የሻዕቢያና የትህነግ ወዳጅነት በየትኛውም ምድራዊ አመክንዮዎች ዛሬ ላይ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል በእርግጠኛነት የሚናገሩ አሉ። “በተመሳሳይ በፖለቲካ ቋሚ ነገር የለም” የሚሉ ወዳጅነቱ ብልጽግናን መብላት የሚያስችል ስምምነት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። ብልጽግና ደግሞ ሻዕቢያ ጦርነትን መርጦ ከጀመረ የሚያስበው ስለቀጣዩ የኤርትራ መንግስትና ስለካርታ ለውጥ እንጂ ሌላ ስጋት እንደሌለበት ነው።
ትህነግ የበረሃ ዘመኑን አገባዶ መንግስት ከሆነ በሁዋላ በይፋ ለሁለት ሲከፈል በይፋ ሲገለጽ እንደነበረው “ሻዕቢያ የትህነግ ስትራቴጂካል ጠላት ነው” የሚለው ዋንኛው የልዩነቱ ነጥብ ነበር። መለስ “ውህዳን” ብሎ የፈረጃቸው የትህነግ ስንጣቂ ክፍል በተደጋጋሚ በሚያወጣው ጽሁፍ ይህንኑ በመግለጽ የመለስን ቡድን “ከሃጂ” በሚል ፈርጆ ነበር።
ሻዕቢያን ማዕከል ያደረገው ልዩነት በትህነግ ሳሎን ውስጥ ዛሬ ድረስ አለ። ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ለሁለት የተከፈለው የትህነግ አንደኛው ወገን ከሻዕቢያ ጋር መግጠሙ በመረጃና ማስረጃ ይፋ እየሆነ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ጥምረቱ በአማራ ክልል ጠብ መንጃ ያነሱ የተወሰኑ አካላትን ያካተተ መሆኑ ደግሞ ከቀድሞ ይልቅ የአሁኑን አካሄድ ልዩ አድርጎታል።
በተራ ፕሮፓጋንዳ የሚከንፉ፣ ረጋ ብለው የሚመረመሩ፣ የቀደመውን ጥምረትና የጥምረቱ መክሰም የምያውቁ፣ ከሁሉም በላይ በሻዕቢያና ትህነግ መካከል ያለውን መርህ ላይ የተመሰረተ ልዩነት የሚያውቁ እየሰጡ ያለው ግምትና አስተያየት ለየቅል ነው። ሻዕቢያና ትህነግ አማራ ክልል ላይ ያላቸው የኖረ እምነትና “አማራን ነጻ እናወጣለን” የሚሉት ወገኖች ህብረትም በተመሳሳይ ቁልፍ ጥያቄ የሚነሳበትና ከሁለቱ ድርጅቶች መሰረታዊ መርህ አንጻር ሲቃኝ ውሃ እንደማይቋጥር እየተገለጸ ነው።
ሞሃመድ ኬይር ኦመር ትውልደ ኤርትራ ፣ በዜግነት ኖርዌጂያዊ ናቸው። አዲስ አበባና ካርቱም ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሞሃመድ በኖርዌይ የእንስሳት ህክምና ዶክተር ለመሆን ችለዋል። Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s በሚል ርዕስ የሱዳናዊውን ሰላይ ከሻዕቢያና ከትህነግ ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ጥምረት የጻፉት ዶክተር ሞሐመድ ጥምረቱ ሊሆን የማይችል እንደሆነ ይገልጻሉ።
እንደ ዶክተር ሞሐመድ እንደሚሉት ሻዕቢያ በመርህ ደረጃ አንድ የማይቀየር መርህ አለው። “ሻዕቢያ ትግራይ በምንም መልኩ ወደ ሱዳን የሚያስወጣ መውጫ ድንበር አይፍለግም። ይህ ለኤርትራ ስጋት ነው” የሚለው ይህ መርህ ለትህነግም ሚስጥር አይደለም።

ዶክተር ሞሐመድ ከሙያቸው ባሻገር በአፍሪካና አፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማሳተም ይታወቃሉ። በአስመራ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና የውሃ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ነበሩ። እ.ኤ.አ. ከ1977 እስከ 1979 ከኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር (ELF) ጋር የተቆራኘው የኤርትራ ተማሪዎች አጠቃላይ ህብረት (GUES) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ ነበሩ ። እ.ኤ.አ. በ 2000 ፣ በ 2000 ተፅእኖ ፈጣሪ “G 13” ቡድን ውስጥ ፣ ለኤርትራ ፕሬዝዳንት ግልፅ ደብዳቤ የፃፈ እና ለዲሞክራሲያዊ ለውጦች የሚደግፉ የኤርትራ ምሁራን ቡድን አባል ነበሩ።
ዶክተር መሐመድ በጉዳዩ ዙሪያ የተጨበጠ አስተያየት ለመስጠት አግባብነት ያላቸው፣ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርታር ያለውን መንግስት የማይደግፉ በመሆናቸውን በመግለጻቸው፣ ከምንም በላይ ሁለቱንም ድርጅቶች ከበረሃ ጀምሮ በወጉ ሰለሚያዉቋቸው፣ ከዚያም በላይ በአካባቢውና በቀተናው ዙሪያ ጥልቅ ተከታታይ ጽሁፍ የሚያዘጋጁ፣ አሁንም ንቁ ተሳትፎ ያላቸው በመሆኑ ኢትዮሪቪው አነጋግራቸዋለች።
“ትህነግ በሱዳን በኩል መውጫና መግቢያ በር ካገኘ ጡንቻው ይጠነክራል። ከሚፈልጋቸው አገራት ጋር በመገናኘት መሳሪያን ጨምሮ ድጋፍ ያገኛል። ይህ ደግሞ ለኤርትራ ስጋት ነው” በማለት የሚናገሩት ዶክተር ሞሐመድ፣ ይህን የቆየና በመርህ ደረጃ የሚታመንበትን ጉዳይ ሊያስቀይር የሚችል አንዳችም ጉዳይ እንደሌለ ያስረዳሉ።
አምባሳደር ቲያትር አገር መከላከያ ሚኒስትር ይሰሩ የነበሩ አንድ ከፍተኛ መኮንን ከምርጫ 97 በሁዋላ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው ሻዕቢያ ላይ ከበረሃ ጀምሮ የነበረውን ልዩነት ገልጸው ነበር። ልዩነቱም “ሻዕቢያ ስትራቴጂካል ጠላታችን ነው” በሚሉና አሁን ድረስ ከሻዕቢያ ጋር እንደሚገናኙ በግልጽ የሚነገርላቸው አዛውንት የትህነግ ዋና መሪዎች መካከል ነበር። እንደ መኮንኑ ገለጻ እነዚህ የሻዕቢያ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ኢትዮጵያን ዋጋ ያስከፍሏታል።
የመለስ ዜናዊ የግል ጠባቂ/አጃቢ የነበረው ሚኪ /ራያ/ ““መለስ ዜናዊ መዝናናት ሲፈልግ ወደ አስመራ ይመላለስ ነበር፤ በረራውም Unofficial በረራ ነበር” በማለት የመከላከያውን መኮንን የቆየ ምስክርነት ያጸናል። ።
ራያ ሰሞኑን በሰጠው መረጃ “መለስ ዜናዊ ከስራ ውጪ መዝናናት ሲፈልግ አስመራ ነበር የሚሄደው። የራሱን ሰዎች ብዙም አይቀርባቸውም ነበር። እኔ ቢያንስ ለሦስት ጊዜ ያህል ከሱ ጋር ወደ አስመራ unofficial በረራዎችን አድርገናል። ኢሳያስና መለስ በሁለት አገሮች ውስጥ ያሉ ወንድማማቾች ይመስሉ ነበር። በቃ በሁለት አገር ያሉ ሁለት ዳይናስቲዎች ነበሩ ማለት ትችላለህ። Scary ነው ግን እውነታው እሱ ነበር”
ይቀጥልና የባድመ ወረራ ያስከተለውን ጦርነት ጠቅሶ “ጦርነቱ ተጀምሮ በሁለቱም ወገን ያለው ወታደር በተጋጋለ ተኩስ ውስጥ ተጥዶ እያለ እሱ ወደ አስመራ ሄዶ ነበር” ሲል የክህደት ፋይል ይክትበታል። በዘመቻ ጸሃይ ግባት የአገር መከላከያ ሰራዊት ድል እያስመዘገበ ወደፊት ሲገሰግስ አቶ መለስ አስመራ መሄዳቸው ብቻ ሳይሆን፣ በመጨረጫው ሰዓት የተፈጠረውን ራያ “በወቅቱ ከመለስ ጋር የሄደውና ከውጪ ሆኖ ሲጠብቅ የነበረ ታጋይ (አሌ ይባላል) ጭቅጭቅ ሰምቶ ወደ ውስጥ ሲገባ ኢሳያስ መለስ ዜናዊን “ጨምላቃ” ብሎ ሲሰድበው ሰምቷል። መለስም ጭንቅላቱን እንዳዘቀዘቀ ድምፅ ሳያሰማ ስድቧን ጠጥቷታል!” ይህን የሚያጣቅሱ አቶ ኢሳያስ የሚታመኑም እንዳልሆነ በመጠቆም ትህነግ አሁን ላይ በጀመረው ወዳጅነት ይሳለቃሉ።
ኢሳያስ ሊታመኑ አይችሉም
ዶክተር ሞሐመድ እንደሚሉት ኢሳያስ በምስራቅ አፍሪቃም ሆነ በኢትዮጵያ አውራ መሆን ይፈልጋሉ። በዚህ የማይቀየር መርሃቸው የተነሳ በጋራ መርህ ላይ የተመሰረተ ወዳጅ የላቸውም። ከጅቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከየመን፣ ከኢትዮጵያ ተጣልተዋል። ተዋግተዋል። ከለውጡ በሁዋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ያልተግባቡትም በዚሁ ባህሪያቸው ነው።
ሁለቱንም እንደማይደግፉ ገልጸው ለወደፊት ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲቋቋም የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ አብረው እንደሚዘልቁ የሚያወሱት ዶክተር ሞሐመድ፣ “ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ሲቀርቡ ኢሳያስ ያሰሉት ስሌት አብይ ልምድ የሌላቸው፣ ልጅና ለስልጣን እንግዳ በመሆናቸው እንዳሻቸው ለመንዳትና አፍሪቃ ቀንድ ላይ አውራ ለመሆን ነበር። ግን አልሆነም”
ቀደም ሲል ከነበራቸው ልምድ በመነሳት እርግጠኛ ሆነው እንደሚናገሩት የኢሳያስ አፉወርቂና የትህነግ ጥምረት የአንድ ሰሞን ነው። በፍጹም ወደፊት አይቀጥልም። ከሻዕቢያ መርህ በተጨማሪ ትግራይ ውስጥ የሚሰማው የሕዝብ “ጦርነት አንፈልግም” ስሜት ሌላው ግንኙነቱን ውጤት አልባ የሚያደርግ ትልቅ ጉዳይ ነው።
ያገናኛቸው ጊዜያዊ ጉዳይ እንደሆነ በማመልክት፣ በቅርቡ ሻዕቢያ የተሳተፈበትን ጦርነት ዶክተር ሞሓመድ ያነሳሉ። “የኤርትራ ሰራዊት ብዙ ግፍ ፈጽሟል። ይህን ግፍ የትግራይ ህዝብ በቀላሉ አይረሳም” በማለት ትህነግና ሻዕቢያ የጀመሩት የማይዘልቅ፣ መርህ አልባ ግንኙነት የማይቀጥለበትን አጋዥ ምክንያት ያክላሉ።
ቀደም ሲል የነበረውን የበረሃ ስምምነት አጣቅሰው ሻዕቢያ እንደማይታመን የገለጹት የአገር መከላከያ ከፈተኛ መኮንና ታጋይ፣ ሻዕቢያ በትግራይ ላይ ያለው አቋምና ሲከተለው የነበረው አቅጣጫ ግልጽ በሚባል ደረጃ ጸረ ትግራይ፣ ጸረ ኢትዮጵያ ነው።
የሻዕቢያና የፋኖ፤ የፋኖና ትህነግ ህብረት
አቶ ጌታቸው ረዳ “የሰሊጥ ፖለቲካ” እያሉ ሲያቃልሉት የኖሩት፣ አሁን በቅርቡም “አንጃ” ያሉትን ኃይል በተመሳሳይ ሰሊጥ ናፋቂ እንደሆነ የሚጠቅሱት የወልቃይት ተገዴ ሁመራን መሬት ነው። ይህ የማንነትና የባለቤትነት ጥያቄ ያልተለየው አካባቢ በመላው አማራ ህዝብ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ወዘተ ሳይለይ አንድ አቋም የተያዘበት ነው። በትግራይ ስር ከገባበት ጊዜ ጀምሮም አቤቱታና ክስ ያልተለየው ግን በህጉ መሰረት ምላሽ ሳይሰጠው ወይም መላ ሳይበጅለት የኖረ ጉዳይ ነው።
በተመሳሳይ ለትህነግ ቁልፍ ጉዳያና ወደፊት አንቀጽ 39 ሲመዘዝ እንደ አገር ከሌሎች አገራት ጋር የሚገናኙበት መተንፈሻ በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ የመግብና የኤክስፖርት ምርት የሚዝቁበትም ስለሆነ በመላው የትግራይ ተወላጅ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል።
ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ ወልቃይት ተገዴ ሁመራ ሙሉ በሙሉ ቀደ ሲል “ያለፈቃዳችን ተነጠቅን” በሚሉ የአካባቢው ተወላጆችና አማራ ክልል ስር ነው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የአማራ ኃይሎችና የትህነግ ግንባር መግጠም ጥያቄ ሆኖ የሚነሳው።
የለውጡ ሰሞን ከኤርትራ ወደ አዲስ አበባ ለስራ ተልኮ ስራውን ሲጨርስ ወደ አስመራ ሳይሆን ዱባይ ገብቶ ኑሮውን የቀጠለው የኢትዮሪቪው ተባባሪ October 7,2024 ባተመነው ዜና “ብታምንም ባታምንም ሻዕቢያ ከወያኔ በላይ ወልቃይት ጠገዴን ይፈልጋል” ብሎ ነበር። ለጥንቃቄ ስሙ የተቀየረውና ሙሴ፣ ስማቸውን ያልጠቀሳቸው በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ የፋኖ ታጣቂዎች ከሻዕቢያ ጋር በጀርባ ውል ማሰራቸውን አመልክቶ ነበር። ይህ መረጃ ሻዕቢያ አልሳካ ብሎት እንጂ ወልቃይትን ይከጅል እንደነበር ለነበረው ሃሜት ደጋፊ ማስረጃ ይሆናል።
(Testimonials of a Sudanese Intelligence Officer on the Proxy war between Sudan and Ethiopia from 1970s to early 1990s) በሚል ርዕስ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል በነበረው የውክልና ጦርነት ትልቁን ሚና የተቻወቱትን ሱዳናዊ ሰላይና ዲፕሎማት አል ፋትህ ኢርዋን /Al Fateh Irwa / አስመልክቶ ዝርዝር መረጃ የሰጡት ዶከተር ሞሓመድ “ ኢሳያስ ወልቃይት ላይ የጸና አቋም አላቸው፤ ትህነግም ወልቃይት ላይ የጸና ይህልውና የሚለው አቋም አለው። ከአማራም ወገን በተመሳሳይ የማይቀየር አቋም አለ። ስለዚህ ስብስቡ ፈራሽ ነው” ባይ ናቸው።
እሳቸው ሙሉ ታሪኩን የጻፉለት ሱዳናዎ ሰላይ አል ፋትህ መቀለ ከኢሳያስና መለስ ዜናዊ ጋር እራት ሲበላ ያጋጥምውን እንደማሳያ በመጠቀም በሰጠው ምስክርነት “ኢሳያስ ለአማራ ሕዝብ ያለው ጥላቻ መረን የለቀቀ ነው” የሰጡት ምስክርነት ሌላው የሻዕቢያና የአማራ ኃይሎች ጥምረት የማይቀጥል ለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ኢሳያስ አፉወርቂ በውል የተስማሙትና ግንባር የገጠሙት በየትኛው አካባቢ ካለው የፋኖ አመራሮች ጋር እንደሆን እያደር ይፋ መሆኑ፣ ከትህነግ ጋርም ግንባር የገጠሙት መታውቃቸው፣ ራሳቸው ሳይቀር በኩራት መናገር በመጀመራቸው ሊደበቅ አይችልም። አሁን ጥያቄው ያለው “ የአማራ ኃይሎች ነን የሚሉት አካላት ከትህነግ ጋር ግንባር ሲገጥሙ የወልቃይት ጸገዴ ሴቲት ሁመራን አስመልክቶ ምን ተስማሙ?” የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው።
በቅርቡ “የፕሪቶሪያው ስምምነት ዳግም እንዲታይ እንፈልጋለን” በሚል መግለጫ ከሰጠ በሁዋላ “ የሻዕቢያን አቋም መድገሙ ምን ፈልጎ ነው? እነሱ ካነሱት ጥያቄ ጋር የፕሪቶሪያው ስምምነት ምን ግንኙነት አለው” የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ይህን የሰሙ “ ሻዕቢያ አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲ ውስጥ ያስቀመጣቸው ሰራተኞቹ ባህር ዳር ቢሮ ከፍተው ነበር” የሚለውን ጥቆማ የሚያጎላ ይሆናል።
እንደ መውጫ
ሻዕቢያ ወልቃት ላይ የያዘው ከላይ የተገለጸው አቋሙ ሁሌም ከትህነግ ተጻራሪና በመርህ ደረጃ የታተመበት ነው። ትህነግ ወልቃይትን ሊደራድርበት የማይፈልገው “ህልውናዬ” የሚለው የአንቀጽ 39 መፍቻ ቁልፍ አጀንዳው ነው። የአማራ ክልልም ሆነ አሁን ላይ “የተከዜ ዘብ ” ሰፊ ሰራዊት አሰልጥኖ “ወልቃይት ወይም ሞት” ብሎ በተጠንቀቅ ቆመዋል።
የፌደራል መንግስት “ቅድሚያ የተፈናቀሉ ይመለሱ፤ ኖርማላይዝ ይደረግና ህዝብ ወደፊት ይወስናል” የሚል አቋም አለው። የእነ ደብረጽዮን በተቃራኒ የቆመው የአቶ ጌታቸው ቡድን “ተፈናቃዮች አስቅድመው ይመለሱ” የሚለውን አቋም በማራመድ፣ የትጥቅ ማስፈታቱን በመቀበል፣ በወልቃይት ጠገዴ የሰፈሩ ታጣቂዎች እንዲወጡ ይጠይቃል። በጦርነትና በስደት የተጎዳው ሕዝብ ወደ ቄዬው መመለስ ይመኛል።
ህብረት ፈጣሪዎቹ፣ ኮማንዶ እንዲሰለጥላቸው የሚጠይቁትን ጨምሮ እርስ በእርስ የሚያግባባ አንድም የጋራ ነጥብ እንደሌላቸው የሚናገረው የጀርመኑ ነዋሪ “ ይህ ቅዠት ኢሳያስን በደንብ ካለመረዳት የመነጨ ነው። ኦነግ ከሃያ ዓመት በላይ ኤርትራ ከትሞ ስድስት ሆኖ ተበጣጥሶ ነው የወጣው፣ ሻዕቢያን ከተገናኘ በሁዋላ ትህነግ ሁለት ቦታ ተክፍሏል። አማራው የተበትተነ ነው። ዓላማው ኢትዮጵያን ማተራመስ እንጂ ሌላ ውጤት እንዲያመጣ ታስቦ አይመስልም። ይህም የሻዕቢያ አጀንዳ ነው። ይህ ሻዕቢያን ካለመረዳት የመነጨ ነው።” ሲል ጥቅል አሳቡን ይሰጣል።
ሰማኒያን የዘለቁት አንጋፋው የኤርትራ መሪ ከግብጽ ጋር ብቻ ቋሚ ወዳጅ መሆናቸው በአባይ ወንዝ ሳቢያ ግብጽ ባላት የማይለወጥ ኢትዮጵያን የማበራየት ዕቅድ መስረተ ነው። ይህንኑ በመጠቀም ምስራቅ አፍሪቃ ላይ አውራ መሆን የሚፈልጉት አቶ ኢሳያስ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያገኙት ምላሽ አልተመቻቸውም። “ትህነግ ከምድር ላይ መወገድ አለበት” በሚል በፕሪቶሪያው ስምምነት ያኮረፉት ኢሳያስ ግፍ የፈጸሙበትን ህዝብና ምድር ወኪል ነኝ የሚለውን የትህነግ አንድ ቡድን ይዘው፣ ፋኖን አክለው መንግስት ለመገልበጥ ይችሉ ይሆን?
ከመንግስት አካባቢ የሚሰማው ግን የተለየ ነው። ከኢሳያስ በሁዋላ ስለሚኖረው አዲስ የኤርትራ ካርታና አዲስ መንግስት ምስረታ ነው። ከመንግስት ወገን የሚድመጠው ሁሉም ሲድመር ኢሳያስን መንቀል ነው። አሁን ላይ አብዛኞች እንደሚሉት ሻዕቢያ እያለ ኤትዮጵያ ሰላም ልትሆን አትችልም። ያሉት ተሞክሮዎች በሙሉ ይህን ያረጋግጣሉ። “ኢትዮጵያን ልጋልባት፣ ኢትዮጵያን እንጋልባት። ኤርትራ የግል፣ ኢትዮጵያ የጋራ” የሚባለው መርህ አልባ ግንኙነት መስመር ሊበጅለት ግድ ነው። ጥሩ ጉርብትና፣ መልካም ወዳጅነት። በህግ አግባብ ተከባብሮና ህግን አክብሮ መኖር።