የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በከተማዋ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የሚከለክለውን መመሪያ በማገድ ያስተላለፈውን ውሳኔ የዞኑ ማዕከላዊ ፍርድቤት ማጽናቱ ተገለጸ።
የአክሱም ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ የተከሳሾች አስተዳደራዊ ትእዛዝ ወይም ውሳኔ መዝገቡ እልባት እስኪያገኝ ወይም ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ በጊዜያዊነት ታግዶ እንዲቆይ ማዘዙ ይታወሳል።
አዲስ ስታንዳርድ ፍርድ ቤቱን ጠቅሶ “የተላለፈው አስተዳደራዊ ውሳኔ ታግዶ ካልቆየ በእስልምና እምነት ተማሪዎች ላይ የማይመለስ የሰብአዊ እና የሞራል ጥሰቶች ሊያስከትል ስለሚችል ተከሳሾች ያስተላለፉት አስተዳደራዊ ውሳኔ በፍታብሔር ህጉ እና በፌደራል የስነስርአት አዋጅ መሰረት እልባት አስኪያገኝ ወይንም ደግሞ ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ እንዳይፈጸም ታግዶ እንዲቆይ” ማለቱን አስታውሷል።
በዚህም መሰረት የክልሉ ማዕከላዊ ዞን ማዕከላዊ ፍርድ ቤት የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት ያሳለፈው የእግድ ውሳኔ እንዲጸና ትዕዛዝ ማስተላለፉን የትግራይ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባጋራው መረጃ አስታውቋል።

በወረዳው ፍርድ ቤት የታገደው የትምህርት ቤቶቹ አስተዳደራዊ ውሳኔ እስከዛሬ በትምህርት ቤቶቹ አለመተግበሩ እና ተማሪዎቹ መማር አለመቻላቸውን ከትግራይ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ምክር ቤቱ በማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ “የማዕከላዊ ፈርድ ቤቱ ያጸናውን ውሳኔ ይተገብሩት ይሁን አይሁን የምናየው ይሆናል” ብሏል።
የዞኑ ማዕከላዊ ፍርድ ቤት በተጨማሪ ካሳለፋቸው ወሳኔዎች መካከል የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ክሱን ወደሚመለከተው ከፍተኛው ፍርድ ቤት እስደዋለሁ በማለቱ የአክሱም ወረዳ ፍርድ ቤት የ12 ሺ 500 ብር ቅጣት ብይን ማስተላለፉን የተመለከተው ይገኝበታል።
የዞኑ ማዕከላዊ ፈርድ ቤት በሰጠው ብይን “በወረዳው የተጣለውን ቅጣት አግባብነት እንደሌለው በመግለጽ እና ውድቅ በማድረግ ገንዘቡ ለምክር ቤቱ እንዲመለስ አዟል።
በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የ12ኛ ክፍል ሙስሊም ተማሪዎች የብሔራዊ ፈተና የኦንላይን ምዝገባ ለማከናወን “ሂጃብ እንዲያወልቁ” መጠየቃቸው ባለመቀበላቸው የምዝገባ ቀኑ እንዳለፋቸው መግለጻቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።
በተጨማሪም በአክሱም ትምህርት ቤቶች የተደረገውን የሂጃብ እገዳን በመቃወም በክልሉ ርዕሰ ከተማ በመቀለ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታደሙበት ሰልፍ መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።