በተደጋጋሚ በዜና መፋለስና መዛባት ስሙ እየተነሳ ያለው ሪፖርተር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አስመልክቶ ያወጣውን ዜና አስመልክቶ የኢኮኖሚ ባለሙያ ገልለተኛ አስተአየት ሰጥተዋል። ሪፖርተር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ 2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የ8 ወራት ሪፖርት ሲያቀርብ፣ ባንኩ ካለበት አጠቃላይ የብድር ክምችት፣ አንድ ትሪሊዮን ብር ዕዳ የመንግስት ነው” ሲል በመሪ ዜናው ማተሙ ነበር “ሰህተት ነው” በሚል ባንኩ ዝርዝር ምላሽ የሰጠበት።
የሪፖርተር ጋዜጣ ይህን ቢልም “በዚህ በጀት ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት ለመንግስት አንድም ብር በቀጥታ አላበደርኩም” ሲል ባንኩ ዘርዝሮ ማብራሪያ መስጠቱና ማስተባበያ ጠይቆ ነበር።
እንደ ባንኩ መግለጫ ከሆነ መንግስት ከሀገር ውስጥ የንግድ ባንኮች በቀጥታ የመበደር አሰራርም ሆነ ልምድ እንደሌለው ገልጾ ነበር የሪፖርተርን ዜና ዋጋ ቢስ ያደርገው። አያይዞም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ብድር መስጡቱን ጠቅሶ ይህ ግን መንግስት በቀጥታ የተበደረው ሳይሆን፣ የልማት ድርጅቶች የተበደሩት ዕዳ ነው ብሏል።
“…የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከአስፈፃሚው መንግስት የተለዩና የራሳቸው ካፒታል ያላቸው፣ እንደ ማንኛውም ድርጅት የንግድ ፍቃድ አውጥተው የሚነግዱ፣ በድርጅታቸው ስም ገንዘብ የሚበደሩ፣ ሊያተርፉም ሆነ ሊከስሩ የሚችሉ፣ ለትርፍ የተቋቋሙ የልማት ድርጅቶች ሲሆኑ ብድሮቹንም የወሰዱት ለራሳቸው ፕሮጀክቶች በመሆኑ ለእነዚህ ተቋማት የተሰጠውን ብድር የመንግስት ብድር ተደርጎ መወሰዱ ስህተት ነው ” በማለት ባንኩ አመክኒዮ የተመላበት ምላሽ ለሪፖርተ ስህትተ የተሞላበት ለተባለው ዜና ትምህርታዊ ማብራሪያ አቅርቧል።
በዚህ አነጋጋሪ ዜና ባንኩ ካሰራጨው ሰፊ ማስረጃና አመክኒዮ የተላበሰ መረጃ በተጨማሪ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ ማብራሪያ “ለመንግስት የልማት ድርጅቶች የተሰጠ ብድር የመንግስት ዕዳ አይደለም ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ለመሆኑ መንግስት ከንግድ ባንኮች የሚበደረው መቼ ነው፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች (እንደ ቴሌኮሚኒኬሽን፣ ኤሌክትሪክ ሀይል፣ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የመሳሰሉት) ከንግድ ባንኮች የወሰዱት ብድር፣ የመንግስት ብድር ሊባል ይችላል ? የሚል ጥያቄ ከቲክቫህ የተሰነዘረላቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሑሴን ዓሊ ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል።
“ መንግስት የሚባለው አካል በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው ዘርፍ ስራ አስፈፃሚው መንግስት (የፌደራሉና የክልሎች) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የመንግስት የልማት ድርጅቶች (ፐብሊክ ኮርፖሬሽንስ) የሚባለው ነው፡፡ ይህ አገላለፅ ግን በሁሉም ሀገራት ላይ ላይሰራ ይችላል፡፡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ያላቸው ሀገራት አሉ፣ የሌላቸው አሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ሊበራል የሆኑ ሀገራት የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሉዋቸውም፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ እንዲህ ዓይነት ድርጅቶች የሉም፡፡
ስራ አስፈፃሚው መንግስት ለአስተዳደራዊና ለልማት ስራዎቹ የሚሆን ገንዘብ የሚያገኘው ከግብር ከፋዮች፣ ግብር ነክ ካልሆኑ ምንጮች ለምሳሌ በራሱ ከሚያከናውናቸው የኢንቨስትመንት ስራዎች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከሚያመነጩት ገቢ/ትርፍ ነው፡፡
ወጪውንም ከግብር ከሚሰበስበው እና በብድር ከሚያገኘው ገንዘብ ይሸፍናል፡፡ ብድር ስንል የውጭ ብድር አለ፣ የሀገር ውስጥ ብድር አለ፡፡ የሀገር ውስጥ ብድር፣ ከግል ባንኮችና ከመንግስት ባንኮች የሚበደረው ገንዘብ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ እንግዲህ መንግስት የምንለው አካል፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌደራል ያለው ስራ አስፈፃሚ አካል የሚበደረው ነው፡፡
መንግስት ለአስተዳደራዊና ለካፒታል ወጭዎቹ ሊበደር ይችላል፡፡ የበጀት ጉድለት ሲገጥመው ሊበደር ይችላል፣ የካፒታል ወጭዎቹንም ለመሸፈን ሊበደር ይችላል፡፡ ግን አሁን ላይ መበደር ያቆመ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ይህ ብድር በአጠቃላይ ዝቅተኛ ነው፡፡
አሁን የቅድሙ አገላለፅ እዚህ ጋር ይመጣል፡፡ መንግስት ተበደረ ስንል ምን ማለታችን ነው ? ይህ ብድር፣ ከፌደራል እስከ ክልል ያሉት ስራ አስፈፃሚ መንግስታት የወሰዱት ነው ወይስ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ? ዝም ተብሎ መንግስት ተበደረ ማለት አንችልም፣ ይህ ስህተት ነው፡፡
መንግስት የሚወስደውና የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚወስዱት ብድር ይለያያል። የልማት ድርጅቶች የተበደሩት ብድር የመንግስት ብድር ሊባል አይችልም፡፡ እናም፣ በንግድ ባንክ ሀሳብ እስማማለሁ፡፡
እነዚህ ድርጅቶች የራሳቸው የማቋቋሚያ ስርዓት፣ ህጋዊ ቁመና፣ የራሳቸው ካፒታል፣ የአሰራር ስርዓት ያላቸውና ዋስትና አሲይዘው የሚበደሩ ናቸው፡፡ የፕሮጀክት ስራዎቻቸውን ለማስፈፀም ሊበደሩ ይችላሉ፡፡ ዕዳቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለባንኩ መክፈል ሲያቅታቸው ግን መንግስት ሐላፊነት አለበት፣ ምክንያቱም ተቋማቱ የመንግስት ናቸው፡፡
ያለባቸውን ዕዳ ሳይሰርዝ አሰራሮቻቸውን እንዲያሻሽሉና ትርፋማ እንዲሆኑ በማድረግ፣ ዕዳቸውን በሒደት እንዲከፍሉ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ከእነሱ ገቢ እየሰበሰበ የባንክ ዕዳቸውን በረዥም ጊዜ እንዲከፍሉ ያደርጋቸዋል፡፡ በአስር አመትም፣ በሀያ አመትም እያመረቱ ገቢ እያስገኙ ለመንግስት ይከፍሉታል፣ መንግስት ደግሞ ያንን ገቢያቸውን ሰብስቦ፣ ለተበደሩበት ባንክ ዕዳቸውን ይከፍላል፡፡ እንደዛ ስለሆነ ግን ዕዳው የመንግስት ነው ሊባል አይችልም፡፡
መንግስት የተበደረው ብድር ከሆነ ገንዘብ በማተም ሊከፍለው ይችላል፣ ወይም ከሚሰበስበው ግብር ዕዳውን ሊከፍለው ይችላል፡፡ መንግስት የሚበደረው በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ነው (የመንግስትን የፋይናንስ ገቢና ወጪ የሚያስተዳድረው እሱ ስለሆነ)፡፡ የብድር አከፋፈሉ ራሱ የተለያየ ነው፣ ዓላማውም የተለየ፡፡
ብሔራዊ ባንክም በአመታዊ ሪፖርቱ ሲያቀርበው የፐብሊክ ሴክተር ብድር (የመንግስት የልማት ድርጅቶች ብድር) እና የመንግስት ብድር ብሎ ነው በሁለት ከፍሎ የሚያቀርበው ” ብለዋል።