ዶናልድ ትራምፕ የአዕምሮ ጤናቸውን ለማረጋገጥ በተሰጣቸው ፈተና 30 ከ30 ማግኘታቸውን ዋይት ኃውስ አስታወቀ። ትራምፕ “በግሩም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።
ትራምፕ በሁለተኛ የፕሬዝደንትነት ዘመናቸው የመጀመሪያውን የጤና ምርመራ ዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ በሚገኝ ሆስፒታል ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝደንቱ ባለፈው ሐምሌ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ምክንያት “ቀኝ ጆሯቸው አካባቢ የጥይት ቁስል” እንዳለባቸው ተገልጿል።
“ፕሬዝደንት ትራምፕ በግሩም ጤንነት ላይ ነው የሚገኙት ልባቸው፤ የነርቭ ስርዓታቸው እና ጠቅላላ አካላዊ ጤናቸው አስደናቂ ነው” ሲሉ ዶክተራቸው ካፕቴን ሾን ባርባቤላ በማስታወሻቸው ፅፈዋል።
ባለፈው አርብ አምስት ሰዓት በወሰደው ዋልተር ሪድ ሆስፒታል በተከናወነው የጤና ምርመራ ትራምፕ በርካታ የደም ምርመራዎች፣ የልብ ምርመራ፣ እና አልትራሳውንድ እንደተደረገላቸው ዶክተራቸው ጠቁመዋል።
“ፕሬዝደንት ትራምፕ ድንቅ የአእምሮ እና የአካል ጤንነት ላይ ነው ያሉት። የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር እና ጠቅላይ አዛዥ ሆነው ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉ ናቸው” ይላል ዋይት ሐውስ እሑድ ይፋ ያደረገው የዶክተሩ ማስታወሻ።
ፕሬዝደንቱ የአእምሮ ጤናቸውን ለማወቅ በሚል ፈተና እንደተሰጣቸው እንዲሁም ሌሎች የአእምሮ ፍተሻዎች እንደተደረጉላቸው ማስታወሻው ጠቅሶ ድባቴም ሆነ ጭንቀት እንደሌለባቸው አስታውቋል።
ዶ/ር ባርባቤላ እንዳስታወቁት ትራምፕ ሞንትሪያል ኮግኒቲቭ አሰስመንት የተሰኘው ፈተና ተሰጥቷቸው 30 ከ30 ደፍነዋል።
ይህ ፈተና የሚሰጠው የአእምሮ ጤናን ለመፈተሽ እና የመርሳት በሽታ አደጋ አለ ወይ የሚለውን ለማወቅ ሲሆን እንስሳትን መሰየም፣ ስዕል እና ቃላትን ደጋግሞ መጥራት የፈተናው አካል ናቸው።
ቅዳሜ ኤር ፎርስ ዋን ወደተሰኘው አውሮፕላናቸው ከመሳፈራቸው በፊት ለጋዜጠኞች ንግግር ያሰሙት ትራምፕ “ሁሉንም ጥያቄ በትክክል መልሻለሁ” ብለዋል።
በዶክተሩ ማስታወሻ መሠረት ፕሬዝደንቱ የኮሌስትሮል መጠናቸው ለመቆጣጠር መድኃኒት የሚወስዱ ሲሆን ለልብ በሽታ አስፒሪን እንዲሁም ለቆዳቸው ጤንነት ደግሞ ሞሜታሶን የተሰኘ ክሪም ይቀባሉ።
ፕሬዝደንቱ ክብደታቸው 101 ኪሎ ግራም፤ ቁመታቸው ደግሞ 1.89 ሴንቲሜትር ገደማ እንደሆነ ማስታወሻው ያሳያል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
via (ጋዜጣ+)