የዓለም ጤና ድርጅት ሩሲያ የጀመረችውን የካንሰር ክትባት ምርምር እና ሙከራ ውጤት በተስፋ እየጠበቀው መሆኑን በድርጅቱ የሞስኮ ጽ/ቤት ኃላፊ ባቲር ቤርድላይቼቭ ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው ክትባቶቹን ለማምረት ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፣ ግኝቱ ግን ከዋጋም በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የክትባቱ ጉዳይ ከቁስ በላይ ለሰው ልጆች ተስማሚ ቴክኖሎጂን ለማግኘት ለአሥርተ ዓመታት የተደረገ ወጤታማ ሙከራን ማሳያ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
ለዓላማው መሳካትም ለብዙ አስርት ዓመታት ሲገነባ የቆየ የምርምር ማዕከል እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አቅም እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
በዚህ ረገድ ስራውን በስኬት ለማጠናቀቅ የተሟላ አቅም ካላቸው ጥቂት የዓለም ሀገራት መካከል ሩሲያ አንዷ ናት ብለዋል ኃላፊው፡፡
ሩሲያ የካንሰር ክትባት ምርምር የጀመረችው እ.አ.አ በ2008 እንደሆነ መረጃዎች የሚያመላክቱ ሲሆን፣ ከ2021 ጀምሮ በትኩረት ሲሠራበት ቆይቶ በ2024 ሙከራ እንደተጀመረበት ተጠቁሟል፡፡
ክትባቱ የተሠራው ጋማሊያ የኤፒዲሚዮሎጂ እና ማይክሮባዮሎጂ ምርምር ኢንስቲትዩት ከብሎክሂን የካንሰር ምርምር ማዕከል እንዲሁም ከሄርዘን ሞስኮ ኦንኮሎጂ ምርምር ተቋም ጋር በመተባበር እንደሆነ የኢንዲያን ቱዴይ ዘገባ ያመላክታል።
ክትባቱ አስፈላጊውን ደረጃዎች በማለፉ በ2025 አጋማሽ በካንሰር በተያዙ ፈቃደኛ ሰዎች ላይ በሙከራ ደረጃ እንደሚጀምር በሞስኮ የሚገኘው የጋማሊያ ብሔራዊ የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አሌክሳንደር ጊንትስበርግ ከወራት በፊት ለስፑትኒክ ተናግረዋል።
ኃላፊው ጃንዋሪ 27፣ 2025 ለአርቲ እንደገለጹት ደግሞ ክትባቱ በዚሁ ዓመት ነሐሴ ድረስ መንግሥታዊ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ተሟላ አገልግሎት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፈረንጆቹ 2024 የካቲት ወር ላይ ስለጉዳዩ በሰጡት አስተያየት፤ ሩሲያ የካንሰር ክትባትን ለመስራት በእጅጉ መቃረቧን አስታውቀው ነበር፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የሞስኮ ጽ/ቤት ኃላፊ ባቲር ቤርድላይቼቭን በተስፋ አየተጠበቀ እንደሚገኝ ዛሬ ለስፑትኒክ የተናገሩለት ክትባት የሳንባ፣ የቆሽት፣ የኩላሊት ካንሰር እና ሜላኖማ ያለባቸውን ሕሙማን ለመርዳት እንደሚውል ተገልጿል።
በለሚ ታደሰ ኢቢሲ