ መተላለፊያ መንገድ በዳታ ባለቤቱ የህይወት እልፈት ወቅት በህግ የወራሽነት ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት የሚተላለፍ ይሆናል። ይህም ዳታ በህግ አግባብ የሚተላለፍበት (Transfer by law) ሁኔታ እንዳለ የሚያሳይ ነው።
በሌላ በኩል በአንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች የዳታው ባለቤት ፈቃድ ሳያስፈልግ ዳታው ወደ ሶስተኛ ወገን ሊተላለፍ የሚችልበት ሁኔታም አለ። ለምሳሌ በአንቀጽ 19(2) እንደተመላከተው ባለሥልጣኑ ተገቢ የዳታ ጥበቃ ደረጃ በሌለበት ሁኔታ የተወሰነ ዳታ ማስተላለፍ ተገቢ ነው ብሎ ሲያምን የዳታ ባለቤቱን መብት በሚገድብ መልኩ ዳታ ማስተላለፉን ሊፈቅድ ይችላል፣ በተያያዘም ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል ዳታ ከአገር ውጭ ለማስወጣት ሲያስፈልግ በቅድሚያ የባለሥልጣኑን ፈቃድ ማግኘት እንዳለበት በአንቀጽ 22(3) ተመላክቷል። (ጥንቃቄ የሚፈልግ የግል ዳታን በሚመለከት በአንቀፅ 2(5) ላይ ዝርዝር ትርጓሜ ተሰጥቶታል)። በተጨማሪም የግል ዳታ ለታሪካዊ፣ ለስታስቲክስ ወይም ለሳይንሳዊ ምርምሮች ዓላማ ለማሳካት የባለቤቱ ፈቃድ ላይ ገደብ ሊጣልበት ይችላል።
አዋጁን የማስፈጸም ስልጣን ስለተሰጣቸው አካላት፣
ይህንን አዋጅ የማስፈጸም ስልጣን በዋነኝነት ለኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለስልጣን ተሰጥቷል። ይህ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስር ያለና ቀደም ብሎ በአዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሠረት የተቋቋመው ባለሥልጣን መስሪያ ቤት ነው። ባለሥልጣኑ በዋነኝነት የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ተሰጥተውታል፤
የዚህን አዋጅ ተፈጻሚነት ያረጋግጣል፤
ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችል አስፈላጊውን አስተዳደራዊ መዋቅር ይፈጥራል፣ የግል ዳታ ማቀናበር፣
ማስተላለፍ ስራዎች በህጉ መሰረት መከናዎናቸውን ያረጋግጣል፣ በተለይም ጥንቃቄ የሚሹ የግል ዳታዎች በተገቢወው መንገድ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ እንዲሁም
ይህንን አዋጅ በሚጥሱ አካላት ላይ ተገቢ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ይወስዳል። በተጨማሪም በሀጉ አንቀጽ 5 ተለይተው የተሰጡትን ሌሎች ዝርዝር ኋላፊነቶችን ይፈጽማል።
የአዋጁ ጥሰትና የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት
አስተዳደራዊ እርምጃዎች
ባለሥልጣኑ የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች እና በዚህ አዋጅ መሠረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎችን በመጣስ የግል ዳታ የሚያቀናብሩ ሰዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው፡፡ በተለይም ጥሰቱ የተፈጸመው
(ሀ) በተቋም ከሆነ፤
(ለ) ጥንቃቄ በሚፈልግ የግል ዳታ ዙሪያ የተፈጸመ ከሆነ፤ ወይም
(ሐ) ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ የግል ዳታን የሚመለከት ከሆነ በጉዳዩ ላይ አቤቱታ ከተመሰረተበት ዓመት በፊት ባለው የሥራ ዘመን ተቋሙ ከሚያካሂደው የንግድ ሥራው ካገኘው ጠቅላላ ሽያጭ እስከ አራት ፐርሰንት(4%) ያህል መቀጮ ይቀጣል፡፡ በድርጊቱ የተገኘ ፍሬ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል።
ይሁን እንጂ አዋጁ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚያስወስዱ ዝርዝር ድርጊቶች የትኞቹ እንደሆኑ በደንብ ይወጣል በማለት ቢያስቀምጥም ይህ ጽሁፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የተባለው ደንብ አልወጣም። በአዋጁ በግልጽ የተቀመጠ የአቤቱታ ማቅረቢያ የጊዜ ገደብም እንዲሁ አልተካተተም።
የወንጀል ተጠያቂነት
ማንኛውም ሰው ከዚህ በታች ወንጀል ተብለው የተዘረዘሩትን ድርጊቶች ፈጽሞ የተገኘ እንደሆነ የተቀመጡት የእስርና የገንዘብ መቀጮዎች ይፈጸሙበታል፣
ሀ) የግል ዳታ ጥሰትን ካላሳወቀ፣
ለ) የግል ዳታ ጥሰት ተፈጽሞ ሲገኝ ተገቢውን የቴክኒክና ተቋማዊ እርምጃዎች ካልወሰደ የግል ዳታ በአዋጁ ከተደነገጉት የማቀናበር መርሆዎች ውጪ ካቀናበረ፤ ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራ ወይም ከብር ከ50000 (ሃምሳ ሽ) እስከ 100000 (መቶ ሽ) በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል።
፪/ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተደነገጉና የግል ዳታ ባለቤት የግል ዳታው
ሀ) እንዲደመሰስ የማድረግ፣
ለ) እንዳይቀናበር የመቃወም፣
ሐ) ማቀናበር እንዲገደብ የመጠየቅ፣
መ) ራስ አዘዝ በሆኑ መሳሪያዎች በሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ ያለውን መብቱን ካላከበረ ከሶስት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከብር 100000 (መቶ ሽ) እስከ 200000 (ሁለት መቶ ሺ) በሚደርስ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል።
፫/ ማንኛውም ሰው
ሀ) የግል ዳታ ባለቤቱ ተለይቶ እንዳይታወቅ የተደረገን የግል ዳታ ተለይቶ እንዲታወቅ ካደረገ፤
ለ) ተለይቶ የታወቀውን የግል ዳታ ካቀናበረ፤
ሐ) የግል ዳታን ከሸጠ ወይም ለሽያጭ ካቀረበ፤ ወይም ለሽያጭ ካቀረበ፤ ወይም
መ) የግል ዳታን በአዋጁ ከተደነገገው ውጪ ከአገር ውጪ ካስተላለፈ አምስት ዓመት አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 200000 (ሁለት መቶ ሽ) እስከ 600000 (ስድስት መቶ ሽ) በሚደርስ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል።
ከዚህ ባለፈ እነዚህ ድርጊቶች ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ወይም የሞራል ጉዳት አስከትለው እንደሆነ ድርጊት ፈፃሚው ተገቢ ካሳ የመክፈል ፍትሀብሄራዊ ሃላፊነት ይወድቅበታል።
ማጠቃለያ
በዚህ አጭር ጽሁፍ ዋና ዋና የግል ዳታ ጥበቃ መርሆዎች፣ እውቅና የተሰጣቸው መብቶቸን፣ ዝርዝር የማስፈጸም ስልጣን የተሰጣቸውን ተቋማትን ከአዲሱ የግል ዳታ ጥበቃ አንጻር ለመዳሰስ ጥረት ተደርጓል። ይሁንና የግል ዳታ ጥበቃ ጉዳይ በአንድ አዋጅ ተጠቃሎ የማያልቅ አይሆንም። በዚህም ምክንያት ውጤታማ ጥበቃ ይኖር ዘንድ በርካታ ዘርፎችን የሚገዙ ህግጋትን መሰረት ያደረገ ጠንካራ ተቋም መገንባት ይጠይቃል። ለምሳሌ በዚህ ጽሁፍ ከተዳሰሰው አዋጅ በተጨማሪ የፍትሃብሄር ህጉ፣ የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን አዋጁ፣ የወንጀል ህጉ፣ የኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ፣ የሰነድ ምዝገባና ማረጋገጥ አዋጅ፣ የካፒታል ማርኬት አዋጅና የመሳሰሉት ህጎች ሁሉ የግል ዳታን በሚመለከት ልዩ ልዩ ይዘቶችን አካተዋል። በዚህም ምክንያት የግል ዳታ ጥበቃ በአገራችን በጅማሮ ላይ ያለና አሁንም ድረስ በተቋም ደረጃ ብዙ የሚቀሩት ዘርፍ ቢሆንም ያለንበት ወቅት ዘርፉን በልዩ ትኩረት ማየት የሚጠይቅ ነው።
የፍትህ ሚኒስቴርን
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter