አርሶ አደሩ ያመረተውን ወደ ገበያ እንዳያወጣ በየአቅጣጫው ታጣቂዎች ገደብ ይጥላሉ። ነጋዴዎችም ሄደው አርሶ አደሩ ዘንድ ገዝተው ወደ ገባያ እንዳያቀርቡ ችግር አለ። ህዝብ በየአቅራቢያው በሚቆሙ ገበያዎች ቀን ጠብቆ ለመሸመት አልቻለም። በዚህ መነሻ ወደ ገበያ የሚቀርብ ምርት እጥረት አለ። ይህ እጥረት ደግሞ የዋጋ መናርን ወልዷል። እየተጎዳ ያለው ደሃው ነው። አርሶ አደሩም ደህይቷል። በግዳጅ ዕህል እየሰፈረ ባዶ እጁን ቀርቷል። ከስር አሚኮ የኑሮ ፈተና ብሎ ይህን ዘግቧል።
የኑሮ ውድነት የዘመኑ የዜጎች ፈተና ነው። ብዙዎች የኑሮን ዳገት መውጣት ፈተና ኾኖባቸዋል። ወር እስከ ወር መድረስ ፈተና የሚኾንባቸው የመንግሥት ሠራተኞች፣ ለልጆቻቸው ምን እናቅርብ የሚሉ እናቶች ብዙዎች ናቸው።
አንድ ጊዜ ወደላይ የወጣ ዋጋ ወደ ታች የመመለስ ሂደቱ አናሳ ነው። ገበያውን ጥጋብ ያድርገው እያለ የሚመኘው የሀገሬው ሰው በገበያው ሲማረር ይውላል። እሥር ሙሉ ብር ይዞ ገበያ ወጥቶ ዘንቢል የማይሞላ ዕቃ ይዞ መመለስ ተለምዷል። ይህ ደግሞ ሀገሬውን አማርሯል።
በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ደግሞ የኑሮ ውድነቱን የበለጠ አባብሶታል
በደቡብ ወሎ ዞን የወረኢሉ ከተማ ነዋሪ እናት የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ይላሉ። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ደግሞ በእንቅርት ላይ እንዲሉ ኾኗል ነው ያሉት።
የመንገድ ሰላም አለመኾን ምርት ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፣ ነጋዴው ለሸማቹ እንዳያደርስ፣ ነዋሪዎችም በገበያው የፈለጉትን እንዳያገኙ አድርጓል ብለዋል።
መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ጥረት ሊያደርግ ይችል ይኾናል፣ ነገር ግን የኑሮ ውድነቱ አልቀነሰም ነው ያሉት። ሰላም እስከሌለ ድረስ የኑሮ ውድነት ሊሻሻል እንደማይችልም ገልጸዋል።
የወልድያ ከተማ ነዋሪዋ እናት ደግሞ የኑሮ ውድነቱ መረጋጋት አሳይቷል እየተባለ የሚነገረው ነገር ልክ አይደለም፣ እንኳ ሊረጋጋ እየተባባሰ ነው የመጣው ይላሉ።
በግብርና ምርት መረጋጋት አሳይቷል የሚባለው ልክ አይደለም፣ የፋብሪካ ውጤቶች ዋጋም አይቀመስም ነው ያሉት።
የሰላሙ ችግር ደግሞ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል ነው የሚሉት። ነጋዴዎች አንድ ጊዜ መንገድ ሲከፈት የሚያመጡትን ምርት በውድ ዋጋ ነው የሚሸጡት፣ ይሄ ደግሞ ኑሮውን አባብሶታል ይላሉ።
ዋጋ እንዲረጋጋ፣ የኑሮ ውድነት እንዲቀንስ ከተፈለገ ሰው በሰላም መንቀሳቀስ አለበት። እንደፈለጉ መንቀሳቀስ እስከሌለ ድረስ የኑሮ ውድነት መቀነስ አይታሰብም ነው ያሉት።
ሰላም መጥቶ ማኅበረሰቡ ቢያንሰ በልቶ ማደር አለበት ብለዋል። ምርት የፈለገውን ያህል ቢመረት ሰላም ከሌለ ምርቱ እንደሌለ ቁጥር ነው፣ ለሁሉም ነገር መሠረቱ ሰላም ነው ይላሉ።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም ሙሐመድ (ዶ.ር) ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሠሩ ተግባራትን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በበጀት ዓመቱ ተቋሙን ለማጠናከር ዕቅድ ተይዞ ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ለመሪዎች፣ ለባለሙያዎች እና ለአጋር አካላት ሥልጠና መሥጠታቸውንም ተናግረዋል። የንግድ እና ገበያ ልማት ሥራን በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችሉ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ነው የገለጹት።
ለንግድ ተቋም ጉልበት የሚኾኑ አደረጃጀቶችን የማጠናከር ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል። ንግድ እና ገበያ ልማት፣ ፖሊስ እና ፍትሕ በቅንጅት ሕገ ወጥነትን የመከላከል ሥራ ሠርተዋል ነው ያሉት።
የኮንትሮባንድ እና የሕገወጥ ግብረ ኀይል ተቋቋሙ ሕገ ወጥነትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ለማጠናከር መሥራታቸውንም ተናግረዋል። ተቋሙን ለሥራ የተመቸ አድርገናልም ብለዋል።
በተቋሙ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አቅደን ሠርተናል ያሉት ኀላፊው 4 ሺህ 500 ቅሬታዎች ቀርበው 98 በመቶ የሚኾኑት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።
ቀሪዎቹ በመጣራት ሂደት ላይ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ለተገልጋዮች ፈጣን ምላሽ መሥጠት እና ተገልጋይን ማርካት በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ የኑው ውድነትን ለማቃለል ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ኀላፊው ለኑሮ ውድነት እና ለዋጋ ግሽበት ዓለማቀፍዊ፣ ሀገራዊ እና ክልላዊ ኹኔታዎች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው የተናገሩት።
ዋጋን ለማረጋጋት የንግድ ተዋንያንን አቅም መገንባት አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል። ጤናማ የኾነ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል።
ለሸማች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የገንዘብ አቅርቦት የማመቻቸት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መመቻቸቱንም ገልጸዋል። ይህ ሀብት ሸማች የኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅም እንዲፈጥሩ አድርጓል ነው ያሉት።
የግብይት ቦታ አማራጮችን ማስፋፋት በዘጠኝ ወራት በትኩረት የተሠራባቸው ሥራዎች መኾናቸውን ነው የተናገሩት። በዘጠኝ ወራት 80 ያህል የንግድ ባዛሮች መካሄዳቸውን የተናገሩት ኀላፊው በዓልን ታሳቢ ያደረጉ 10 ባዛሮች እንደሚካሄዱም ገልጸዋል።
ተደጋጋሚ የድንኳን ገበያዎችን በማዘጋጀት የፍጆታ ምርቶችን ለማቅረብ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት። የእሕድ ገበያዎችም ተጠናክረው መሠራታቸውን ነው የገለጹት። በስምንት ታላላቅ ከተሞች የገበያ ማዕከላት እየተሠሩ መኮናቸውንም ገልጸዋል።
በተሠራው ጠንካራ ሥራ በግብርና ምርቶች ላይ መረጋጋት እንደታየም ገልጸዋል። በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ግን አኺንም ፈተናዎች እንዳሉ ነው የተናገሩት። የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማስፋፋት እና አቅርቦትን ከፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል። የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት አቅርቦትን ማትረፍረፍ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ለጤናማ የንግድ ሥርዓት ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል። ባለፉት ወራት የኑሮ ውድነት ሊያሳድር የነበረውን ከፍተኛ ተጽዕኖ መቀነስ የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ከፍተኛ ሥራ ባይሠራ ኖሮ ሕዝብን ለከፍተኛ ጫና የሚያጋልጡ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችሉ እንደነበር ነው የተናገሩት። የኑሮ ውድነትን የበለጠ ለማሻሻል አኹንም ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚጠይቁ አመላክተዋል። የኑሮ ውድነት አባባሽ ምክንያት የኾነውን የሰላም ችግር ታግሎ መፍታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በክልሉ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ሕገ ወጥ አካሄዶች መኖራቸውን ተናግረዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕገ ወጥነት እንዲስፋፋ እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
በየቦታው ያለው ዘራፊ ቡድን በየቦታው ኬላ በመዘርጋት አቅርቦት በወቅቱ እንዳይቀርብ ያደርጋል፣ ቀረጥ ይጥላል፣ ይቀማል፣ ይዘርፋል፣ ነዳጅ የጫኑ መኪናዎችን በጥይት እየመታ ነዳጅ ይደፋል ነው ያሉት።
የንግድ ሥርዓቱ ጤናማ እንዲኾን ከተፈለገ ምርት በነጻነት መንቀሳቀስ ይገባዋል ብለዋል። የምርት እንቅስቃሴን የሚገድብ ቡድን የሚጎዳው ሕዝብን ነው ያሉት ኀላፊው በክልሉ የኑሮ ውድነትን እያባባሰ ያለው የጸጥታ ችግር መኾኑን ኃላፊውን ጠቅሶ አሚኮ ዘግቧል።