ቅዱስ ሲኖዶስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ገብርዔል “አትደንግጡ፣ ማርያም የዓለም ቤዛ አይደለችም!” ማለታቸውን ተከትሎ ስብሰባ ተቀመጠ።ውሳኔ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ ሁሉም የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በምልዓት በተገኙበት ለአርብ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ቀጠሮ ያዘ።
ብጹዕ አቡነ ገብርዔል አርብ ዕለተ ስቅለትን አስመልክተው በፎኖተ ጽድቅ ቴሌቪዥን “የሰባ ግብዣ” በሚል የትምህርት ርዕስ ሰብከው ነበር። በዚሁ የክርስቶስን ሞትና ትንሳዔ ላይ የተንተራሰ ትምህርት ስለ መለዓክት አዳኝ አለመሆናቸውን አብራርተዋል። አያዘውም “አትደንግጡ። ማርያም የዓለም ቤዛ አይደለችም” ብለዋል።

“የሞት አለቃው የሞተው በኢየሱስ ብቻ ነው” በማለት የዕብራዊያንን ወንጌል ጠቅሰው ያለፉት በጹዕነታቸው፣ አክለውም ሰውን ማዳን የቻለ ማንም አልነበረም ሲሉ በርካታ ሰዎች ይከራከሩበታል ያሉትን የመለዓክት ጉዳይ ዘርዘሩ።
መለዓክት በብሉይ ዘመን የጸለዩት ጸሎት፣ ያቀረቡት ማስዋዕት፣ አምልኳቸው ወዘተ እንኳን ሌላውን ሊያድኑ እነሱን ሊያድናቸው እንዳልቻለ መጽሃፍ እየጠቀሱ አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ገብርዔል ይህን ካሉ በሁዋላ “ሰውን ማዳን የሚችለው ሰሪው ብቻ ነው” ሲሉ ሞትን ድል የተነሳውን ኢየሱስን አገነኑ።
ኤየሱስን ከጸሃይ ጋር አያዘው “ እኛ ከቸረቃ ወይም ከከዋክብት ጋር አንጨቃጨቅም” ሲሉ የሁሉም ዓይን ዋና ጸሃይ ላይ ሊሆን እንደሚገባው አስተማሩ። በዚሁ መንደርደሪያ ስለ “ቤዛ”አነሱ።
“ሮሜ 8:11 ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል” የሚለውን ጠቅሰው ይህ እንደ ክርክር ሊቀርብ እንደማይገባ እግረመንገዳቸውን ጠቁመው ገላትያን 3.13ን ጠቅሰዋል።
“ዕብራውያን 9÷11- 12 ላይ፣ “ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በኮርማዎች ደም አይደለም’ ተብሎ ተጽፏል። ሚካኤል ቤዛ መሆን አይችልም፣ ገብርኤል ቤዛ አልሆነም፣ አብርሃምም ቤዛ አልሆነም፣ የትኛውም ፍጡር ቤዛ አይሆንም። ቤዛችን ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ እመቤታችን ማርያም አይደለችም። …” ብለዋል።
የቤተክርስቲያኗ የሕዝብግንኙነት ባሰራጨው ዜና ሲኖዶሱ አቡነ ገብርዔል ባሰተላለፉት የወንጌል ትምህርት ላይ ቀድሞ ባልተለመደ መልኩ ቅድስት ድንግልን ማሪያምን አስመልክተው የሰጡትን ትምህርት በተመለከተ ውይይት አድርጓል።
ቋሚ ሲኖዶስ ዛሬ ማለዳ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ በብፁዕነታቸው የተላለፈውን ትምህርት ዝርዝር ሁኔታ በመመርመር ሁሉም የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በምልዓት በሚገኙበት ውሳኔ ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድሁሉም ለአርብ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ቀጠሮ መያዙ ታውቋል።
“ቤዛ መሆንና ማዳን የሚችለው ሠሪው፣ ፈጣሪው የእግዚአብሔር ልጅ እንጂ ፍጡር አይደለም። ፍጡር ፍጡርን ማዳን አይችልም” በማለት ብጽዕነታቸው “አትደንግጡ ማሪያም ቤዛ አይድለችም” ላሉት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
“ታላቁ ነቢይ ኢሳያስ ስለ ቤዛነት ሲናገር፣ [የተናገረውን በግዕዝ ጠቅሰዋል] በመልዓክ አይደለም፣ በአማላጅ አይደለም፣ እርሱ ራሱ የእግዚአብሔር ልጅ መጥቶ ያድናቸዋል ይላል። ለዘላለም ወደዳቸው፣ ተሸከማቸው ብሏል” በሚል ሲያስረዱ ተሰምቷል።
ብጹዕ አቡነ ገብርዔል አክለው “ፍጡር ቤዛ መሆን አይችልም። ቤዛ ማለት ስለ ሌላው ተላልፎ መሠጠት ማለት ነው። ‘ነይ ነይ እምዬ ማርያም፣ ቤዛ ነሽ አሉ ለዓለም’ ይባላል። ነገር ግን እመቤታችን ቤዛ አይደለችም፤ አትደንግጡ ቤዛ ልጇ ነው። ቤዛችን ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ነው” ሲሉ ዝርዝር ማጣቀሻና ማስረጃ ያሉትን አስተምረዋል።
የቤተክርስቲያኗ የሕዝብግንኙነት ቋሚ ሲኖዶስ ይህን በማስተማራቸው ስብሰባ መቀመጡን ከመግለጹ ውጭ በዝርዝር በምን በምን ጉዳይ ውይይት እንደተደረገ አላብራራም።
ብጹዕ አቡነ ገብርዔል “አትደንግጡ፣ ማርያም የዓለም ቤዛ አይደለችም” በማለት ማስተማራቸው እንደተሰማ ምስላቸውና ስለ ማሪያም የተናገሩት እየተነቀሰ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አውዶች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የነቀፏቸው እጅግ በርካታ ሲሆኑ “ቤዛ” ማለት ያልገባቸውና ከተረዱ በሁዋላ ስብከቱን የወደዱም ታይተዋል።
በሌላ ወገን የፕሮቴስታንት ተከታይ ነን የሚሉ “አትደንግጡ፣ ማርያም የዓለም ቤዛ አይደለችም!” ማለታቸውን ሰባኪው ካቀረቡበት አውድ ውጭ በመጠቀም ተራ የብሽሽቅና የልዩነት ማሳያ አድርገው ሲጠቀሙበት ታይቷል።
ብጹዕ አቡነ ገብርዔል “ፈጣሪ እንጂ ተፈጣሪ አያድንም” ሲሉ ስለ መለዓክት ሚናም በስበከታቸው አጉልተው አሳይተዋል። “እኔ ህይወትም መንገድም ነኝ” ሲል ኢየሱስ መናገሩ ለፍጡራን ሁሉ መሆኑን ባማሳየት ተፈጣሪዎች ራሳቸውን ማዳን የማይችሉ እንደሆነ ገልጸዋል።
ቋሚ ሲኖዶስ በጉዳዩ ዙሪያ መክሮ ምን እንደሚወስን የታወቀ ነገር የለም። እሳቸውም የሲኒዶሱን መሰብሰብ አስምለክቶ ይህ እስከተሳፈ ድረስ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
“የሰባ ስጦታ” የሚለው ትምህርታቸው እዚህ ላይ ይመልከቱ
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter