ትግራይን ከሃምሳ ዓመት በሁዋላ ከነጻ አውጪ ፓርቲ የሚመነጭቅ ፓርቲ ተመሰረተ። በትግራይ ያሉት ድርጅቶች በሙሉ ከትህነግ ምን የዓላማና የአስተሳሰብ ልዩነት እንዳላቸው በግልጽ ባይታወቅም ስማቸው በሙሉ “ነጻ አውጪ” አርማ የያዘ ነው። ዛሬ መወለዱ የተነገረለት አዲስ ፓርቲ ግን የሊብራል እሳቤ ያለው። አብዮታዊ ዴሞክራሲን ያራገፈ ስለመሆኑ መረጃውን የሰጡ አመልክተዋል።
ዜናው የትህነግ ፍጻሜ መዳረሱን የሚያሳይ መስሏል። በትግራይ የተወለደው አዲስ ፓርቲ በምሁራን የተዋቀረ ሲሆን መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ሰፊ ቁጥር ያላቸው ከወዲሁ ፓርቲውን እያጀቡት ነው። ልምድ፣ ዕውቀትና በቂ የግንኙነት መሰረት ያላቸው የፓርቲው መስራቾች ትህነግን በሚጠላው የዴሞክራሲ አግባብ አሸኛኘት እንደሚያደርጉለት ከወዲሁ እየተነገረ ነው።
እነ ዶክተር ደብረጽዮን ምርጫ ቦርድ የሚሰርዛቸው ከሆነ አገር እንደሚተራመስ ባስታወቁና ባስጠነቀቁ ማግስት መወለዱን ይፋ የተደረገው አዲሱ ፓርቲ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባለው ዳፍንታም አስተሳሰብ ከትግራይ ምድር ይጠርገዋል እየተባለ ነው።
እነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩት ትህነግ የክልሉን ጊዚያዊ አስተዳደር በኃይል ማፍረሱን ተከትሎ ለሰራዊቱ የሚከዱ በርካታ ታጣቂዎችን መልሰው እያደራጁ መሆናቸውን አቶ ጌታቸው ረዳ በሚመሩት ካቢኔ ውስጥ አባል የሆኑ መናገራቸውን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።
እነዚሁ ወገኖች “ትህነግ እንዳይሰረዝ አንድ ላይ ጉባኤ እናካሂድ” በማለት ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ማጣታቸውን አስታውቀው ነበር። በመሆኑም ለትህነግ ምርጫ ቦርድ የሰጠው የጊዜ ገደቡ ሊጠናቀቅ በቋፍ ላይ ባለበት ወቅት ነው አዲስ ፓርቲ ማቋቋማቸውን ይፋ ያደረጉት።
ፓርቲው ይፋ ከመደረጉ በፊት ወይዘሮ ኬሪያ “በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ሞጋች ማኅበረሰብ ተፈጥሯል፤ ወንበሩን ብረት ምጣድ የሚያደርግ ትውልድ ተፈጥሯል” ካሉ በሁዋላ፣ ይህን ለውጥ ፈላጊ ትውልድ መምራትና ማደራጀት አግባብ መሆኑን አመልክተው ነበር። ይህ ጥቆማቸው አቶ ጌታቸው በትግራይ ለውጥ የሚያቀጣጥሉ ኃይሎች ተፈጥረዋል ከማለታቸው ጋር የሚስማማ መሆኑን ጠቁመን አስተያየታቸው ፓርቲ እንደሚመሰረት አመላካች መሆኑን አመላክተን ነበር።
” ከብልጽግና ጋር ልክ እንደሌሎቹ በአገር ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ተባብሮ ለመሥራት ይችላል እንጂ የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ገለልተኛ እና ነጻ ፓርቲ ነው ” በማለት ስለአዲሱ ትሊዴፓ / ትግራይ ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከመስራቾቹ መካከል ለቢቢሲ አስታውቀዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ከትህነግ የተከፈለው ቡድን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም በሂደት ላይ መሆኑን ከአመራሮቹ መካከል አንዱ ለቢቢሲ ሲገልጹ “የፖለቲካ ፓርቲው በሊብራል ዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ የሚመራ ነው” ብለዋል። ይህ አነጋገራቸው ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በኮሙኒዝም አስተሳሰብ ተቸንክሮ በትግራይና በመላው ኢትዮጵያ የተዘረጋው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚባል ርዕዮት ግብአተ መሬትን ያበሰረ ሆኗል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ለርዕዮት እንዳሉት ትህነግ ከተከመረው ጥፋቱ በላይ ሻዕቢያ ጉያ ስር ተመልሶ መለጠፉ ፖለቲካዊ ኪሳራ አጎናጽፎታል። በትግራይ ሕዝብ እንዲተፋ ምክንያት ሆኗል። ድሮም በቋፍ ነበር አሁን አክትሞለታል ብለዋል።
” የፓርቲው ሕገ ደንብ እና ፕሮግራሞቻችን አርቅቀን ጨርሰናል። ” አሁን ላይ የደጋፊዎችን ፊርማ በማሰባሰብ ላይ እንገኛለን። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች ገና ስላልተሟሉ እስካሁን ድረስ ለቦርዱ በይፋ የቀረበ ጥያቄ የለም ” ሲሉም መስራቾቹ ከተናገሩት ለመረዳት ተችሏል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቡድኑ ለምዝገባ እየሄደበት ያለውን ሂደት እንደሚያውቅ ተመልክቷል። ፓርቲው ክልላዊ ፓርቲ ነው። ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በግንቦት የመጀመሪያ ወር ላይ ቅድመ እውቅና ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የምዝገባ ሂደቱን ካጠናቀቁ በሁዋላ የውስጥ ስራቸውን በመስራት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአንድ ዓመት ጊዜ ካበቃ በኋላ ክልላዊ መንግሥትን ለመመሥረት በሚደረገው ምርጫ እንደሚሳተፉም ተመልክቷል።
ፓርቲው ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እውቅና ካገኘን በኋላ ከባለሀብቶች ጀምሮ የቀን ሠራተኞች ድረስ በአባልነት እና በአመራርነት ተቀላቅለው እንዲሳተፉበት እንደሚደረግ ተሰምቷል።
” ትግራይ ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከብልጽግና ጋር ልክ እንደሌሎቹ በአገር ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ተባብሮ ለመሥራት ይችላል እንጂ የሚያገናኘው ነገር የለም፤ ገለልተኛ እና ነጻ ፓርቲ ነው። ” ሲሉም አስታውቀዋል።
የትግራይ ሊብራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ እየመሠረቱ ካሉተ አንጋፋ ሰዎች መካከል የቀድሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የትህነግ ፖሊት ቢሮ አባል የነበሩት እና የትዕምት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በየነ መክሩ፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት ይገኙበታል። ፕሮፌሰር ክንደያ በቅርቡ በጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አማካሪ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።
በሁለት ተከፍሎ እርስ በእርሱ ሲካሰስ የቆየው ትህነግ የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ ጉባዔ ማካሄድ ባለመቻሉ ከፓርቲነት ሊሰረዝ እንደሚችል ቦርዱ ማስታወቁ ይታወሳል።
የመሰረዝ አደጋ የገጠመው በደብረፂዮን (ዶ/ር) የሚመራው ትህነግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተደራድሮ የፕሪቶሪያ ስምምነትን እንደፈረመ ድርጅት እንደ አዲስ በቦርዱ መመዝገቡ ተገቢ አለመሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።
የህወሓት መሰረዝ ስጋት የፈጠረባቸው በአቶ ጌታቸው የሚመራው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከሳምንታት በፊት ባወጡት መግለጫ በደብረፂዮን (ዶ/ር) ለሚመራው ቡድን በጋራ ጉባዔ ለማካሄድ ጥሪ አቅርበው የነበረ ቢሆንም በጎ ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter