በምዕራብ አርሲ ዞን ነገሌ አርሲ ከተማ ነዋሪ የሆኑት በተመሳሳይ ሙያ ላይ የሚገኙት መምሕር ጉተማ ኡካ እና መምሕርት ጠይባ ቱሪ ለሀያ ሠባት ዓመታት በትዳር የቆዩ ሲሆን አራት ልጆችንም አፍተዋል።
ጥንዶች ሠላማዊ የሆነ የትዳር ጉዞ የነበራቸውና ቤት ለመስራት ዝግጅት ላይ ነበሩ ያለው የምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ ሚስት ባል በትዳሩ ላይ እንደቀድሞ አልሆን አለ የሚል የቅናት ጥርጣሬ በመያዝ አለመግባባቶች መፈጠራቸውንም ይገልፃል።
ሚስት በመሀላቸው የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ስትጥር በነበረበት ሠዓት ደግሞ ሁለተኛ ሚስት ሊያገባ ነው የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ በመስማቷ መኮራረፍ ብሎም መጨቃጨቅ ይቀጥላል።
በሰማችው ነገር ብስጭት ያለባት ተከሳሽና የሟች ሚስት የሆነችው መምህርት ጠይባ ቱሪ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ከለሊቱ 9:00 ላይ ባለቤቷና የአራት ልጆቿ አባት የሆነው መምህር ጉተማ ኡካ በተኛበት በእንጨት መፍለጫ መጥረቢያ አንገቱ ላይ ደጋግማ በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጓን ነው የአርሲ ዞን ፖሊስ የገለፀው።
ተከሳሿ ድርጊቱን ከፈፀመች በኋላ እስኪ ነጋ ቆይታ እጅዋን ለፖሊስ የሰጠች ሲሆን ፖሊስም በስፍራው ተገኝቶ የሟችን አስክሬን በማንሣት ለምርመራ ወደ ሆስፒታል በመላክ ወንጀል የተፈፀመበትን የእንጨት መፍለጫ መጥረቢያ በማስረጃነት በመያዝ የምርመራ መዝገቡን አጣርቶ ለአቃቤ ህግ ልኳል።
አቃቤ ህግም ከፖሊስ የደረሰውን የወንጀል ምርመራ መዝገብ መነሻ በማድረግ ክስ የመሰረተ ሲሆን ክሱን ሲመለከት የቆየው የምዕራብ የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት መምሕርት ጠይባ ቱሪ መምሕር መሆኗ ፣ ወንጀሉን ለሊት ላይ መፈፀሟ እንደ ማክበጃ ታይቶ እጅ በመስጠቷ እና ቀደም ሲል መልካም ባሕሪ የነበራት በመሆኑ ግምት ውስጥ በማስገባት በ25 ዓመት እስራት እንድትቀጣ መወሰኑን ከምዕራብ አርሲ ዞን ፖሊስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።