ቋሚ ሲኖዶስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከቤተክርስቲያናችን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውጪ በፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማኅበር አዳራሽ የሰጡትን ትምህርትና በማኅበሩ ሚዲያ የተላለፈበትን ሁኔታ በተመለከተ በዛሬው መደበኛ ጉባኤው በሰፊው ተወያይቶ ለመወሰን በያዘው ቀጠሮ መሰረት በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
1 – ፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማህበር በተለያዩ ጊዜያት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጪ በሚዲያው ያስተላለፈው የስሕተት ትምህርት የቤተክርስቲያናችንን አባቶች፣ሊቃውንቱንና መላው ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘነ በመሆኑ በማህበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ በኩል ጊዜያዊ የእገዳ ደብዳቤ እንዲደርሰው እና በመምሪያው በኩል አስፈላጊው ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ሆኖ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ይቻል ዘንድ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲቋቋም አድርጓል።
በዚህም መሰረት ቋማ ሲኖዶስ ያቋቋማቸው አጣሪ ልዑካን አጠቃላይ የማህበሩን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እና በሚዲያው ያስተላለፋቸውን የስህተት ትምህርቶች በተመለከተ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ከማህበራት ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ክትትል መምሪያ ጋር በመነጋገር በሚገባ መርምርውና አጣርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውሳኔ ሐሳብ ጋር ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲያቀርቡ፣
2, ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “ማርያም ቤዛዊተ ዓለም” አትባልም በማለት ከቤተ ክርስቲያናችን የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውጪ የሰጡት ሕጸጽ ያለበት ትምህርት በሊቃውንት ጉባኤ በኩል በሚገባ ተመርምሮና ተጣርቶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር ለቋሚ ሲኖዶስ በአስቸኳይ እንዲቀርብ ብፁዕነታቸውም ጉዳዩ ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተአቅቦ እንዲቆዩ፣
3, ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እና ብፁዕ አቡነ በርናባስ የደቡብ ካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያስተላለፏቸው የስሕተት ትምህርቶችና በሌሎችም መምህራን የተላለፉ ነቀፋ ያለባቸው ትምህርቶች ካሉ የሊቃውንት ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ አንጻር በሚገባ መርምሮና አጣርቶ ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲያቀርብ፣
3. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኝ ብዙኃን ስርጭት ድርጅት ለፍኖተ ጽድቅ ጠቅላላ ማህበር ሚዲያ የአየር ሰዓት የሰጠበትን ዝርዝር ሁኔታና ከማኅበሩ ጋር በተያያዘ አየር ላይ ያዋላቸውን ትምህርቶች የሚያሳይ ሪፖርት እንዲያቀርብ ይደረግ በማለት ቋሚ ሲኖዶስ ወስኖ የዕለቱን ጉባኤ በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ አጠናቋል
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter