” ለውይይት በራችንን ከፍተን እየጠበቅን ነው ” – ገቢዎች ቢሮ
” ለመነጋገር ዝግጁ ነን ” – ማኅበራቱ
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በኢትዮጵያ የሂሳብ እና የኦዲት ቦርድ ፈቃድ ከተሰጣቸው 863 የሂሳብ ባለሙሞያዎችና ኦዲተሮች ያቀረቡት የሂሳብ ሪፖርት በማሳነስና በመሰወር የቀረበ ነው ሲል ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ፍቃድ መንጠቅ የደረሰ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቋል።
” የገቢ ግብርን በማሳነስና በመሰወር የተሳሳተ የሂሳብ ሪፖርት አቅርበውልኛል እርምጃ ይወሰድባቸው ” ብሎ በሚዲያ ያስተላለፈው መረጃ የኦዲተርነት ሙያን ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ መክተቱን የሂሳብና የኦዲተሮች ማህበራት ተናግረዋል።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከወንኩት ባለው የቅድመ ኦዲት ስራ ” ባለፈው ዓመት ብቻ 36,729 የታክስ መዝገቦች ገቢ በማሳነስና በመሰወር የሚቀርቡ መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ” ብሏል።
በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ የሂሳብ እና የኦዲት ቦርድ ፈቃድ ከተሰጣቸው 863 የሂሳብ ባለሙሞያዎችና ኦዲተሮች 824ቱ ባለሞያዎች ያቀረቡት የሂሳብ ሪፖርት በማሳነስና በመሰወር የቀረበ በመሆኑ፤ በቦርዱ ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ፍቃድ መንጠቅ የደረሰ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ቢሮው ጠይቋል።
ይህን ተከትሎ 3 የሂሳብና የኦዲተሮች ማኅበራት ተፈፀመ የተባለው ስህተት በቦርዱ ሳይረጋገጥ መረጃው በሚዲያ መተላለፉ አግባብነት የሌለውና ሙያውንም ኪሳራ ውስጥ የከተተ ነው ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫቸውም ” ባለሙያዎቹ ይቀጡልኝ ” የሚለው ጥያቄ ላይ ምንም ቅሬታ እንደሌላቸው ጠቅሰው ይሁንና በሚዲያ የተላለፈበት አግባብ አሳሳች የነበረ በመሆኑ መረጃው ከሚዲያዎችና መረጃ ቋቶች ላይ እንዲወርድ ጠይቀዋል።
ይህንንኑ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውንና በጉዳዩ ዙሪያ ለመነጋገር የገቢዎች ቢሮን በደብዳቤ መጠየቃቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች ማህበር፣ የውጭ ኦዲተሮች ማህበርና የአካውንቲንግ ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ ማህበር ናቸው።
በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ምን ምላሽ ሰጠ ?
በአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ለውይይት ለመቀመጥ የማህበራቱን ህጋዊ እውቅና እና የአባላት ዝርዝር በህጋዊ መንገድ እንዲቀርብለት ጠይቋል።
የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ሰውነት አየለ ለማኅበራቱ አመራሮች በስልክ በመደወል ህጋዊ እውቅናቸውን እንዲያቀርቡ ነግረናል ያሉ ሲሆን ለውይይት በራችንን ከፍተን እየጠበቅን ነው ሲሉ ለሸገር ኤፍ ኤም ተናግረዋል።
ቢሮው 863 የሂሳብ ባለሙያዎች ይቀጡልኝ ሲል ለኢትዮጵያ የሂሳብና የኦዲት ቦርድ ማቅረቡን ተከትሎ በሚዲያ የወጣው መግለጫ በተመለከተ፥ አቶ ሰውነት በስም ዝርዝር የተነሳ የለም በማለት የተሰራው ስራ በአዋጅ በተቀመጠው መሰረት እንደሆነ አስረድተዋል።
አክለውም ” እስካሁን በስም ዝርዝር ያወጣነው ነገር የለም ያሉ ሲሆን 490 የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጥልን 333 ደግሞ ፈቃዳቸው ይሰረዝ 39ኙ እውቅና ይሰጣቸው ያልነው በደፈናው ነው ” ብለዋል።
ማጣራቱ ከተጠናቀቀ እና ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በስም ዝርዝር ይፋ እንደሚደረግም አቶ ሰውነት አየለ ተናግረዋል።
ማኅበራቱ በቢሮው ምላሽ ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ምንድነው ?
ማኅበራቱ ” በደብዳቤ ለጠየቅነው ጥያቄ በደብዳቤ ምላሽ አልተሰጠንም ” ያሉ ሲሆን በስልክ ቅድመ ሁኔታውን እንዲያሟሉ እንደተነገራቸው እና መቼ እንደሚወያዩ ቀጠሮ እንዳልተሰጣቸው ለሸገር ኤፍ ኤም ገልፀዋል።
የውጪ ኦዲተሮች ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ማሞ ለሁለቱ ማህበራት ፕሬዚዳንቶች ” እውቅናን እና የአባላትን ዝርዝር በህጋዊ መንገድ አረጋግጣችሁ አምጡ ” የሚል ቅድመ ሁኔታ በስልክ እንደተነገራቸው አረጋግጠዋል።
የማህበራቱን እውቅና ማረጋገጫ ማቅረብ እንደሚቻል ” የማህበራቱን አባላት ዝርዝር ግን ይዞ መቅረብ አስፈላጊ ሆኖ አላገኘነውም ” ብለዋል።
በተጨማሪ አቶ ሚሊዮን ” ‘ ህጋዊነታችሁን የሚያረጋግጥ ዶክመንት በዚህ ቀን ይዛችሁ ኑ እና እንወያይ ‘ የሚል ሃሳብ አልተሰጠም ” ያሉ ሲሆን ” በደብዳቤም በፅሁፍም ምንም ነገር አልተባለም ” ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ሚሊዮን፥ ቀን እና ቦታው ከተነገራቸው ማኅበራቱ ህጋዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ዶክመንት ይዘው ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ጣቢያ ነው።
Via ShegerFM102.1
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter