ኤርትራ ባለስልጣኖቿን ወደ ሩሲያ ልካ የጦር መሳሪያ ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ እንደተደረገ ከተሰማ በሁዋላ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጀቶችን ከሩሲያ መረከብ መጀመሯ ተገለጸ። ለተቋሙ ቅርብ የሆኑ ዝርዝር ሳያቀርቡ እንደገለጹት ጀቶቹ ኢትዮጵያን በአየር ኃይል አቅሟ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጥ ነው።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል እየተረከባቸው ያለው የጦር ጀቶች የአምስተኛ ትውልድ ምርት እንደሆነ የሚነገርላቸውን የሱክሆይ-30 (Sukhoi Su-30) ናቸው።
“በተመሳሳይ ለጊዜው ስሙን ከማንገልጸው የአውሮጳ ሀገር AI ቴክኖሎጀ የታጠቁ የረቀቁ ሰው-አልባ በራሪዎችን በመረከብ ወደ ሃይል ስምሪት ገብቷል” ሲሉ መረጃው ያላቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ድሮን አምራች ተቋም የሆነው Sky Win Aeronautics Industries Inc. ከአራት የአፍሪካ ሃገራት የፍላጎት መልዕክት እየደረሰለት መሆኑ ተሰምቷል። የኢትዮሪቪው ታማኝ የመረጃ አቀባይ እንዳሉት ሁለት የአፍሪካ አገራት ግዢውን ለመፈጸም ስምምነት ደርሰዋል። ሌሎችም አገራት ጥያቄ እያቀረቡ ነው። የመረጃው ሰዎች የአገራቱን ስም ለመግለጽ አልፈለጉም።
የኢትዮጵያ መንግስት ራሱን በዘመናዊ ደረጃ እያበቃ ያለው ለመዋጋት ሳይሆን ውጊያን ለማስቀረት፣ ድንገት ጦርነት ከተከፈተብንም በአጭር ጊዜና ኪሳራ ድልን ለመቀዳጀት እንደሆነ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ይህ ዜና ከመሰማቱ ቀደም ሲል የኤርትራ ወታደራዊ ልዑክ የሩሲያ ማቅናቱ ተገልጾ ነበር። በቆይታቸው “ኢትዮጵያ የባህር በር ይገባኛል በማለት ወረራ ልትከፍትብን ስለሆነ የጦር መሳሪያ በግዥና በብድር ስጡን፤ ታርቱስ የሚገኘውን የሶሪያ ወታደራዊ ጣቢያን የምትዘጉ ከሆነ በቀይ ባህር ላይ ወሳኝ Strategic ጠቀሜታ ያለውን የአሰብ ወደብን ለፈለጋችሁት ጊዜ ያለምንም ክፍያ ለመፍቀድ ዝግጁ ነን…” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን የድህንነት ምንጮችን የጠቀሱ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች አስታውቀው ነበር።
የራሽያ መንግስት በተለይም የራሽያ ወታደራዊ ኢንዱስትሪ (Russia’s Arms Industry) ዋና አዛዥ “በአሁኑ ወቅት ሩሲያ በሽያጭ፣ በብድርም ሆነ በእርዳታ ለሌሎች ሃገራት የጦር መሳሪያ የማቅረብ አቅም እንደሌላት፣ ይልቁንም ሙሉ ትከረቷ ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ጦርነት በድል ማጠናቀቅ መሆኑን አስገንዝበው ሩሲያ የኢትዮጵያ መንግስት የይገባኛል ጥያቄ እያቀረበበት በሚገኝበት የአሰብ ወደብ ላይ የጦር ሰፈር የመገንባት ፍላጎት እንደሌለው ማስገንዘባቸውን እነዚሁ የዜና አውታሮች አመልክተው ነበር።
የሩሲያ ፌድሬሽን የዓለም አቀፍ ትብብር እና የውጭ ግንኙነት ሃላፊ የኤርትራን ወታደራዊ ልኡክ በቢሮአቸው ተቀብለው ያጋገሩ ሲሆን ሩሲያ የቀይ ባህር ወደብ በሆነችው የሱዳኗ ሱአኪን (Suakin) ወታደራዊ ጣቢያ ለመመስረት ከሱዳን መንግስት ጋር ሥምምነት ፈርመው በግንባታ ላይ መሆኗን አስገንዝበው ኤርትራ ከጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ያላትን ልዩነት የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ በንግግር እንድትፈታ የሃገራቸው ፍላጎት መሆኑን በማስገንዘብ ከኢትዮጵያ ባህር ሃይል ጋር በቅንጅት ለመስራት ወታደራዊ ስምምነት መደረሱን ጨምረው አብራርተውላቸዋል። ሩሲያ ሁለቱን ሃገራት አቀራርቦ ለማነጋገር ዝግጁ ስለመሆኗም በአጽንኦት ሰጥተው ምክር መለገሳቸውንም እነዚሁ ወገኖች አመልክተዋል።
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter