በሀረር ከተማ በአንድ ግለሰብ ቤት በህገወጥ መንገድ የተከማቸ ከ10 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀረሪ ክልል ፖሊስ አስታውቋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ጣሰው ቻለው እንዳሉት፤ በክልሉ ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን ለማስቆም በተሰራው ስራ በአንድ ግለሰብ ቤት ተከማችቶ የተገኘን ከ10ሺ ሊትር በላይ ነዳጅ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ነዳጁ የተያዘው ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በሕገ ወጥ መንገድ በቤት ውስጥ ተከማችቶ የተገኘ ነው ብለዋል።
ነዳጅን በጄሪካን እና በሀይላንድ በህገ ወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤታቸው ደብቀው የተገኙት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ የሚያስገባው ነዳጅ ለታለመለት አላማ ሊውል ይገባል ያሉት ኮማንደሩ በህገወጥ የነዳጅ ግብይት በሚሳተፉ አካላት ላይ በቀጣይም የተጠናከረ ክትትል በማድረግ አስተማሪ የሆነ እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክተዋል።
በቀጣይም ሕገ ወጥ ነዳጅን ጨምሮ ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉም ኮማንደር ጣሰው መጠቆማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመልክቷል።
ማህበረሰቡም በአካባቢው ሕገ ወጥ የነዳጅ ግብይትን ሲመለከት እንደተለመደው በአካባቢው ለሚገኝ የፖሊስ ጽ/ቤት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፈዋል።
