ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 19/2017 ዓ.ም. በተካሄደው የለንደን ማራቶን ውድድር አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ቀዳሚ በመሆን አሸንፋለች። አትሌት ትዕግሥት ውድድሩን ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመግባት (2:15:50) እና ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ነው ያሸነፈችው።
አትሌት ትዕግሥት ዛሬ ያስመዘገበችው ሰዓት በሴቶች ብቻ የተሮጠ የዓለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦላታል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ሁለተኛ በመውጣት ብር ያገኘችው ትዕግሥት አሰፋ፣ በዛሬው የለንደን ማራቶን ከዚህ ቀደም በኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር የተያዘውን ፈጣን ሰዓት በ26 ሰከንድ በማሻሻል ማሸነፍ ችላለች።
ትዕግሥት “ባለፈው ዓመት [በለንደን ማራቶን] ሁለተኛ ነበር የወጣሁት፤ ስለዚህ በዚህ ዓመት ማሸነፌ በጣም ልዩ ነው። በጣም፣ በጣም ደስተኛ ነኝ” ስትል ለቢቢሲ ዋን ተናግራለች።
“ባለፈው ዓመት ከቅዝቃዜው ጋር በተያያዘ ትንሽ ችግር አጋጥሞኝ ነበር። እንዲሁም የእግሬ ጡንቻ ላይ ሕመም ነበረኝ። በዚህ ዓመት አየሩ በጣም ተስማምቶኛል” ስትል አክላለች።
“ሩጫው የተጠናቀቀበት መንገድ በጣም አስደስቶኛል።”
በዘንድሮው የለንደን ማራቶን ኬንያዊቷ ጄፕኮስፔ ሁለተኛ፣ ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሀሰን ደግሞ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቅቀዋል።
ትዕግሥት ባለፈው ዓመት በለንደን ማራቶን ሪከርድ ለማስመዝገብ እንደምትሮጥ ተናግራ የነበረ ቢሆንም ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሳለች።
የፓሪስ ኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ሲፋን ሀሰን ዘንድሮ በተካሄደው የለንደን ማራቶን ሦስተኛ ሆና አጠናቅቃለች።
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ አቅራቢያ በምትገኘው ሆለታ ከተማ ነው።
አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ፣ አትሌት ሲፋን ሀሰንን ተከትላ ሁለተኛ ሆና በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አምጥታለች።
ትዕግሥት ወደ አትሌቲክስ የገባችው በትምህርት ቤቶች መካከል በተደረጉ ውድድሮች እንደሆነ ተናግራ ለዚህም የሰውነት ማጎልመሻ መምህሯ አስተዋፅዖ ማድረጋቸውን ተናግራ ነበር።
ትዕግሥት በ2016 ዓ.ም. በጀርመን በርሊን በተካሄደ 48ኛው የማራቶን ውድድር የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ ወሰንን ከሁለት ደቂቃ በላይ በማሻሻል አሸንፋለች።
ለረዥም ጊዜያት የ800 ሜትር ሯጭ የነበረችው ትዕግሥት፣ ወደ ጎዳና ሩጫ ፊቷን ያዞረችው ዘግይታ ነው።
በ2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክላ በ800 ሜትር ተሳትፋለች።ሆኖም ከግማሽ ፍጻሜው ማለፍ ባለመቻሏ ከውድድሩ ውጪ ሆና ነበር።
ትዕግሥት ከ800 ሜትር በተጨማሪ በ400 ሜትርም ስትወዳደር ቆይታለች።
አትሌቷ ቀደም ሲልም የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ለማሸነፍ በቅታለች።
የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ባለቤቷ ትዕግሥት አሰፋ በፓሪስ ኦሎምፒክ በ2 ሰዓት ከ22 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።
የ2025 የወንዶች ለንደን ማራቶን ውድድር ኬንያዊው ሴባስቲያን ሳው በአሸናፊነት አጠናቋል።
ኬንያዊው አትሌት ሴባስቲያን ሳው ውድድሩን 2:02:27 በመግባት በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ፣ ኡጋንዳዊው አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ ሁለተኛ ኬንያዊው አትሌት ሙቲሶ ሙንያኦ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter