“አብንን ወከለዋል” በሚል በፓርላማና በክልል የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች ከአንድ ዞን ወይም ከሁለት ብቻ መሆናቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ማስታወቃቸውን ተከትሎ “እንዴት? ማን አደርገው? ለምን ሆነ” የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ከብልጽግና ጋር እርስ በርስ ላለመፎካከር ተስማምተው ምርጫውን ማከናወናቸው ” ይህን ያከናወነው የማን ኔት ዎርክ ነው?” የሚለውንም ጉዳይ አጉልቶታል።
“ለብዙ የከረመ ጩኸትና ፍረጃቸው መልስ ላለመስጠት ተቆጥበን የቆየንባቸው ግዜአት ዋጋ እንዳስከፈሉን አላጣነውም” ያሉት አቶ በለጠ በርካታ መረጃ እንዳላቸው አመልክተዋል።
” … እሱ ብቻ ሀቀኛ የህዝብ ታጋይ፣ አዋቂና ተቆርቋሪ የሆነ ቡድን በውስጣችንና በዙሪያችን ከቦን ነበር/አለ። ይህ አካል ሜዳውንና ሚዲያውን በጩኸት ተቆጣጥሮና Echo-chamber አስፍኖ ብቻውን ሲናገር፣ ሲከስ፣ ሲወነጅል፣ ሲራገምና ስም ሲያወጣ ቆይቷል” ያሉት ይህ ቡድን ሌሎች የንቅናቄውን አባላት ሲፈረጅ መኖሩን አውስተዋል።
“… የፍረጃ ሜዳውንና ሚዲያውን በሙሉ የተቆጣጠረ አንድ ቡድን መኖሩ ገሀድ ሆኗል። እሱ ላልወደደው ሁሉ ስም የሚያወጣ፣ የማንነት ደረጃ የሚመድብ፣ እሱ ብቻ ሀቀኛ የህዝብ ታጋይ፣ አዋቂና ተቆርቋሪ የሆነ ቡድን” አድርጎ ራሱን እንደሚቆጥር ገልጸዋል። ቡድኑን ” ውስጣችንና በዙሪያችን ከቦን ነበር/አለ” ብለዋል።
ይህ ቡድን እያደናገረ መሄድ ስለሌለበት ዝምታ መቆሙን ያመለከቱት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ” … ከእንግዲህ ተገቢውን ምላሽ መስጠትና አደናጋሪወች እያደናገሩ እንዳይቀጥሉ እግር በእግር ሊጋለጡ ይገባል፤ ይህንን በማድረግም የሚወናበደውን ወገን ማዳን ያስፈልጋል ብለን አምነናል።” ሲሉ በግል የፌስቡክ ገጻቸው አስነብበዋል። መደናገሩና ሌሎችን በማሸማቀቅ የተኬደበት አግባብ ዛሬ ክልሉ ለደረሰበት ምስቅልቅል ግብዐት እንደሆነም አመልክተዋል።
” … ምን ዋጋ አለው! ምርጫው 2013 ዓ.ም ሰኔ ሊካሄድ ገና በመጋቢት ወር በሁለት ዞኖች የሚወዳደሩ “የአብን ሰወች” (የዛሬወቹ 5ቱ የፓርላማ እና 13ቱ የክልል ምክርቤት “የአብን” ተወካዮች…..18ቱም ከአንድ ዞን ቢበዛ ከሁለት ዞኖች ብቻ የተመረጡ መሆናቸውን ልብ ይበሉ) ከአካባቢያቸው የብልጽግና ሰወች ጋር (የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል እና ዛሬ በብልጽግና ውስጥ የሌሉ በወቅቱ የፌዴራል ቱባ ባለስልጣናት ጋር) ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ “እርስበርስ ላለመፎካከር” እና “ሰወቻችንን ማስመረጥ” በሚል ምክክር አንድ ስምምነት ላይ የደረሱ መሆኑን መረጃ ነበረኝ። በርግጥም ከምርጫው ቀደም ብሎ መጋቢት ወር ላይ በዚህ ጉዳይ ከአንድ ሁነኛ ሰው መረጃ በጽሁፍ ደርሶኝ ነበር። ይህንንም መረጃ በወቅቱ ለአስፈጻሚ አባላት አካፈልኩ። ሆኖም የምርጫ ዝግጅታችንን እንዳያስተጓጉል መተው የተሻለ ስለመሰለን ትተነዋል” ያሉት የአብን ሊቀመንበር ጽሁፋቸውን ባጋሩበት ገጻቸው ግርጌ ፓርቲያቸውን በመጻረር የተቹበትን ቃለ ምልልስ አያይዘዋል። ጽሁፋቸውን ከስር እንዳለ አቅርበነዋል።
“በጫማችን ስር የማይወድቅ፣ በብብታችን ስር የማይወሸቅ ተቋም መፍረስ አለበት” በፓርላማ ያሉ አንዳንድ “የኛ ሰወች”¡¡
ለብዙ የከረመ ጩኸትና ፍረጃቸው መልስ ላለመስጠት ተቆጥበን የቆየንባቸው ግዜአት ዋጋ እንዳስከፈሉን አላጣነውም። በአጠቃላይ ንቅናቄአችን ውስጥ የፍረጃ ሜዳውንና ሚዲያውን በሙሉ የተቆጣጠረ አንድ ቡድን መኖሩ ገሀድ ሆኗል። እሱ ላልወደደው ሁሉ ስም የሚያወጣ፣ የማንነት ደረጃ የሚመድብ፣ እሱ ብቻ ሀቀኛ የህዝብ ታጋይ፣ አዋቂና ተቆርቋሪ የሆነ ቡድን በውስጣችንና በዙሪያችን ከቦን ነበር/አለ። ይህ አካል ሜዳውንና ሚዲያውን በጩኸት ተቆጣጥሮና Echo-chamber አስፍኖ ብቻውን ሲናገር፣ ሲከስ፣ ሲወነጅል፣ ሲራገምና ስም ሲያወጣ ቆይቷል።
እኛም በማያልቅ ዝምታ ሁሉን በመቻል ቆይተናል። ዝምታችን አንድም በምልልስ ህዝብን ላለማደናገር በማሰብ፤ ሁለትም የርስበርስ መጓተትና መፈራረጅ ቀዳሚ ጉዳያችን አይደለም ሊሆንም አይገባም በሚል የጸና እምነት፤ ሶስትም ወርደን እሰጣገባ ውስጥ ራሳችንን ለማዋል ባለመፍቀድ ነበር። ከእንግዲህ ተገቢውን ምላሽ መስጠትና አደናጋሪወች እያደናገሩ እንዳይቀጥሉ እግር በእግር ሊጋለጡ ይገባል፤ ይህንን በማድረግም የሚወናበደውን ወገን ማዳን ያስፈልጋል ብለን አምነናል።
ይህ ከውስጣችን ያስወጣነው መንጋ-አንጋሽ የዘወትር ጎታች ሀይል፤ በአደባባይ ልኩን ሊነግረው የደፈረ እምብዛም አልነበረም። በማያባራ ዘመቻ ሰውን ሁሉ ስም አውጥተው ስላሸማቀቁት ብቻቸውን ብይን የሚሰጡ ሆነው እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። ሆኖም አንዳንዴ “እኛ እንናገር ሰው አይደናገር” እንደተባለው እነዚህን አደናጋሪወች በልኩ ማሳፈር አስፈላጊ ይሆናል። ይህ ሁኔታቸው ህዝባችን ዛሬ ለገባበት ምስቅልቅል አንድ ምክንያት በመሆኑ እጅጉን ያሳዝናል ልብንም ይሰብራል!
ለመሆኑ እነዚህን “በጫማችን ስር የማይወድቅ፣ በብብታችን ስር የማይወሸቅ ተቋም መፍረስ አለበት” የሚሉ ሰወችን ምን ብናረጋቸው ይሻል ይሆን? ፖለቲካ ማለት “ጉዳይ እንዳይረጋ መወዝወዝ፣ ወደፊት እንዳይራመድ መጎተት፣ እንዳይጸና ማሰናከል” የሚመስላቸው ራሳቸውን የሁሉ ነገር ሚዛን ያደረጉ የጥጥ ልቃቂወች ምን ብናደርጋቸው ይሻል ይሆን!?
እነሆ “የአብኑ የፓርላማ ተወካይ” የምንወደውን ፓርቲአችንን “የማፍርበት ፓርቲ ነው” ሲል ይደመጣል። ይህስ አያሳፍርም ወይ!? አንድ ሰሞን አብን በሩን ስለዘጋብን ፓርቲ ልንመሰርት ብለን አዳራሽ ተከለከልን በማለት ሲጮሁ ነበር። እነሱ ፓርቲ ሲያፈርሱ መብት አላቸው ትክክልም ናቸው፣ እኛ ፓርቲ ስናድን ተሳስተናል! ከእንዲህ ያለ ሰው ጋር እንዴትስ መግባባት ይቻላል?! አንድ ወቅት የፈረንሳዊ ፈላስፋ ሞሪስ መርሉፖንት (Maurice Merleau-Ponty) ያለውን አስታወሰኝ። Rene Descartesን የመሰሉ ፍጹማውያንን ሲተች አይመቹም ይላቸዋል።
ሚስጥር ከፈጣሪ ለኛ ብቻ ተገልጦልናል ከሚሉ፣ የእውነት መንገድ ለኛ ብቻ የሆነ ነው ከሚሉ፣ የእውነትን ቁልፍም እኛ ብቻ ይዘናል ከሚሉ ፍጹማን ክርስቲያኖች ጋር የሀሳብ ሙግትና ክርክር ማድረግ ፈጽሞ አይቻልም ይላል። ስህተት፣ አለመታመን፣ ውድቀት ወዘተ ከሌላው ዘንድ ብቻ ነው ከሚሉ (Hell is the Other እንዲል Jean-Paul Sartre)፤ እውነት፣ መታመን፣ ተቆርቋሪነትና ህሊና ከኛ ዘንድ ብቻ የሚገኝ ከሚሉ….ከነዚህ “ሁሌ ትክክልና ንጹህ” ከሆኑ ከኛ ድኩማኖች ጋር መግባባት በርግጥሞ እጅግ የከበደ ጉዳይ ሆኗል።
እናም Maurice Merleau-Ponty እንዲህ ሲል ገለጻቸው:-
It is impossible to engage in a genuine dialogue with the Christian who believes that he possesses this Truth in faith and thinks that he can look at man, at the world and history in the light of this Truth. [Such a person] is not a man among men, because he enjoys a divine guarantee.
ለማንኛውም ወደ ጉዳየ ስመለስ ይሄ ከሳሻችን ከምርጫ በፊት አባል እያለ እንኳ በቅጡ አናውቀውም። ድንገት ከአንድ ወረዳ ተመረጠ ሲባል ሰማን። ከአሁን ቀደምም ቢሆን የጠቅላላ ጉባኤ አባልም የነበረ አይመስለኝም። ምን ዋጋ አለው! ምርጫው 2013 ዓ.ም ሰኔ ሊካሄድ ገና በመጋቢት ወር በሁለት ዞኖች የሚወዳደሩ “የአብን ሰወች” (የዛሬወቹ 5ቱ የፓርላማ እና 13ቱ የክልል ምክርቤት “የአብን” ተወካዮች…..18ቱም ከአንድ ዞን ቢበዛ ከሁለት ዞኖች ብቻ የተመረጡ መሆናቸውን ልብ ይበሉ) ከአካባቢያቸው የብልጽግና ሰወች ጋር (የወረዳ፣ የዞን፣ የክልል እና ዛሬ በብልጽግና ውስጥ የሌሉ በወቅቱ የፌዴራል ቱባ ባለስልጣናት ጋር) ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ “እርስበርስ ላለመፎካከር” እና “ሰወቻችንን ማስመረጥ” በሚል ምክክር አንድ ስምምነት ላይ የደረሱ መሆኑን መረጃ ነበረኝ። በርግጥም ከምርጫው ቀደም ብሎ መጋቢት ወር ላይ በዚህ ጉዳይ ከአንድ ሁነኛ ሰው መረጃ በጽሁፍ ደርሶኝ ነበር። ይህንንም መረጃ በወቅቱ ለአስፈጻሚ አባላት አካፈልኩ። ሆኖም የምርጫ ዝግጅታችንን እንዳያስተጓጉል መተው የተሻለ ስለመሰለን ትተነዋል።
የፌዴራል ፓርላማ ሰወቻችን እኛን በወገብ ሰባሪው የምርጫ ዝግጅት ስራ ከማዕከል ከማገዝና ከማስተባበር ይልቅ፤ ምርጫው ወራቶች እየቀሩት ወደ አካባቢያቸው በመሄድና እዛ ከድርጅት ስምሪት ውጭ የአካባቢያቸው የብልጽግና ሰወች ጋር በመገናኘትና በመምከር፣ ከፓርቲ እውቅና ውጭ ከፍተኛ ገንዘብ ከዳያስፖራው በመሰብሰብ፣ ፓርቲን ሳይሆን ራሳቸውን ብቻ አስቀድመው ተንቀሳቅሰዋል። በወቅቱ ይሄንን ለማረም ብንሞክርም ዲሲፕሊንና መደማመጥ ጠፍቶ ተቸግረን ነበር። አለፈ።
የኛ የምርጫ ወረዳ ላይ ደግሞ በወቅቱ የክልሉ የአደረጃጀት ጉዳዮች ሀላፊ የነበረውና የኔ ምርጫ ወረዳ ተፎካካሪየ በነበረ ሰው (ደሳለ በላይ ) በልጆቻችን ላይ ወከባ በመፈጸምና በማስፈጸም በምርጫ ሂደቱም ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። በቂ የቪዲዮ፣ የድምጽና፣ የፎቶ ማስረጃ ስለነበረን ቅሬታችንን ለምርጫ ቦርድ በማቅረብ እንዲታይልን ስላደረግን ቦርዱ ምርጫው በድጋሜ እንዲካሄድ ወስኗል (ምንም እንኳ በሰላም እጦት ምክንያት ድጋሜ ምርጫ ባይደረግም)። ህገ ወጥ ሰው ድርብርብ ጉዳት ነው በሌሎች ላይ የሚያደርሰው። በነዚህ ህገወጦች ምክንያት የራያ ቆቦ ህዝብ በፓርላማ ያለወኪል እንዲቀር ሆኗል። ይሄ ልቤን ያደማዋል። የራያ ቆቦ ህዝብ በፓርላማ ድምጽ የሚሆነውና ጥያቄወቹን የሚያቀርብለት አካል እጅጉን ያሻው ነበር። ሁለት ግዜ የተወረረ፣ ሰፊ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያስተናገደ ህዝብ እንደመሆኑ ሊደመጡለት የሚገባቸው ጉዳዮች ነበሩት፣ ሊመለሱለት የሚገባቸው ጥያቄወች ነበሩት!
ወደኛወቹ የፓርላማ ሰወች ልመለስና ቁመናቸው ምን ይመስላል ቢባል ግማሽ ወያኔ፣ ሲሶ ታጣቂ፣ ሲሶ አብን ሆነው ስላገኘናቸው የሰላማዊ ትግላችን አካል ባለመሆናቸው ጥለናቸው ልንጓዝ ተገደናል።
ለህዝብ ድምጽ መሆን አንድ ጉዳይ ነው። ሆኖም በፓርላማ አብዝተው ይጮሀሉ። ከጮሁም በኋላ እኛኑ ሳይቀር በቢሮ ቀጠር እንድንይዝላቸው ይወተውታሉ። ስናገኛቸው ስራ እንድንሰጣቸው እንድንተባበር ይጠይቃሉ። የበላይ አካላትንም እንድናገናኛቸው ከአደራ ጭምር ይወተውታሉ። ግራ!
ሰው አመታትን ተጉዞ፣ እድሜ ጨምሮ፣ ልምምዱ ሰፍቶ፣ ምንም ለውጥ አለማሳየቱ ግን ምንኛ ነው!? እንደሚገባኝ ፖለቲካ ማለት መራመድም፣ መጓዝም፣ ወደፊት ወደኋላና ዙሪያገባ ማየትም፣ መታደስም፣ መለወጥም፣ መነጋገር፣ መደማመጥ፣ መግባባት፣ መቀራረብ፣ መተባበር፣ መስጠት-መቀበል፣ መሀል መፈለግ፣ አማካይ ማመላከት፣ ወዳጅ ማብዛት፣ ጠላት መቀነስ….እንዲህ እንዲህ መሰለኝ! ወይ ተሳስቻለሁ!?
ሁሌም ባሉበት መርገጥ፣ አለመጓዝ፣ አለመከፈት፣ አለመነጋገር፣ አለመተባበር፣ መጮህ፣ መፈረጅ፣ ቆሞ መቅረት…..ፖለቲካ አልመሰለኝም!
ዮሀንስ የሳሊስቡሪው (John of Salisbury) ወደ ሩቅ ሀገር ኖሮ ሲመለስ የድሮ ጓደኞቹ ምንም ሳይለወጡ ባሉበት ተደንቅረውና ይልቁንም ትህትናን አውልቀው ጥለው ሲያገኛቸው እንዲህ ገለጻቸው:-
as before, and where they were before; they did not appear to have advanced an inch in setting the old questions, nor had they added a single proposition. The aims that since inspired them, inspired them still; they had progressed in one point only: they had unlearned moderation, they knew not modesty; and that to such an extent that one might despair of their recovery…
የኛወቹስ ይድኑ ይሆን !?
(አበባው ደሳለው በአብን ስም በፓርላማ የተቀመጠ ሰው ስለሆነ ነው ይህንን እንጽፍ ዘንድ ያስፈለገን)።
ተናግረው ከሚያናግሩ ይጠብቀን እንጂ እንዲህ መሆንንማ አንወደውም ነበር!