የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን “የተከዜ ዘብ” ያላቸውን ማስመረቁን ተከትሎ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ መግለጫ በማውጣት መቃወሙ የሚታወስ ነው። ይህንኑ አስመልክቶ ዞኑ “ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም አጀንዳችን ሰላም ነው!” በሚል ርዕስ ምላሽ ሰጥቷል። የተከዜ ዘብ የራሱን የማይሰጥ፣ የራሱን ሰላም የሚያስጠብቅ ኃይል እንደሆነ ገልጿል።
” … የራሱንና የአካባቢውን ውስጣዊ ሰላም ከሰርጎ ገቦች፣ ከወያኔ መንገድ ጠራጊ ኃይሎች፣ ከባንዳዎች ሲጠብቅ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ የተከዜ ዘብ፣ የሰላም ዘብ ሲሆን በዞኑ ሕዝብ የተዋቀረ የዞኑ ሰላም አስከባሪ እንጂ የማንንም አልፎ የማይጠይቅ፣ የራሱን ማንነት አሳልፎ የማይሰጥ እና የጠባ-ጫሪነት አጀንዳ የሌለው ኃይላችን ነው” ሲል መግለጫው ዘብ ያስመረቀበትን ምክንያት ገልጿል።
በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው ትህነግ ባሰራጨው መግለጫ “በወረራ የተያዘ የትግራይ ምዕራባዊ ዞን” የሚለው አካባቢ አሁን ላይ በአማራ ክልል ስር ሆኖ እየመራ ያለው ክፍል አካሄድ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ እንደሆነ ገልጿል።
በትግራይ ክልል ያሉ ህገ ወጥ የታጠቁ ኃይሎች ለቀው መውጣት እንዳለባቸው በማሳሰብ መግለጫ ያወጣው ትህነግ፣ የኤርትራ ወታደሮች ስለወረሩት አካባቢ አላነሳም። በመግለጫው የራያ ስም ግን አካቷል።
መግለጫውን ወደ አማርኛ በመመለስ ያስራጩት እንዳሉት ትህነግ የፊደራል መንግስት ይህን ጸብ አጫሪ የሆነ ድርጊት ሊያስቆም እንደሚገባ ጠይቀዋል። ድርጊቱ የሰላም ማስፈኑን እንቅስቃሴ ላይ የተለየ ተግዳሮች እንደሚያስከትልም አመልክተዋል። በጉዳዩ ዙሪያ ከፌደራል መንግስት በይፋ የተሰጠ መግለጫም ሆነ ምላሽ ይህ እስከተጻፈ ድረስ አልተደመጠም።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንን ባወጣው መግለጫ ሰላምን ሊያደፈረስ የሚችል አንዳችም ጉዳይ እንደሌለ አመልክቷል። ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚል መግለጫ ማውጣቱን ያመለከተው ዞኑ፣ “በትህነግ የግፍ አገዛዝ ለ27 ዓመታት ሲማቅቅ፣ ሲገደልና ሲፈናቀል ለኖረው ሕዝባችን ሰላም ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ሰላሙን ለማረጋገጥ ያለ እንቅልፍ ይሠራል፣ ይተጋል፣ ያተጋል፣ ለአማራዊ ማንቱ ዘብ ሁኖ ይቆማል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። መግለጫውን ከስር ያንብቡ።
ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም አጀንዳችን ሰላም ነው!
ሕወሓት ሚያዚያ 10/2017 ዓ.ም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞንን የተመለከተ መግለጫ ማውጣቱን ለመረዳት ችለናል፡፡
ቡድኑ በመግለጫው እንደተለመደው ራሱን የሰላም ዘብ አደርጎ በማቅረብ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሚያደርገውን የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ በጸብ-አጫሪነት ወንጅሏል፡፡
ከሕወሓት ጥንተ-ተፈጥሮ አንጻር የወጣው መግለጫና የመግለጫው ይዘት የሚያስገርም ባይሆንም፣ አንዱ ወገን የፈለገውን ተናግሮ ሌላው ጉዳዩን በዝምታ ማለፉ የዚያኛውን ወገን መሠረተ-ቢስ ውንጀላ የእውነተኛነት ገጽታ ስለሚያላብሰው፣ ይህን አጭር ማስታወሻ ለማቅረብ ተገደናል፡፡
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ የትላንትም፣ የዛሬም፣ የነገም መሪ አጀንዳ ሰላምና ሰላም ብቻ ነው፡፡
በሕወሓት የግፍ አገዛዝ ለ27 ዓመታት ሲማቅቅ፣ ሲገደልና ሲፈናቀል ለኖረው ሕዝባችን ሰላም ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ሰላሙን ለማረጋገጥ ያለ እንቅልፍ ይሠራል፣ ይተጋል፣ ያተጋል፣ ለአማራዊ ማንቱ ዘብ ሁኖ ይቆማል፡፡
መላው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ ራሱን በሰላም አስከባሪነት በማዘጋጀት የራሱንና የአካባቢውን ውስጣዊ ሰላም ከሰርጎ ገቦች፣ ከወያኔ መንገድ ጠራጊ ኃይሎች፣ ከባንዳዎች ሲጠብቅ ቆይቷል፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ የተከዜ ዘብ፣ የሰላም ዘብ ሲሆን በዞኑ ሕዝብ የተዋቀረ የዞኑ ሰላም አስከባሪ እንጂ የማንንም አልፎ የማይጠይቅ፣ የራሱን ማንነት አሳልፎ የማይሰጥ እና የጠባ-ጫሪነት አጀንዳ የሌለው ኃይላችን ነው ፡፡
ሕወሓት ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን እንዲወጣለት የጠየቀው የዞኑን ሕዝብ ነው፡፡ በርግጥ ከፍ ብሎ እንደተገለጸው፣ ለእኛ ሕወሓት ይህን ማለቱ ፈፅሞ አያስገርመንም፡፡
ሕወሓት ከጥንት እስከ ዛሬ የማያከብረውን ሕገ መንግሥትና ፌዴሬሽን ደግሞ ደጋግሞ የሚጠቅስ፤ የማያምንበትንና የማያከብረውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ደግሞ ደጋግሞ የሚያወሳ ቡድን እንደሆነ አሳምረን እናውቃለንና፡፡
ስለሆነም ሕወሓት የሚፈልገው የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ እንደለመደው ከርስቱ አፈናቅሎና ጨፍጭፎ የአማራ ርስት የሆነውን የወልቃይት ጠገዴን ለም መሬት መጠቅለል እንደሆነ ግልጽ ነው።
ቡድኑ አካባቢውን በጉልበት በወረረበት ዘመን ያደረሳቸው ግፎችና በደሎችም ሆነ በጎረቤት አገር ያሉ ተዋጊዎቹ በወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ላይ እያደረሱት ያለው ማሳደድና መጨፍጨፍ የቡድኑን ፍላጎትና ቋሚ ዓላማ በማያሻማ መልኩ ፍንትው አድርገው የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡
በመሆኑም ከመግለጫው ለመረዳት እንደሚቻለው ወያኔ አጭበርባሪና ቁማርተኛ ቡድን መሆኑን ፀሐይ የሞቀው፣ ሕዝብ ያወቀው ነውና አዲሳችን አይደለም!
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዛሬም እንደ ትላንቱ ሕግንና ሕገ መንግሥትን መሠረት አድርጎ ሰላሙንና ነፃነቱን አስጠብቆ ለመኖር ይሰራል፣ ለሀገር ዳር ደንበር በጎ ጠረፍ ጠባቂ ሁኖ ይቀጥላል፡፡
የፕሪቶሪው ስምምነት በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ያለንን ቁርጠኝነትም ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ የስምምነቱ በተሟላ ሁኔታ ተፈጻሚ መሆን፣ ለዞናችን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊያን ዘላቂ ሰላም በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለንና!
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን
ሁመራ ከተማ
ሚያዚያ 12/2017 ዓ.ም
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter