የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ፖሊስ “በሽብር ወንጀል ጉዳይ ጠርጥሬያቸዋለሁ” ባላቸው አራት የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች ላይ የ14 ቀናት የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ። ባለፈው አርብ ፍርድ ቤት ከቀረቡ የጣቢያው ሰራተኞች መካከል፤ የካሜራ ባለሙያ የሆነው አቶ ቶማስ ደመቀ ከእስር ተለቅቋል ተብሏል።
የአቶ ደመቀን ከእስር መለቀቅ ከፖሊስ የምርመራ ምዝገባ መረዳቱን የገለጸው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ነው። ችሎቱ የኢቤኤስ ሰራተኞች የተካተቱበት የ8 ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ መመልከት የጀመረው ባለፈው አርብ መጋቢት 19 ነበር።
የፌደራል ፖሊስ ለችሎቱ ባቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማመልከቻ ላይ በተጠርጣሪዎቹ ላይ እያካሄደ ያለውን ምርመራ “በሰው እና በሰነድ ማስረጃ በስፋት ለማጣራት” የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ነበር። ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በዛሬው ዕለት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ከመስጠቱ አስቀድሞ፤ የፖሊስ ጅምር የምርመራ መዝገብ እንዲቀርብለት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ችሎቱ ዛሬ ሰኞ ከሰዓት በነበረው ውሎው፤
ተጠርጣሪዎቹን በሽብር ወንጀል ለመጠርጠር አመላካች የሆኑ ነገሮች ከፖሊስ ምርመራ መዝገብ ተመልክቼያለሁ ብሏል። የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች፤ ደንበኞቻቸው ቢጠረጠሩ እንኳን “የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ስር ባሉ ድንጋጌዎች” እንደሆነ ያቀረቡት መከራከሪያ “የተፈጸመ ጥፋት መኖሩን” የሚያሳይ እንደሆነ ችሎቱ ጠቅሷል።
ምንጭ ኢትዮጵያን ኢንሳይደር