ጎንደርን “ማርሽ ቀያሪ” የሚሏት በርካቶች ናቸው። ” የኦሮሞ ደም የእኔም ደም ነው” በማለት ለውጡ እንዲቀጣጠል፣ የትግል ትስስር እንዲፈጠር ያደረጉት ብልህ አካሄድ መለያቸው ነው። በቅርቡ በጅምላ በአማራ ስም ሌሎች ሲወገዙ “ጸባችን ከድርጅቱ ጋር ነው” በማለት መንገድ አስተካክለዋል። ከምንም በላይ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከትና ጦርነት መርመረው ጀርባቸውን በመስጠት “የተፈጠረውን የልማት አጋጣሚ እንጠቀምበት” በማለት አካባቢያቸውን ከሁከት አጽድተዋል።
ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትና ከዚያም በፊት ከልማትና ዕድገት ተገላ የኖረችው ታሪካዊቷ ጎንደር አሁን ላይ አይኗን እየገለጠች ነው። በርካታ ችግሮች ቢኖሩባትም ወዟን ለመመለስ ደፋ ቀና እያለች ነው። ታሪካዊ አሻራዎቿንና የኢትዮጵያን የስልጣኔ ደረጃ ምስክር የሆኑትን ቅርሶቿንና ዕድሜ ጠገብ ህንጻዎቿን አቧራ አራግፋ እንዲያበሩ አድርጋለች። ጎርጎራም ላይ ስቃለች። የ”ውሃ ያለህ” የዘመናት ጩኸቷን ለታቆም መገጭን አንቃ ይዛ ጥሟን ልትቆርጥ እየተንደረደረች ነው። ማርሽ ቀያሪዋ ጎንደር።
ፖለቲካና የፖለቲካን አካሄድ ክህነት ጠንቅቃ ያጠናችው ጎንደር፣ ጉድለቷ ብዙ ቢሆንም፣ የታሪክ ጠገብትነቷን በሚመጥን ደረጃ አብሪ ኮከብ እንድትሆን ከተጀመረው ልማቷ በተጨምሪ “እንሞሽራት” በሚል ለቀረበ ጥሪ የተሰጠው መልስ ይሁን የሚያሰኝ ነው።
“አዲሷ ቅኔ” ጎንደር የአብራክ ክፋዮቿና ጎረቤቶቿ ለመፍረስ ሲዳክሩ፣ ለቀውስ ሌት ተቀን ሲተጉ፣ ተቋም ለሚያወድመው ፍልሚያ ነዶ ሲወዘውዙ ማርሽ በመቀየር ወደ ውስጧ ያየችው ጎንደር “ልሞሸር” ባለችበት ቅጽበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ዘመናዊ የአየር ማረፊያ “እነሆኝ” ብሎ አበባ ነስንሶላታል። የኢትዮጵያዊያን ኩራት የሆነው አየር መንገዳችን ኩራት ለሆነችው ጎንደር የሚገባትን “ይኼው ከጄ” ብሏል።
የሶማሌ ክልል 15 ሚሊዮን ብር፣ ባላሃብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ 20 ሚሊዮን ብር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 121 ሚሊየን ብር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። እነዚህ ለጊዜው ቢጠቀሱም እጃቸውን የሰነዘሩት ብዙ ናቸው።
“ኑ ጎንደርን እንሞሽር” በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ዛሬ ሲዘጋ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰብ ተችሏል። በዛሬው የገንዘብ ማሠባቢያ መርሐ ግብር ከ2 ሺህ ብር እስከ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ድጋፍ መደረጉ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ከስድስት ዓመት ታዳጊ እስከ ሀገር ሽማግሌዎች የታደሙበት፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉ ወገኖች የተሳተፉበት መሆኑን አሚኮ ዘግቧል።
ሌሎች የጦርነት ከበሮ ሲደልቁ፣ የጦርነት ዘናና ዕቅድ ሲያስተጋቡ፣ እዛም እዚህም ጥይት ሲያጮኹ “ኑ ጎንደርን እንሞሽር” በሚል መሪ አሳብ የተጀመረው ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እስከ ግንቦት 30/2017 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚቀጥል አስታውቃለች። ጎንደር የጦርነት ወሬን “መስሚያዬ ጥጥ ነው” ብላ ከዘመኑ ጋር አብራ መራመድን መርጣለች።
“በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮችና ሙያተኞች፣ የወረዳና ከተማ አመራሮች ደሞዛቸውን ለእናትዋ ጎንደር ለመሞሸር 2,118,212.8 ብር አበርክተዋል። ጎንደር የሀገር ብልጽግና ማገር” ሲሉ ተሳትፏቸውን አስታውቀዋል።
መርሃ ግብሩ ሲጀመር “ጎንደር የኢትዮጵያውያን ሁሉ የታሪካችን አሻራ እና የማንነታችን መገለጫ ናት” ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ጎንደርን አሞካሽተዋል።
“ኑ ጎንደርን እንሞሽር” በሚለው መሪ ሐሳብ ለታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ዘርፈ ብዙ ልማት የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል መጀመሩን አብስረዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ መንግስት ለጎንደር፣ ለባሕር ዳር እና ለደሴ ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለእያንዳንዳቸው 100 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክታቸውም÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ጎንደርን አቧራዋን በማራገፍ ያላትን እምቅ የመበልጸግ ዕድል በመጠቀም ድምቀቷ የበለጠ እንዲታይ ጅምር ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለትውልድ የምናስረክባትን ውብ እና ማራኪ ከተማ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል ያሉት አቶ አረጋ÷ ይህንን ለማድረግ ጊዜው አሁን እና ዛሬ መሆኑን ተናግረዋል።
አባቶቻችን ውብ አድርገው የሰጡንን፣ እስካሁን ግን አቧራ ለብሳ የቆየችውን ከተማ ውብ እና ማራኪ አድርጎ የመገንባቱን ኃላፊነት ወስደናል ሲሉም አመላክተዋል።
“ጎንደር ሕንጻ ብቻ አይደለም የተሸከመችው፤ ይልቁንም የማንነት መገለጫ አሻራዎችን አምቃ የያዛች ከተማ መሆኗን መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter