ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከልዑካን ቡድናቸው ጋር በቬየትናም የነበራቸው ይፋዊ ጉብኝት የተሳካ እና “ጉብኝቱ ኢትዮጵያ አስፈላጊ ሀገር መኾኗን ያረጋገጠ ነበር” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጂኦ-ፖለቲካል ነባራዊ ሁኔታ እና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይኾን ከአሁናዊ የብልጽግና ዕይታ እና ፕራግማቲክ ጉዞዋ የሚቀዳ የስኬት ጉዞዋ እጅግ አስፈላጊ ሀገር እየኾነች ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በያዝነው ሳምንት ለይፋዊ መንግሥታዊ ጉብኝት ወደ ቬይትናም አቅንተው ነበር። ጉብኝታቸው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተጀመረበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1976 ወዲህ በሀገር መሪ ደረጃ ሲደረግ የመጀመሪያው እንደኾነም አስፍረዋል፡፡
በሌላ አነጋገር ላለፉት 50 ዓመት ያህል በመሪዎች ደረጃ ያልነበረውን ግንኙነት የቀየረ እጥፋት ኾኗል ነው ያሉት። በዚህም ምክንያት ቬይትናም በመሪዋ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህን የቆየ ወዳጅነት እና ስትራቴጂክ አጋርነትን የሚያጠናክር፣ የመሪያችንን እና የሕዝባቸውን ክብር የሚመጥን እጅግ የደመቀ አቀባበል አድርጋላቸዋለች ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቆይታቸው ከሀገሪቱ ፕሬዝደንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ከኾነው የቬይትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም ብዝኅ ግንኙነቶች ላይ ያተኮረ የሰከነ እና ጥልቀት ያላቸው ውይይቶችን አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) እና ልዑካቸው ከሀገሪቱ ቁልፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋርም የመወያየት እድል አግኝቷል፡፡ የሮቦቲክ እና ሃይቴክ ኢንዱስትሪዎችንም ጎብኝቷል፡፡ ኦሽን ፓርክ በመባል የሚታወቀውን በሀገር በቀል ኩባንያ የሚለማ የከተማ ግንባታ ሥራዎችንም ተመልክቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸው በሁለትዮሽ እና ብዝኅ ግንኙነቶች ላይ ያተኮሩ ውይይቶችን ከማድረጋቸውም በላይ በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሰው ሃብት ልማት እና አቪዬሽን ኢንደስትሪ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ የመግባቢያ ስምምነቶች ፈርመዋል ብለዋል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ልዑኩ አጋርነት ለዕድገት እና ልማት (P4G) ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን ልምድ እና ተሞክሮ አካፍሏል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
የደቡብ ምሥራቅ እስያ አካል የኾነችው ቬይትናም ከቀጣናው ሀገሮች እጅግ በመዘግየት በ1986 በሯን ለዓለም የከፈተች እና የኢኮኖሚ ሪፎርሟን የጀመረች ሀገር ናት፡፡ ለሀገራዊ አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም የተረጋጋ ኢኮኖሚና ፈጣን እድገት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የኢኮኖሚ ሪፎርሟ ዶይ ሞይ (Đổi Mới) ወይም Economic renovation through opening up በመባል የሚታወቅ ነው ብለዋል፡፡
ቬይትናም የኢኮኖሚ ሪፎርሙን መሠረት በማድረግ በጠንካራ ፓርቲ የሚመራ ጠንካራ መንግሥት በመገንባቷ ባለፉት 30 ዓመታት እጅግ አስደናቂ የሚባል የኢኮኖሚ እድገት እና ማኅበራዊ ለውጥ ያስመዘገበች ሀገር ናት፡፡ ከ1990ዎቹ በፊት እጅግ ድሃ ከሚባሉ ሀገሮች ታርታ ተሰላፊ የነበረች ኾን ከነበረችበት እጅግ ጥልቅ የኾነ ድህነት ተነስታ በአንድ ትውልድ ብቻ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ መሰለፍ የቻለች ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ቬይትናም ዛሬ በምግብ ሰብል ራሷን ከመቻል አልፋ በቀጣናው በግብርና ምርቶች በተለይም በሩዝ፣ በቡና፣ ፍራፍሬ እና ሌሎች ምርቶች ግምባር ቀደም ላኪ ሀገር መኾን ችላለች፡፡ የከፍተኛ አምራች ኢንደስትሪ ማዕከል በመፍጠር በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚታገዙ የኤሌክትሮኒክስ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የመጫሚያ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ኤክስፖርት ከሚያደርጉ ሀገሮች ተርታ የምትሰለፍ ናት፡፡
በጠንካራ ፓርቲ የሚመራው የቬይትናም ጠንካራ መንግሥታዊ ቢሮክራሲ፣ ለብዝኅ የኢኮኖሚ ግንባታ በተለይም ለግብርና ልማት እና ኤክስፖርት መር አምራች ኢንዱስትሪዋ ስኬታማነት የላቀ አበርክቶ አለው፤ ሀገሪቱ በዚህ ዕይታ በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በቀጣናው ለነጻ የንግድ ስምምነቶች እና ዝቅተኛ ታሪፍ እንዲሁም በክህሎት እና እውቀቱ የበለፀገ የሰው ኃይል ልማት የሰጠችው ትኩረት ለኢኮኖሚ እድገቷና ልማቷ ውጤታማነት መሠረት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ይፋዊ ጉብኝትም ሀገራችን የጀመረችውን የማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ የሪፎርም ሥራዎችን የሚያጠናክሩ፣ የሁለቱን ሀገሮች ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያጎለብቱ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን የሚያሻሽሉ ልምዶች መቅሰም አስችሏል፡፡ የተገኙ ልምዶች እና ተሞክሮዎችንም ከብዙ በጥቂቱ እንደሚከተለው ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
ተሞክሮ አንድ:-
ለብዝኀ የኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠት እና በፅናት የታገዘ እልህ አስጨራሽ ርብርብ በማድረግ በአንድ ትውልድ የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ብቻ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መዝገብ የሚቻል መኾኑን ከቬይትናም የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ቬይትናሞች ለግብርና ልማት፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም፣ ለሰው ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቶችን በማድረግ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበዋል፤ በዚሁ ባለፉት 30 ዓመታት ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ ያልተቋረጠ እድገት በማስመዝገብ አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገትን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በአንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ከተንጠለጠለ የኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ብዝኀ ሴክተር የኢኮኖሚ ግንባታ ተሸጋግራለች፡፡ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ እቅዷ እና ሪፎርሟ ግብርናን፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ግንባታዋ አዕማድ ወይም ምሰሶ በማድረግ ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት ከሰባት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት በማረጋገጥ ታሪካዊ ሥራ አከናውናለች፡፡ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷንም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ አሳድጋለች፡፡
የቬይትናሞቹ ልምድ እና ተሞክሮም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ አቅጣጫ ትክክለኛነትን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከቬይትናም የተገኘው ልምድ እና ተሞክሮ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሪፎርም በማጠናከር እና ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር በያዘችው መንገድ ከቀጠለች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቬየትናም ካስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት የላቀ እድገት ማስመዝገብ እንደምትችል የሚጠቁም ነው፡፡
ተሞክሮ ሁለት:-
ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የቬየትናም ዜጎች በ1990ዎቹ ዓመታት ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ ነበር። ሆኖም ቬየትናም በተከተለችው የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ በተለይም ለግብርና ልማት በሰጠቸው ልዩ ትኩረት በ2020 ይህን አኃዝ ወደ 4% (በመቶ) ዝቅ እንዲል አድርጋለች:: የግብርና ሪፎርሟ ውጤታማ በመሆኑ ራሷን በምግብ ሰብል ከመቻል አልፋ በሩዝ፣ በፍራፍሬ፣ በቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በቀጣናው ከፍተኛ ላኪ ሀገር ሆናለች::
ይህ በጎ ልምድና ተሞክሮም፣ ኢትዮጵያ ተረጅነትን በመቀነስ፣ ራስን በምግብ ሰብል በመቻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገችው ላለው ሁለንተናዊ ጥረት በእጅጉ ጠቃሚ አስረጂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ አብዮት ራስን ለመቻል ያደረገችው እንቅስቃሴ ስኬታማ ሆኗል፡፡
ከዚህ የተገኘውን ልምድ በመውሰድ አሁን ደግሞ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በሩዝ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ጀምራለች፡፡ በዚህም ረገድ የቬየትናሞች ስኬት ኢትዮጵያ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኗን ከማረጋገጥ ባለፈ ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡
በመሆኑም የጀመርናቸውን መልካም ስራዎች የሚያጠናክሩ የአገር ውስጥ ልምዶችን ከማጎልበት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ በጎ ልምዶች በመቀመር በግብርና ዘርፍ የተጀመረውን መነሳሳት ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቬየትናም ያሉ በግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ የሆኑ አገሮች ኢትዮጵያ ለምትካሂዳቸው የሪፎርም ስራዎች ጥሩ መነሻ ሆኖ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
ተሞክሮ ሶስት:-
ቬየትናም የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ በቀጠናው ካሉ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር በነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ዙሪያ ሰፋፊ ድርድሮችን አካሂዳለች፡፡ በዚህም ረገድ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በየዓመቱ ከ34 ቢሊየን ዶላር በላይ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡ በተለይም እንደ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና የጫማ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መሳብ ችላለች፡፡ ይህም በቀጠናው ከፍተኛ የሚባል የኢንቨስትመን ስበት ማሳያ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ጋር ብዙ ርቀት የተጓዘ ድርድሮችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ድርድሮቹም ውጤት እየተገኘባቸው መጥቷል፡፡ በምስራቅ አፍሪካም ነፃ የንግድ ስምምነት ለመፍጠር ከሀገሮቹ ጋር በርካታ ድርጅሮችን እያካሄደች ነው፡፡ ይህም ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡
በአፍሪካ ኅብረት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ስራ እያከናወነች ነው፡፡ ነፃ የንግድ ቀጠና ድርድር በማካሄድ ቬየትናምን ሰፊና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንድታገኝ ያስቻሏትን የድርድር መንገዶች፣ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎችን በመመርመር ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ ለምትፈጽማቸው ስራዎች እንደየሁኔታው መጠቀም ይገባል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቬየትናም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ታሪፍ እየተጋረጠባቸው መጥቷል፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ታሪፍ፣ ታዳሽ የሃይል አቅርቦት፣ ርካሽ ጉልበት፣ እየዘመነ የመጣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በአንድ ማዕከል ወይም አካባቢ የተሰበሰቡ ኢንዲስትሪዎች መጠናከር እና የነጻ የንግድ እና ኢኮኖሚ ዞኖች መፈጠር እንደ ቬየትናም ላሉ ሀገሮችና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ከዚህ አኳያ ጥሩ ልምድ ለመቅሰም ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም መንገድ የከፈተ ነው፡፡ ይህን ምቹ እድል አጠናክሮ መጠቀም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
ተሞክሮ አራት:-
ቬየትናሞች ለሰብዓዊ ልማት በተለይም ደግሞ ለቴክኒክና ሙያ የሰጡት ልዩ ትኩረት ኢኮኖሚያቸው ይበልጥ እንዲያድግ ረድቷል::
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅባለቸው ከ99 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅበላውም ወደ ዘጠና በመቶ የተጠጋ ነው፡፡ ይህ አሃዝ በመካከለኛ እድገት ደረጃ ካሉት ሀገሮች ከፍተኛው ነው፡፡ ቬየትናም በዓለም አቀፉ የሰብአዊ ልማት index መሰረት ከሲንጋፖር ቀጥላ ሁለተኛዋ የሰብአዊ ካፒታል የገነባች ሀገር ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያም በቅርቡ ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የትውልድ ግንባታ አቅጣጫን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የቬየትናም ጉብኝትም ከዚህ አኳያ ጠቃሚ ልምድ የተገኘበት ነው፡፡ ቬየትናሞች የኢትዮጵያን ሰብዓዊ ሀብት ልማት ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡ በየዓመቱ መጠነኛ ቁጥር ላላቸው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ለመስጠት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አብሮ ለመስራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
ይህንኑም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልገናል፡፡
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቬየትናም የነበራቸው ቆይታ ስኬታማና የኢትዮጵያን አስፈላጊ አጋርነት ያረጋገጠ ነው። የልዑኩም ቆይታ የኢትዮጵያን ያለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ተሞክሮ ለመቃኘትና የጉዞአችንን ትክክለኛነት ከማረጋገጥ ባለፈ መጪው ጊዜ አዲስ የታሪክ እጥፋት የምናስመዘግብበት እንዲሆን አቅም የፈጠረ ነው።
በቬየትናም የቆይታ ምዕራፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የታደሙበት “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የቬየትናሙ የፒ4ጂ ጉባኤ፣ ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ትልቅ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች የታዩበት መሆኑ ታይቷል።
የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።
ጉባኤው ለ2027 ለሀገራችን ሌላ እድል አምጥቶና የመሪያችንንና ህዝባችንን ክብር ባረጋገጠ አኳሃን ኢትዮጵያ 5ኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንድታካሂድ ችቦ አረካክቧል። በመሆኑም ሀገራችን እንደ ቬየትናም በሌላ ምዕራፍ ልምድና ተሞክሮዋን፣ በብዝሃ እምርታና ስኬት ይዛ እንድትቀርብ ለማድረግ ርብርባችንን ከወዲሁ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል።
አሚኮ