የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ለስድስት የልማት መርሃ ግብሮች የሚውል የ240 ሚሊየን ዩሮ (32 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር) ድጋፍ አደረገ። የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴና በኢትዮጵያ የህብረቱ ተወካይ አምባሳደር ሶፊ ኢመስበርገር ተፈራርመዋል። ኢትዮጵያና የዓለም ባንክ የ96 ነጥብ 367 ሚሊየን ዶላር የድጋፍና ብድር ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፥ ድጋፉ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገች ባለችበት ወቅት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። አምባሳደር ሶፊ ኢመስበርገር በበኩላቸው፥ ድጋፉ ከሁሉም የህብረቱ አባል ሀገራት የተሰበሰበ መሆኑን ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያን ልማትና ኢኮኖሚ እንደሚውል ገልጸዋል።
ድጋፉ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከርና የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ለመደገፍ እንዲሁም የሥርዓተ ፆታ እኩልነትና ማህበራዊ ትስስርን ለማሳደግ እንደሚውል ተገልጿል።በተጨማሪም የዴሞክራሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተከሰቱ ግጭቶች ማገገሚያ የሚሆን ነው ተብሏል።
ብቅርቡ ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል የሚውል የ96 ነጥብ 367 ሚሊየን ዶላር ወይም የ12 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የድጋፍ እና ብድር ስምምነት መፈራረማቸው ይታዋሳል።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና በዓለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር ማሪያም ሳሊም ተፈራርመዋል። ከተፈረመው ስምምነት ውስጥ 50 ሚሊየን ዶላሩ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር በብድር መልክ የተሰጠ ሲሆን÷ 46 ነጥብ 367 ሚሊየን ዶላሩ ደግሞ ከዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት ፈንድ በድጋፍ የተገኘ መሆኑ ተገልጿል።

ድጋፉ የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የሚውል ነው መባሉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል። በተለይም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ደረጃ ያሉ መምህራንን አቅም ለመገንባት እንዲሁም ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተጣጣመ መልኩ የቅደመ መምህርነት ስልጠናዎችን ለመስጠት እንደሚውል ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም ለማጎልበት፣ የሴት አመራሮችን ለመደገፍ እና በዲጂታል የታገዘ ሥርዓት ትምህርትን ለመገንባት የሚያግዝ እንደሆነ ከመንግስት መገናኛ ሪፖርቶች ለመረዳት ተችሏል።