ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አማራዊ ማንነት እንደ ወንጀል በመቁጠር አፍኖ በመሰወር፣ በመግደል፣ አካልን በማጉደል፣ ከሰማይ በታች ከመሬት በላይ አለ የሚባል ግፍ ሁሉ በመፈፀም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ታሪክ አዋቂዎች፣ ስለ ህዝብ መብት ተከራካሪ የሆኑትን የሀይማኖት አባቶችን፣ሲገድል ደብዛቸውን ሲያጠፋና ሲያሳድድ የኖረው ህወሓት ዛሬም በህዝብ ትግል ከወልቃይት ጠገዴ ቢባረርም ነገር ግን የወልቃይት ጠገዴ ጎንደር አማራ ተወላጅ የሆኑ በሱዳን አገር አድኖ በማንነታቸው ለይቶ ግፍና በደል እያደረሰባቸው ይገኛል።
በኢትዮጵያ አንድነትና ዳር ድንበር መከበር፣ በርስቱና፣ በማንነቱ ድርድር የማያውቀው የወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብ በተለይም የትህነግን አገር አፍራሽ እኩይ ሴራና ድርጊት ቀድሞ በመረዳት አቅሙና ሁኔታው በፈቀደለት መንገድና መጠን እራሱን አደራጅቶ በመታገሉ የትህነግን ቀጣይ መስፋፋት እቅድና የሃገር ግንጠላ ሴራ በማክሸፍ ህዝባችን አማራዊ ማንነቱን ለማስከበር ባደረገው የተቀናጀ መራር ትግል መላውን አማራና ፍትህ ወዳዱን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ የትህነግን ፋሽስታዊና አምባገነናዊ ስርዓት አስወግዶ በሚፈልገው አማራዊ ማንነቱ ከአብራኩ ክፋይ ከሆነው የአማራ ክልል ህዝብ ጋር እየተዳደረ ይገኛል።
ከ30 አመት ትግል በሗላ ህወሓት የሰሜን እዝ ማጥቃቱን ተከትሎ ነፃ የወጣውን ወልቃይት ጠገዴ ዳግም በሃይል ለመያዝ ያልጎነጎነው ሴራ፣ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም፣ ሁሉንም ሙከራ ያደረገው ህወሓት በሰመረ የህዝብና መንግስት ጠንካራ ትግል መክሸፉ የሚታወስ ነው።
በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ራያ አወዛጋቢ ቦታ ( Contested Area) ስለሆነ አይመለከትህም ተብሎ ትጥቁን አውርዶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የፈረመው ህወሓት ስምምነቱን ጥሶ የወልቃይት ጠገዴን ህዝብ ለመውረር ቀን ከሌት እየዛተ ይገኛል።
ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ህዝባችን ማንነትን መሰረት አድርጎ ሲገድልና ሲያሰቃይ የኖረው ህወሓት በህዝባችን ብርቱ ትግል ከአካባቢው ማስለቀቅ ቢቻልም በህዝባችን ላይ ያለው ጥላቻ የመጨረሻ መጀመሪያ የክፋት ጥግ ማሳያው ማይካድራ ላይ ወገኖቻችን በአማራነታቸው ጨፍጭፎ የሸሸውና በሱዳን ሃገር በሚገኘው የታጣቂ አንጃ አማካኝነት በደርዘኞች በሚቆጠሩ የወልቃይት ጠገዴ ጎንደር አማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት ፈፅሟል።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ ወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመው አረመኔያዊ ተግባር በማውገዝ በቀጣይ በጉዳዩ ዙሪያ ከፌደራል መንግስት፣ከአለም አቀፉ ማህበረሰብና ከሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጋር የሚነጋገር ይሆናል።
ህዝባችንም ዛሬም ህወሓት የወልቃይት ጠገዴ ምድር ዳግም ቢረግጥ ከትናንቱ የባሰ ግፍ እንደሚጠብቀው ሰሞኑን በሱዳን በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የፈፀመው ወንጀል ማሳያ መሆኑ ተገንዘቦ በያዘው ፅኑ የትግል መንገድና አቋም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚቴው ያሳስባል። ይህ ድርጊት የትግራይና የጎንደር አማራ ህዝብ እንዳይቀራረቡና ዘላቂ ጠላት ሆነው እንዲተያዩ ታስቦና ታልሞ እየተፈፀመ ያለ ወግናኝ ድርጊት ነው። ስለሆነም በፈተና እና በመከራ እየፀና የሚቀጥል አማራዊ የማንነት ትግል እንጂ በዚህ የሳምሪ ቡድን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ወደ ኋላ የማንል መሆናችንን እየገለጽን መስዋዕት ለሆናችሁ ወገኖቻችን መጽናናትን እየተመኘን በሰማዕታት አደራ የሚፀና አማራዊ ማንነታችሁን አስጠብቀንና አጽንተን የምንቀጥል እና ይህ ዓይነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁሉም ሰው የሆነ ፍጡር እንዲታገለው ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ምንጊዜም ለአማራዊ ማንነታችን ትርጉም ያለው መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን!
ከወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
ሁመራ-ጎንደር-አማራ-ኢትዮጵያ
መጋቢት 25/2017 ዓ.ም