” … ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” የሚል ምላሽ ሰጡ። ይህን ምስክርነታቸውን የሰጡት ስለተበሳጩበት ጉዳይ ሲያብራሩ ነው። ” የተበሳጨሁት ሊገድሉኝ አቅደው እንደነበር ያወቅኩኝ ጊዜ ነው” በማለት የሽግግር ጊዜ ቆይታቸውን ወደ ኋላ ተመልሰው ገልጸዋል። ዛሬ በይፋ ከሃላፊነታቸው ተሰናብተዋል።
“ኋላ ላይ” አሉ አቶ ጌታቸው ስልጣን ከተረከቡ በሁዋላ ሰምተው ስለተበሳጩበት ጉዳይ ሲናገሩ፣ “… ኋላ ላይ በደረሰኝ መረጃ መሠረት ሁለት የማከብራቸው ወታደራዊ አዛዦች ‘እንዴት አመለጠን ቀድመን ነበርእኮ ማስወገድ የነበረብን’ ብለው በቁጭት እንዳወሩ አወቅኩኝ። ለነገሩ የሚታወቅ ባህሪያቸው ነው። ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” በማለት የትህነግን አመራሮችን የመግደል ታሪክ ራሳቸው ላይ ከተሞከረው ግድያ ጋር አያይዘው ያጋለጡት።
አቶ ጌታቸው ከትናንት ” UMD ” ከሚሰኝ ሚድያ ጋር ባደረጉት ረዥም ቃለ ምልልስ ” በሁለት ዓመቱ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የስልጣን ቆይታህ ያልጠበቅከውና በጣም መጥፎ ነበር ብለህ የምትገልፀው አጋጣሚ አለ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “አዎ አዎ በጣም ያልጠበቅኩትና መጥፎ አጋጣሚ ነበር ” በማለት ከመገደላቸው በፊት እንዴት አምልጠው እንደወጡ ሲያስታውቁ፣ ግድያውን እንዲያስፈጽሙ የታዘዙትን ሰዎች በስም ጠቅሰአል።
አቶ ጌታቸው “እኔን እስከማስወገድ ድረስ ፍላጎት እንደነበራቸው አላውቅም ነበር። መጨረሻ ላይ ግን ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ወደ ኤርፖርት ሳመራ እኔን አግቶ ለማስቀረት ሙከራ አደረጉ። ለማገት መሞከራቸው አይደለም እኔን ያበሳጨኝ። እኔ የተበሳጨሁት ሊገድሉኝ አቅደው እንደነበር ያወቅኩኝ ጊዜ ላይ ነው” ሲሉ በተቀነባበረባቸው የግድያ ሙከራ በዝርዝር አስረድተዋል።
ይቀጥሉና “ኋላ ላይ በደረሰኝ መረጃ መሠረት ሁለት የማከብራቸው ወታደራዊ አዛዦች እንዴት አመለጠን ቀድመን ነበር እኮ ማስወገድ የነበረብን” በቁጭት መናገራቸውን መስማታቸውን እንደደረሱበት በዚሁ የትግርኛ ቃለ ምልልሳቸው አስታውቀዋል። ይህንኑ አቅዶ የማስወገድ ተግባር ነው ለጠያቂያቸው “… ለነገሩ የሚታወቅ ባህሪ ነው። ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ሲሉ የሚያውቁትን የትህነግን ታሪክና ገድል አስታውሰው ያለፉት። በርካታ ከትህነግ ጋር ሲሰስሩ የነበሩና የሚቃወሟቸው ሰዎች መገደላቸው፣ አንዳንዶቹም የት እንደገቡ አሁን ድረስ የማይታወቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአቶ ጌታቸው ምስክርነት መነጋገሪያ ሆኗል።
አቶ ጌታቸው በዚህ አያበቁም ” ኬላ ጥሎ እኔን ለማገት ተልዕኮ ተሰጥቶት የነበረው አወጣኸኝ የተባለ የኮር አዛዥ ነው። እንደውም ኋላ ላይ ተልዕኮውን ባለመፈፀሙ አስረውታል። እኔን ለመግደል ዝርዝር ፕላን ያወጡትን ሰዎችን ሳይቀር አውቃቸዋለሁ” በማለት ቀደም ሲል ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደነበር በጥቅል የገለጹትን ጉዳይ፣ ስም፣ ቦታ፣ ማዕረግና ኩኔታዎችን በመዘርዘር አመልክተዋል።
ከዛ በፊት በውጭ ሚዲያዎች ባደረጉት ቃለ ምልልስ እሳቸውን እንዲያስወገዱ ተልዕኮ ወሰደው መቀለ የመጡ ሃብታሞች ተይዘው እንደነበር፣ በሁዋላ ላይ በዋስ እንዲለቀቁ መደረጉንና አዲስ አበባ ሲመጡ መያዛቸውን አቶ ጌታቸው ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
በዱባይ ቆይታቸው ከቢርድ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልሳቸው ከመጀመሪያው ጀምሮ መተባበር ከባድ እንደሚሆን እውቀቱ ነበራቸው። ይህም የሚሆነው ክልሉን ከመሩት አምስት ሰዎች መካከል እሳቸው የጫካው ትግል አባል ባለመሆናቸው። በትግርኛው ቃለ ምልልሳቸው ላይ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ በብዙ ውጣ ውረድ ተቋቁሞ ፕሬዚዳንት ሆኜ መምራት ስጀምር በቀናት ውስጥ ‘ ባንዳ ‘ የሚል ስያሜ ተለጠፈብኝ ” ሲልይ የቀደመውን ስጋታቸውን ትክክለኛነት አቶ ጌታቸው ረዳ አስረድተዋል።
በርካታ ጉዳዮች ባነሱበት ቃለ መጠይቃቸው ” አሁንም ትግራይ መላ ቅጡ በማይታወቅ ሁኔታ ላይ ናት ፤ በርካታ የትግራይ ህዝብ በከፍተኛ ጭንቅና መከራ ውስጥ ይገኛል ” ሲሉ በገሃድ የሚያውቁትን ዕውነት ገልጸዋል።
” በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት ጊዚያዊ አስተዳደሩ ሲመሰረት የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ጦርነቱ በመምራት ከፍተኛ ሚና የነበረን 5 ስራ አስፈፃሚዎች ወደ ፕሬዜዳንት የኋላፊነት ቦታ እንዳንመጣ ፍላጎት ነበረቸው ” በማለት ወደ ኋላ ተመልሰው አስታውሰዋል።
ይህን ሃሳብ እሳቸው ቢቀበሉትም የተቀሩት አራቱ ስራ አስፈፃሚዎች የጠቅላይ ሚንስትሩን ሃሳብ ውድቅ ማድረጋቸው ተናግረዋል።
” ጊዚያዊ አስተዳደሩ ለማቋቋም በአላስፈላጊ ክርክር አራት ወራት ፈጅተናል፤ በብዙ ውጣ ውረድ መጋቢት 21/2015 ዓ.ም ተቋቁሞ ፕሬዜዳንት ሆኜ መምራት ስጀምር በቀናት ውስጥ ‘ ባንዳ ‘ የሚል ስያሜ ተለጠፈብኝ ” ሲሉ ተደምጠዋል።
አቶ ጌታቸው ” በዚያው ዓመት ወርሃ ግንቦት የባሰውኑ ‘ ከሃዲ ‘ ተባልኩኝ ” በማለት ተናግረዋል።
” አራቱ የህወሓት ስራ አስፈፃሚዎች በየሦስት ወሩ ለማድረግ የሚፈቅደውን የድርጅቱ ውስጠ ደንብ በመጣስ በየሦስት ቀኑ ፍሬ በሌለው ስብሰባ በመጥመድ ከመንግስታዊ ስራ ውጭ እንድሆን አበክረው ሰርተዋል ፤ በዚሁ ተማርሬ ኃላፊነቴ በራሴ ፍቃድ መልቀቅ ባለመቻሌ ተናደው እኔን ጨምሮ 16 የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላትን ‘ ከሃዲዎች ከጂዎች ‘ ብለው በመፈረጅ አላሰራ አሉን ” ብለዋል።
” የተቀረው የህወሓት የስራ አስፈፃሚ በፕሪቶሪያው የተኩስ ማቆም ስምምነት እንደ ሽንፈት የሚቆጥር ፣ በተፈናቃዮች እጣ ፈንታ የሚቆምር ፣ ጊዚያዊ አስተዳደሩ የተሰጡት ተልእኮዎች እንዳይፈፅም ከላይ እስከ ታች በእቅድ የሰራ አደናቃፊ ” ብለውታል አቶ ጌታቸው።
አቶ ጌታቸው ” ለውጥ የማይቀበሉ ፤ የተቸከሉ ” ሲሉ የገለፁዋቸው የህወሓት 4ቱ ስራ አስፈፃሚዎች እሳቸው ወደ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት በመጡበት ማግስት የሚሰራ በሌለበት 55 የድርጅቱ ሰዎች በምክትል የስራ ኃላፊ ደረጃ እንዲሾሙ ፕሮፓዛል እንዳቀረቡላቸው ፤ ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ስራ ሳይሰራ ደመወዝ የሚከፈለው አመራር ለመመደብ ቢቸገሩም ከክርክር በኋላ 35 #በግድ መመደባቸው ገልጸዋል።
ድርጅታዊ ውስጥ ደንብ በመጣስ የ65 እና የ70 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የማእከላይ ኮሚቴ አመራር እንዲሆኑ መመረጣቸው በርካታ ቁጥር ያለው አመራር ከሃላፊነት ምድብ ውጭ ሆኖም ቁጭ ብሎ በፊት የነበረው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኝ የሚያደርግ እጅግ ዘግናኝ አሰራር ክልሉን ጠልፎ መጣሉ አቶ ጌታቸው ገልፀዋል።
” ጡረታ የማይፈቀድበት ክልል ቢኖር ትግራይ ነው ” ያሉት አቶ ጌታቸው ፤ ከጦርነቱ በፊት በ2012 ዓ.ም 800 ሚሊዮን ብር የነበረው የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጊዚያዊ አስተዳደሩ ተቋቁሞ ስራው በ2015 ዓ.ም ሲጀምር ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ማሻቀቡ በክልሉ ያለው ቅጥ ያጣ በልሹ አሰራር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
” በትግራይ ያለው አሁናዊ ፓለቲካዊ ቀውስና ችግር ህወሓት ብቻውን ስልጣን እንዲቆጣጠር ያለው ያልተገራ ፍላጎት የፈጠረው ነው ” ያሉት አቶ ጌታቸው ” ይህንን ሁሉንም ነገር በብቸኝነት የመያዝ ያልተገራ የህወሓት ፍላጎት የማይሸከም በተግባር የተደገፈ ለውጥ በትግራይ መፈጠሩ ማሳያዎችን በመጥቀስ አስረድተዋል።
ከትናንት ወዲህ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም ከዱባይ ‘ bird story agency ‘ ለተባለ ሚድያ በሰጡት ቃለመጠይቅ ” በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እመለሳሎህ ማለታቸው ” ተከትሎ ትናንት ወደ አዲሰ አበባ መመለሳቸው በአንዳንድ የማህበራዊ የትስስር ገፅ ተጠቃሚዎች ቢፃፍም ፤ ፕሬዜዳንቱ ለUMD ሚድያ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ስለዚሁ ጉዳይ ያሉት የለም።
NB. አቶ ጌታቸው ረዳ አራቱ ስራ አስፈጻሚዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ ውድቅ እንዳደረጉ በገለጹበት አውድ ስም ባይጠቅሱም በይፋ የሚታወቁት ስራ አስፈጻሚዎች ፦
1. ደብረፅዮን (ዶ/ር)
2. ወ/ሮ ፈትለወርቅ
3. አቶ ኣለም ገብረዋህድ
4. አቶ ጌታቸው ኣሰፋ ናቸው።
አቶ ጌታቸው ረዳ ትህነግ በከፈታቸው ጦርነቶች ሁሉ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የጦርነቱ አፈ ቀላጤ በመሆን በፕሮፓጋንዳ ጦርነቱን ሲያቀጣጥሉ የነበሩና ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ “መጠየቅ ካለብኝ ልጠየቅ፣ በመጀመሪያ ትህነግ ጉባኤ ከማድረጉ በፊት አስቀድመን ጦርነቱን እንገምግም ከሚሉት”ከሚሉት ወገኖች መካከል እንደሆኑ በተደጋጋሚ መገለጹ አይዘነጋም።
በሌላ ተመሳሳይ ዜና አቶ ጌታቸው ዛሬ በይፋ ተሰናብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ “አመሰግናለሁ” ሲሉ በትግርኛ ባሰራጩት የስንብት መልዕክት የሚከተለውን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሰገኑ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ ላለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት÷“በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት 62 (9)፣ አዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15(3) እና ደንብ ቁጥር 533/2015 እንዲሁም በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት አቶ ጌታቸው ረዳ ላለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል፡፡
በተለይም አቶ ጌታቸው የተገኘው ሰላም እንዲጸና ለነበራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄና አመራር የፌደራል መንግስት እውቅና እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይ ሥራዎች በጋራ ተቀራርበው እንደሚሰሩ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ አቶ ጌታቸው ረዳ በአመራርነት ቆይታቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሪፖርቱ የተጠናከረው ከተለያዩ ጽሁፉን ያጋሩ ገጾች ሲሆን ለዜና እንዲያመች ተደርጎ ቀርቧል።