በተደጋጋሚ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ኤርትራ አገር እንድትሆነ የተወሰነበት አግባብና የውሳኔው አፈጻጸም በህግና በሕዝብ ዕውቅና በሌለው አስገንታይ ቡድን አማካይነት የተድረገ በመሆኑ ዳግም ሊጤንና ከኢትዮጵያ ጥቅም አንጻር ሊጤን እንደሚገባው ሲያሳስቡ ነበር። ዛሬ አብን ባወጣው መግለጫ ይህንኑ ጠቅሶ ጉዳዩ እንዲጤን ጠይቋል።
አብን ውቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ ገምግሞ ባወጣው ሰፊ መግለጫ ” ትላንት ኢትዮጵያ በተዳከመችበት ዘመን ሻዕቢያና ወያኔ መሩ የጣምራ መንግስታት የፖለቲካ መድረኩን በተቆጣጠሩበት ዘመን በተናጥል ስምምነት እና በሁለትዮሽ መመሳጠር በሽግግር መንግስት ወቅት የተገንጣይነት አጀንዳውን የኢትዮጵያ ህዝብ ባልተሳተፈበት በቀላሉ እንዲያሳካ ተደርጓል” ሲል አስታውቋል።
“… አብን ኤርትራ የሚባለው ሐገር የተመሰረተበት ታሪካዊ ሂደት ቅቡልነት ላይ ጥያቄ ያለው ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ሐገራችን ታሪካዊ ይዞታዋ ከሆነው የባህር በር የተገፋችበት የሸፍጥ አካሄድ እንደገና ይፋና ቀዳሚ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲያዝና ቁርጠኛ ትግልም እንዲደረግበት ይጠይቃል” ሲል በመግለጫው ተይቋል። አብሁን ላይ የአማራ ህዝብ ላይ ሊረሳ የማይችል ግፍና ወንጀል የፈጸመው ትህነግን በማገልገል፣ ከሻዕቢያ ጋር በመሆን የአማራ ክልልን ለማውደም በተጀመረው እንቅስቅሴ ውስጥ እጃቸውን የከተቱ ሁሉ እንዲታቀቡ ታሪካዊ ጥሪ አቅርቧል።
ትህነግ ወልቃይት ጠገዴን ዳግም በመውረ የቀድሞውን የዘር ማጽዳት ለመድገም መዘጋጀቱን፣ መዘጋጀቱንም በራሱ አንደበት ማስታወቁን ያስታወቀው አብን ህዝብ ከወልቃይት ጠገዴ ጎን እንዲቆም ጥሪ አድርጓል። የራያን ህዝብ ነጻ የማውጣቱ ስራ በመነግስት ዕገዛ እንዲደረግ አመልክቷል። ሙሉ መግለጫውን ያንቡ።
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ፤
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ክልላዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በቅርቡ ባካሄደው 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የተዋቀረው የብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ክልላዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አቋም የወሰደ ሲሆን ጉባኤውን ተከትሎም እንደ አዲስ መታገል ያለበትን የትግል ነጥቦች ነቅሶ ተወያይቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን የተራዘመ ግጭት የገመገመ ሲሆን የአማራን ህዝብ ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ለመክተት ግጭት እየጠመቁ ያሉ እና የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲዘነጉ የሚያደርጉ ኃይሎችን አሰላለፍ በመለየት አቋም ላይ ደርሷል።
ሁለት አመት ያስቆጠረው የአማራ ክልል የጸጥታ መታወክ ያስከተለው መጠነ ሰፊ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ፤ የህዝባችን መሰረታዊ ጠላቶች የሆኑ ውጫዊ ሀይሎች ጭምር ግጭቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተዋናይ እየሆኑ መምጣታቸው አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ በክልሉ በቀጠለው ግጭት በተኩስ ልውውጥ አያሌ ንጹሀኖች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ቆስለዋል፣ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣ ፖለቲካ ውስጥ የሌሉ መምህራኖችና ተማሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተረሽነዋል፣ የባለሀብቶችና የታዋቂ ሰዎች ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል፣ ህዝቡ በተራዘመ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ገብቷል፡፡ በዚህም የተነሳ የአማራ ህዝብ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገም የነቃ ተተኪ ትውልድ እንዳይኖረው እና ከአሁኑ የማህበረ-ኢኮኖሚ ፈተና ይልቅ የነገው እየከፋ አንዲመጣ በጠላቶቹና ተላላኪዎቹ በስፋት እየተሰራበት ይገኛል። በዋናነት የአማራ ልጆች በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ-ምግባር ታንጸው ተወዳዳሪ እና ሐገር ተረካቢ እንዳይሆኑ እየተደረገም ይገኛል።
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ በመሆናቸው የተነሳ ህጻናት ልጆች ያለ እድሜ ጋብቻ ውስጥ እየገቡ እንደሆነ እና የህጻናት መደፈር ስለመበራከቱ መረጃወች እየደረሱን ይገኛሉ፡፡ ግጭቱ የጤና መሰረተ ልማቶችና በጤና አገልግሎት ላይ ሰፊ አደጋ በመጋረጡ በህክምና እጦት ህዝብችን ለሞትና ለማይድን ህመም እየተዳረገ ይገኛል፣ ህጻናት የወቅት ክትባት እያለፈባቸው ይገኛል ወዘተ። በኢኮኖሚው ረገድ ሲታይ አቅም ያላቸው የክልሉ ባለሀብቶች ተሰደዋል፣ የሸቀጥ ዝውውር በከፍተኛ ሁኔታ በመስተጓጎሉ የኑሮ ውድነት ተባብሷል፣ በርካታ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ የአማራ ክልልን ኢንቨስትመንት የመሳብ እምቅ አቅም እና የቱሪዝም መዳከም ኢኮኖሚውን በመጎተቱ የህዝቡ የመልማት እድል እየተነጠቀ ይገኛልም፡፡ ይህም የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የሚደረገውን የሰላማዊ ትግል አማራጭ አንዲደበዝዝ እያደረገ ሲገኝ ህዝባችንም ለአጠቃላይ የጸጥታ ስጋት ተዳርጎ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ይህንን ለመጭው ዘመን ጭምር የሚተርፍ ዳፋ ያለው ተግባር በማያሻማ ሁኔታ እያወገዝን ሁሉም የሚመለከተው አካል ይህ አይነትና መሰል ድርጊቶች በአፋጣኝ እንዲታረሙ እንዲታገል እና ህዝባችንን ለመታደግ እንደ አዲስ ለጀመርነው እንቅስቃሴ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ እናሳስባለን። እንዲሁም በውጊያ ቀጠና እና በከበባ (Hostage) ውስጥ የሚገኘው ህዝባችን ለከፍተኛ ሁለንተናዊ ጉዳት የተዳረገ ሲሆን ሁሉም ኃይሎች የንጹሀንን ከለላ በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ በጥብቅ እያሳሰብን ችግሩ በውይይትና የሰላምን አማራጭ በማስቀደም እንዲፈታ አበክረን እንመክራለን።
አብን የሀገራዊ ምክክሩ ስትራቴጂካዊ የጋራ መፍትሄ የምናፈልቅበት አንዲሆን ይመኛል፡፡ በመሆኑም የብሄራዊ ምክክር ጉዳይ በብዙ ውትወታ እና የፖለቲካ ትግል የተገኘ ሀገራዊ መድረክ መሆኑ ታውቆ ህዝባችንን እንወክላለን የሚሉ ኃይሎች ሁሉ በሂደቱ ላይ በንቃት በመሳተፍ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አደራ እያልን ይህንኑም በንቃት የምንከታተል መሆኑን አያይዘን እንገልጻለን።
በሌላ በኩል የአብን ስራ እሰፈጻሚ ኮሚቴ የአማራ ክልልን የወያኔ የጥፋት ድግስ የጨዋታ ሜዳ ለማድረግ ከዚህም ከዛም የተጣቀሱ ያልተቀደሱ ጋብቻዎች መፈጸማቸውንና የሚደረጉ የጦርነት ቅስቃሳና ፕሮፓጋንዳወችን በተመለከተ ጥልቅ ግምገማ አድርጓል፡፡ ወያኔ የፖለቲካ ትርክት፣ አደረጃጀት እና የህግ ማዕቀፍ ዘርግቶ፣ ተቋማት አቋቁሞ በአማራ ህዝብ ላይ ስርዓታዊ ግፍ ሲፈጽም የኖረ ድርጅት መሆኑ የሚታወቅ የቅርብ ዘመን ታሪካዊ ሀቅ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ የአማራ ህዝብ ጠላት በቅርቡ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁምራን አስመልክቶ ያንጸባረቀው የወራራ አቋም የህዝባችንን አንጻራዊ ነጻነት በኃይል የመንጠቅ እኩይ አላማን ያነገበ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በመሆኑም በተጠቀሰው አካባቢ ባለው የአማራ ህዝብ ላይ ዳግም ሊፈጽም ያለመውን የዘር ማጽዳት፣ የዘር ማጥፋትና በ2013 ዓ.ም ጥቅምት 30 ማይካድራ ላይ የተፈጸመን የጦር ወንጀል ዳግም የማስቀጠል አላማ እንዲያቆም አበክረን እንገልፃለን። ወልቃይትን አስመልክቶ የወያኔ ትንኮሳና የጦርነት ቅስቀሳ ከሰብአዊነት ጉዳይና ከሀገራዊ ሰላምና ጸጥታ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ የሚከተለውን ጥሪ ለሚመለከታቸው አካላት አናቀርባለን፡፡
1. የፌደራሉ መንግስት እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ህዝብ ያገኘው አንጻራዊ ነጻነት፣ ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት እንዲጸና እና አካባቢው የህወሃት የጦርነት አጀንዳ ሰለባ አንዳይሆን ከሰላም ወዳዱ ከወልቃይት ህዝብ ጎን አንዲሆን አበክረን አንጠይቃለን፡፡
2. በራያ አካባቢወች በህዝብ ትግል የተገኘውን ድል ማጽናት ያልቻለው መንግስት በፈጠረው ክፍተት የወያኔ ሀይሎች ዛሬም ድረስ ህዝባችንን በተራዘመ መከራ ውስጥ ያስገቡት ቢሆንም ህዝባችን ዕለት በዕለት መስዋዕትነት እየከፈለ ለነጻነቱ መረጋገጥ የሚያደርገውን መዋደቅ መንግስት እውቅና እንዲሰጠውና ለወያኔ የተጋለጠውን ህዝባችንን ህልውና እንዲያስጠብቅ በጽኑ እናሳስባለን።
3. የአማራና የትግራይ ህዝቦች የረጅም ዘመናት ታሪካዊና ባህላዊ ቁርኝት ያላቸው መሆናቸው የማይሻር ሀቅ ሲሆን፤ በወያኔ ሃይል የተሳሳተ ትርክት ምክንያት የተፈጠረውን ነውረኛ ማህበራዊ አጥር (wall of shame) በጋራ ትግልና በትብብር ለዘለቄታው ማፍረስ እጅጉን ያስፈልጋል። እስካሁን የተፈጠሩ ቅራኔዎች በሰላማዊ መንገድ በሀቀኛ ውይይትና ድርድር እልባት እንዲያገኙ፤ የትግራይ ህዝብ ከወያኔ የ50 ዓመታት የነጣይ ትርክትና የአፈና ቀንበር መንጭቆ ነጻነቱን ለማወጅና አዲስ መስመር ለማስቀመጥ የሚያደርገውን የከበረ የትግል ጅማሮ እውቅና እየሰጠን ይገደናል ከሚሉ ሰላማዊ የትግራይ ሀይሎች ጋር ተቀራርበን የምንሰራ መሆኑን እንገልጻለን።
አብን ከአማራ ህዝብና ከቀጣናዊ የሰላም መረጋገጥ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም አንጻር በሻዕቢያ አሁናዊና የትላንትና ዘመን ሁኔታ ላይ ሰፊ ግምገማ አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ሻዕቢያ ከፍጥረቱ ጀምሮ ከአማራ ህዝብ ብሎም ከኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ ህልውና አንጻር በበጎ ሊመዘገብለት የሚያስችል ታሪክ የሌለው ኃይል መሆኑ ይታወቃል። አሁን ላይም በአማራ ክልል እንዲሁም በኦሮምያ ክልል አንዳንድ አካባቢወች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር ለማባባስ ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር የአጋርነት ዝንባሌ እንዳለው መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተቀጽላ በመሆን በሀገራችን ብሄራዊ ጥቅም ላይ ጉዳት ለመጣል ያለመታከት የሚሰራ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አጥብቆ ሊያወግዘውና ሊታገለው ይገባል:።
ትላንት ኢትዮጵያ በተዳከመችበት ዘመን ሻዕቢያና ወያኔ መሩ የጣምራ መንግስታት የፖለቲካ መድረኩን በተቆጣጠሩበት ዘመን በተናጥል ስምምነት እና በሁለትዮሽ መመሳጠር በሽግግር መንግስት ወቅት የተገንጣይነት አጀንዳውን የኢትዮጵያ ህዝብ ባልተሳተፈበት በቀላሉ እንዲያሳካ ተደርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ፓርቲያችን አብን ኤርትራ የሚባለው ሐገር የተመሰረተበት ታሪካዊ ሂደት ቅቡልነት ላይ ጥያቄ ያለው ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ ሐገራችን ታሪካዊ ይዞታዋ ከሆነው የባህር በር የተገፋችበት የሸፍጥ አካሄድ እንደገና ይፋና ቀዳሚ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲያዝና ቁርጠኛ ትግልም እንዲደረግበት ይጠይቃል።
በአጠቃላይ ግምገማም ሻዕቢያ የኢትዮጵያ እና የቀጠናው መልክዓ-ፖለቲካ (geopolitics) ጉዳዮች ከሰላማዊ ውይይትና ድርድር ይልቅ በግጭትና በጦርነት ብቻ መፈታት አለባቸው የሚል ሃላፊነት የጎደለውና አውዳሚ የሆነ ባህል እንዲንሰራፋ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት መቆየቱ፣ ኤርትራም ሀገር ከሆነች በኋላም ቢሆን ይሄን አመለካከት በፊታውራሪነት የሚያራምድ ሀይል መሆኑ፣ ባጠቃላይም በህዝቦችና በሀገራቱ መካከል ከፍትሃዊ አማካኝና ከትብብር ይልቅ ተናጥላዊ ጥቅምን በሴራ እና በሃይል የማስፈፀም እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ በዛው የቀረ ሃይል መሆኑ አለም ያወቀው ሀቅ ሆኗል።
በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ግጭት በተመለከተ አሁንም አጽንኦት ልንሰጠው የምንወደው ጉዳይ ከታሪክ፣ ከፖለቲካና ከሞራል ፍልስፍና አኳያ፣ እንዲሁም አሁን ካለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር፣ “ጦርነት የችግሮች መፍቻ ብቸኛው መንገድ ነው” የሚለው ሃሳብ የተሳሳተ መሆኑን አስምረን እንገልጻለን። ይህንንም ከታሪካዊ እውነታዎች አንጻር ከተመለከትን ሻዕቢያ ከ1953 – 1983 ዓ.ም ለ30 ዓመታት ያካሄደው ጦርነት ለምስኪን የኤርትራ ህዝቦች አምጥቶታል የሚባለው ነጻነት በተጨባጭ ሚዛን ሲለካ ህዝቦችን ለሰፊ አፈና ከመዳረጉ በቀር ዛሬም ለነጻነታቸው የሚታገሉ ነጻነት የተነፈጉ ህዝቦች መሆናቸው ግልጽ ነው። “ነጻነት” ተብሎ ከበሮ የሚደለቅለትም ታሪካዊ ክስተት የሻዕቢያንና የጥቂት ግለሰቦችን አምባገነናዊ አገዛዝ ከማፅናት ባለፈ ቅንጣት አዎንታዊ ፋይዳ እንዳሌለው፣ ይባስ ብሎም ተጨማሪ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና የሰዎችን ፍልሰት ያስከተለ መሆኑ የሚታወቅ ሀቅ ነው። ሌላው ታሪካዊ እውነታ በደቡብ ሱዳን የምናየው ሲሆን በጦርነት የተገኘው ነፃነት ከ10 አመት በላይ የዘለቀ የእርስበርስ ውጊያ ማስከተሉ እና ከ400,000 በላይ ሰዎችን ለሞት የዳረገ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።
አብን ኢትዮጵያ ከጦርነት አዙሪት ወጥታ ወደ ሰላም ማድረግ ስለሚገባት ሽግግር ላይ መክሯል፡፡ ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ታሪኮች እንደሚስረዱት የብሄር ይዘት ያላቸው ግጭቶችና ጦርነቶች በማህበረሰቦች ግንኙነት ላይ አሉታዊ ጠባሳ ጥሎ ስለሚያልፍ በቀጣይ አብሮነት ላይ ተግዳሮችን የሚፈጥር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በህወሀትና ኦነግ ጥምረት በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጂም ዘመን የቆየው የግጭት አዙሪት አስተማሪ ተሞክሮ የሚሆን ነው፡፡ በሚሊዬን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ከመሆኑም በላይ ባጠቃላይ የነበረው ዑደት የሚያስገነዝበው የግጭትና የጦርነት አማራጭ መቋጫ እንደማይኖረው ሲሆን መንግስትን ጨምሮ ሁሉም አካል ይህንን በማጤን ሀገራችንና ህዝባችን በዘላቂ እፎይታ ውስጥ እንዲገባ የልተሄደበትን መንገድ ሁሉ አሟጦ መጓዝ ያስፈልገናል።
እንደሚታወቀው በተለይ የርስበርስ ጦርነት አሸናፊም ተሸናፊ የሌለውና አጠቃላይ ድል ሊያጸና የማይችል፤ ይልቁንም ተጨማሪ ሞት እና ውድመት ከማስከተሉም በላይ ዘላቂ ቅራኔ የሚፈጥር መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ረገድ የቅርቡን ህወሀት የጫረው ሁለት ዙር ጦርነት በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልል ህዝቦች ያስከተለው መጠነ ሰፊ ሰብአዊ፣ ስልቦናዊና ቁሳዊ ቀውስ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡ “የሰላማዊ ትግል አይሰራም” በሚል አንዳንዶች የሚያራምዱት ሃሳብ ትክክል እንዳልሆነ በ2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ህዝቦች የተደረገው ሰላማዊ ትግል የስርዓት ለውጥ ማምጣቱ በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችል ሲሆን ሂደቱም በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የተሻለ መቀራረብንና የአንድነት መንፈስን የፈጠረ ነበር፡፡ ስለሆነም ከግጭትና ከጦርነት አዙሪት ለመውጣትና በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሀገራዊ ውይይት ሂደቶች ጤናማነት፣ የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ማህበረሰባዊ የጋራ እሴቶችን ማጎልበትና መጠቀም፣ እና የኢኮኖሚ እድሎችን መፍጠርና ማስፋት አንደሚያስፈልግ አብን ያምናል፡፡
የጦርነት አማራጮች በሂደትም ይሁን በመጨረሻ የግለሰቦችና የጠባብ ቡድኖች ጥቅም ማስፈፀሚያ የመሆን እድላቸው ሰፊ ሲሆን ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የስልጣን ሽኩቻ መድረክ መሆናቸው አንደማይቀር፣ ይሄን እውነታ በኤርትራ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ከነበሩትና አሁንም ካሉት ሁኔታዎች በቀላሉ መገንዘብ እንደሚቻል አብን ሁሉንም ወገን እያስታወሰ “ጦርነት ክብር ይሰጣል” ለሚሉ አካላትም መልሱ “ጦርነት ክብር አይሰጥም፣ ጦርነት የሚያስከትለው ተጨማሪ ሞት እና ውድመት ብቻ መሆኑ”፣ በዚህም ረገድ ህወሀት የጫረው ሁለት ዙር ጦርነት ሁለንተናዊ ውድመት እንጂ ሰላምን አንድነት እና ክብርን አላመጣም። ስለሆነም ሁልጊዜም ቢሆን የሰላም አማራጮችን በመከተል የግጭትና ጦርነት አዙሪትን መስበር እንደሚገባ አብን ሁሉንም ሀይሎች በአጽንኦት ማሳሰብ ይወዳል።
በተለይ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ከሌሎች የማህበረ ኢኮኖሚ መስኮች ጋር አመጋግቦ በመስራት የሁላችንም አጀንዳ የሆነውን የህዝብን ሰላም መመለስ የሚቻልበት እድል አለ ብለን እናምናለን፡፡ የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣ የህግ የበይነትን የማስፈን ስምሪቶች በህዝብ አመኔታና ተሳትፎ የታጀቡ በማድረግ፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራዎችን በሰላማዊ ኮሚዩኒኬሽን ማገዝና እና ይህን ክንውን ከማህበረ-ኢኮኖሚ መርሃግብሮች ጋር ማስተሳስር አንዱና ዋናው የሰላም መንገድ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በማህበረ-ኢኮኖሚው ዘርፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪኮችና የጋራ እሴቶች ለሰምና ለሀገራዊ አንድነት መጠቀም፤ በግጭት ወይም በጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላትን መቀነስ የሚያስችል የኢኮኖሚ አማራጮችን ቀርጾ መተግበርና ማስፋት ብሎም የስራ እድሎችን መፍጠርን የሚመለከት ሲሆን መንግስት እና መሰል አካላት በነዚህ ቁልፍ ተግባራት ላይ አበክረው አንዲሰሩ አብን ጥሪ ያቀርባል፡፡
በመጨረሻም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፓርቲው በቅርቡ ያካሄደው ደማቅ 3ኛ ጉባኤ የተመራበትን አካሄድና ዲሲፕሊን፣ የፈጠረውን ሰላማዊ መድረክ፣ እና የተሰጠውን ቁርጠኛ አመራር ያደነቀ ሲሆን ፓርቲው ራሱን ከውስጥ የትግል ጎታቾችና የሌላ አጀንዳ ተሸካሚወች ያጸዳበትን ሂደት “ታሪካዊና ቆራጥ” እርምጃ ሲል አውስቶታል። ጉባኤው በአባላትና ደጋፊወቻችን ዘንድ የፈጠረውን የታደሰ ተስፋና የትግል ቁርጠኝነት በማድነቅም ይህ ሁኔታ ለቁርጠኛ ትግል ስንቅ እንደሚሆነው ገምግሟል።
ብሄራዊ አስፈጻሚ ኮሚቴውም ከወቅታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ የፖርቲውን መዋቅሮች እና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል። በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ተቀራርቦ በመወያየት፣ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ ለማስቻል በቀረበው እቅድ ዙሪያ በሰፊው ተወያይቶ አጽድቋል። በመጨረሻም ጠንካራ ሀገር እንዲገነባ፤ የአማራ ህዝብም ከገባበት ውስብስብ ችግር እንዲወጣ ራሱን መልሶ የማይናወጥ የልማትና የሰላም አለኝታ እንዲሆን ለማስቻል በምናደርገው የትግል ሂደት ይገደናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ ድጋፋቸውን እንዲሰጡን በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ እያቀረብን በተለይ መንግስት ዋና ባለድርሻ እንደመሆኑ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ያልተሄደበትን የሰላም አማራጭ መንገድ ሁሉ በመፈተሽና በመቀየስ፤ የህዝባችን ሰላም እንዲመለስ በጽኑ እንዲሰራና ሰላምንም እንዲያረጋግጥ ስንል እናሳውቃለን።
ሚያዝያ 19/2017 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter