ትህነግ የመጨረሻ ምሽጉ አድርጎ ሲንከባከበው የነበረውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአፈ ጉባዔነት ሲመሩ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሒም “በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ሞጋች ማኅበረሰብ ተፈጥሯል፤ ወንበሩን ብረት ምጣድ የሚያደርግ ትውልድ ተፈጥሯል” ሲሉ ደምድመዋል።

ከተራ አባልነት እስከ ስራ አስፈጻሚነት ማዕረግ ትህነግን ያገለገሉት ኬሪያ ኢብራሒም ከዚህ ድምዳሜ የደረሱት ከቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ሥራ አስፈጻሚ ድረስ ባለፉባቸው መንገዶች ሁሉ የደረሰባቸው፣ ያሳለፉትን፣ ያጋጠማቸውን፣ ያዘኑባቸውን፣ የታዘቧቸውን የተከማቹ ጉዳዮች በጥሞና ከመረመሩ በኋላ ነው። “በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ሞጋች ማኅበረሰብ ተፈጥሯል፤ ወንበሩን ብረት ምጣድ የሚያደርግ ትውልድ ተፈጥሯል” ያሉትም በዚሁ ጥልቅ ምርመራቸው ሲሆን፤ ይህ ድምዳሜያቸው እየፈረሰ ካለው የትህነግ አምልኮ እሳቤ ጋር የሚያያዝና ሚዛን የሚደፋ ሆኗል።
“እኛ (ትህነግ) ዓይን ነበረን እንጂ ጆሮ አልነበረንም፤ አመራሩ ስታክ አድርጎ ነበር፤ ጥያቄዎችን ከመመለስ ይልቅ ከፍተኛ የሆነ ንቀት፣ ቸልተኝነት፣ ምን ያመጣሉ ባይነት ውስጥ ነበርን። በተለይ መለስ ከሞተ በኋላ አሁን ድረስ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፤ አመራሩ ወደ ራሱ ክብርና ጥቅም ውስጥ የገባ ነበር” ሲሉ ቁጭት የተሞላበትን ግምገማቸውን አኑረዋል። በዚሁ በሽታ ሳቢያ “ጥያቄን ያነሳ ሁሉ ወደ እስር ቤት በመወርወር በሰድዶ ማሳደድ ውስጥ ነበርን” ሲሉ የውድቀቱን ምክንያት ይፋ አድርገዋል። ብዙዎቹ የተለመዱና ተደጋግመው የተባሉ ቢሆንም “ንቀት፣ ቸልተኝነት፣ ምን ያመጣሉ፣ ደፍረው አይነኩንም ወይም አይደፍሩንም” የሚል ትምክህት እንደነበር ከእሳቸው አንደበት መሰማቱ አሁን በትግራይ የተነሳውን የእሳቤ ለውጥ አጉልቶ የሚያሳይ ሆኗል።
በዚህ ተንደርድረው “የህወሃት አካሄድ ጸረ ዴሞክራሲዊያ ነበር፤ በአመራር መካከል መናናቅ ነበር፤ አለመከባበር ነበር” ሲሉ በተጎዳ መንፈስ የገለጹት ኬሪያ ኢብራሒም፣ በአመራሩ ውስጥ የነበረውና የአተያይ ልዩነት ያስነሳው ጥያቄ በሒደት እንዴት እያደገ እንደሄደ ሲያስረዱ፣ “ይህ በአመራሩ ውስጥ የተፈጠረ ችግር ወደ ትግራይ ሕዝብ ወረደ፤ ለምን የአንድ መሪ ሥራ ሕዝብን ተጠያቂ ያደርጋል፤ ለምን የህወሃት መሪ ስህተት የትግራይን ሕዝብ ተጠያቂ ያስደርጋል፤ ለምን እኛ ከማንም በላይ የሕገ መንግሥት፣ የብሔር ብሔረሰብ ቋሚ ጠበቃ ሆንን፤ ለምን ለነዚህ ጉዳዮች እኛ ብቻ ተሟጋች ሆንን ወይም ለምን ህወሃት ብቻ ሆነ” በማለት ጠይቀዋል።

ከስትራቴጂ አኳያ ማሰብ፣ ጊዜና ወቅትን ገምግሞ የሚመራ መሪ ከመለስ በኋላ ያጣው ትህነግ ከቀን ወደ ቀን በሁሉም አግባብ እየተሽመድመደ መሄዱን ሲያስረዱ “የነበረው አመራር ለተፈጠረው ችግር (የለውጥ እንቅስቃሴ) የምንመጥን አልነበርንም” በማለት ነበር። አመራሩ ከውስጥና ከውጭ ሲታይ የተለያየ ቀለም ያላቸው እንደሆኑ በማከል አገሪቱን የመምራት ብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ የሚግባባት አጀንዳ ያልነበረው ቡድንተኞች መሆናቸውን አመልክተዋል።
በወ/ሮ ኬሪያ ቃለ ምልልስ ወቅት ጸጥ ብሎ ለመስማት የተገደደው የርዕዮት ዩቲዩብ ባለቤት ቴዎድሮስ ያሳየው ጽሞና አስገራሚ ነበር። ትህነግን በሌላ በሆነ አንድ አጋጣሚ የተቹ፣ ያወገዙና ውድቀቱን ያጣደፉ ወገኖችን በመጋበዝ ማራከስ፣ መበቀልና ማዋረድ መለያው የሆነው ቴዎድሮስ ጣልቃ ከገባባቸው ውስን ጉዳዮች አንዱ ስለ መለስ ሲነሳ ነበር።
“የመለስ መሞት ችግሩን ያባባሰ ከሆነ by implication መለስ ብቁ መሪ አልነበረም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ተተኪ አላፈራም፤ ስለዚህ ተተኪ አለማፍራቱ የመለስን ብቃት ማነስ የሚያሳይ ነው” ሲል አከለ።
“ጦርነቱ ልናስቀር እንችል ነበር”
ወይዘሮ ኬሪያ አስደንጋጭ የሆነና የጠያቂያቸውን ቅንድብ ያወዛወዘ ጉዳይ አነሱ። ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል የነበረበትን ቀላልና ግልጽ አመክንዮ አቀረቡ። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የትግራይን ሕዝብ ከብቦ ለማጥፋት በያዘው አጀንዳ ምክንያት ነው ጦርነቱ የተነሳው” በሚል በተደጋጋሚ ወደ ዘር ማጥፋት ወይም ጄኖሳይድ ክስ የሚንደርደረው ቴዎድሮስን ያስደነገጠው የወ/ሮ ኬሪያ ምስክርነት የታጀበው እጅግ ቀላል በሆነ አመክንዮ በመሆኑ ቴዎድሮስ አጁን ባፉ እንደጫነ እንዲያደምጥ አስገድዶታል።
ወ/ሮ ኬሪያ “በህወሃት ውስጥ የነበረው ልዩነት፣ መናናቅ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። ለ፯ ዓመት ስናሰቃያቸው የነበሩትን ሕዝቦች ነው የፌዴራሊስት ኃይሎች ብለን መቀሌ ላይ ሰብስበን ከእኛ ጋር ሥሩ ያልናቸው። ሁሌ እናውቃለን፣ አይደፍሩንም፣ የትም አይደርሱም የሚሉ ፉከራዎች ነበሩ በግምገማችን” ካሉ በኋላ ይህ መደናቆር እንዴት ወደ ጦርነቱ እንደገፋቸው ያስረዳሉ።
“ምርጫ ብናራዝም እንችል ነበር፤ ለፌዴራል ዕውቅና ሰጥተን እኛም እንዲሁ ፌዴራል ሊሰጠን ይችል ነበር፤ ይህንን ብንከተል ጦርነት ልናስቀር እንችል ነበር” ሲሉ የትህነግ ሥራ አስፈጻሚ የትህነግን ሕግ ጥሶ ምርጫ ውስጥ የገባበትን ምሥጢር ይፋ አደረጉ። ሁሉም ነገር ሲወሰን በሥራ አስፈጻሚነት ወንበራቸው ተሳትፎ ያላቸው ኬሪያ ጦርነቱ ሊቀር የሚችል እንደነበር ገልጸው የሰጡት ምላሽ፣ ጦርነቱን አስመልክቶ ቀደም ሲል የተገነባውን የቴዎድሮስና የሌሎች ትህነጋውያንን ትርክት አክሽፏል። በአጭሩ ጦርነቱ የተፈለገበትን አግባብ የትህነግ ሥራ አስፈጻሚ ይፋ አድርገዋል። ይህ ምስክርነት “መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመናል” በማለት ሟቹ ሴኩቱሬ ከሰጠው ምስክርነት ጋር ሲጋመድ ታሪካዊ ሰነድ ሊሆን የሚችል ሆኗል።
ኬሪያ ኢብራሂም ጦርነቱ ያደረሰውን ውድመትና ጥፋት በሚያሳዝን መልኩ ማሰብ ለሚችሉ ሁሉ ሲያስረዱ “ምርጫውን በአንድ ዓመት ብናራዝም ጦርነት ይቀር ነበር፤ ወይም ጊዜ ለመግዛት ዕድል ይሰጠን ነበር” ሲሉ አመራሩንና ግብሩን ሳይሸሽጉ ይፋ ተናግረዋል።
ስለ ሻዕቢያ ጣልቃ ገብነት
ሻዕቢያ የሚባለውን ወንጀለኛ ወደ ትግራይ የጋበዘው የፌደራል መንግሥት እንደሆነ ለሚከሱ ብዥታ ማጥሪያ ይሆን ዘንድ ኬሪያ ምላሽ ሰጥተዋል። “በነበረን ግምገማ ሁሉ የነበረን ዓቋም አስፈጻሚውን ሳይሆን ላኪውን መምታት ነው በሚል ሻዕቢያን በደንብ ነበር የገመገምነው” ሲሉ የትህነግ ሥራ አስፈጻሚ ሻዕቢያ ለወረራ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር ሙሉ በሙሉ እንደሚታወቅ መስክረዋል።
“እኛ በዚህ ልክ ሻዕቢያ ወደ ትግራይ ገብቶ ጥቃት ይሰነዝራል ብለን አልገመትንም ነበር፤ ጠንቋይ አይደለንም” በማለት አቶ ጌታቸው ያድበሰበሱትን ሃቅ ይፋ ያወጡት ኬሪያ ኢብራሒም፣ “ሰሜን ዕዝን መቱት። ሳያስብ በተኛበት በክህደት አረዱት። ከዚያ ጦርነቱ ሲነሳ ሻዕቢያ ጊዜ ይጠብቅ ስለነበር፣ የሚከላከልው ጦር በክህደት መመታቱን ተከትሎ ትግራይን ወረር። ተጠያቂው 22 ዓመታት ምሽግ ውስጥ የነበረውን ሰሜን ዕዝን ደፍሮ ጠላት እንዲፈነጭ ያደረገው አካል ነው” የሚል መከራከሪያ ለሚያቀርቡት ኬሪያ መልስ ሆነዋል።

“የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት የተፈጠረ አድርገን ነው የምናስበው” በማለት ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ይከተሉ እንደነበር የገለጹበት አግባብ “ጦርነት ባሕላዊ ጫወታችን ነው” በማለት የትግራይን ወጣት ሲያስጨርሱ ከነበሩት እንደ አሉላ ዓይነቶች ቅስቀሳ ጋር የሚመሳሰል ሆኗል።
“የሰው ዋጋ ከምንከፍል የጊዜ ዋጋ ብንከፍል ይሻል ነበር፤ ይህንን አሟጥጠን ከተጠቀምን በኋላ ነው ወደ መጨረሻው የጦርነት ሃሳብ መሄድ የነበረብን” ሲሉ ጠያቂያቸውን ጨምሮ በርካታ በወቅቱ “ጦርነት ባሕላችን ነው” ሲሉ የነበሩና አሁን ድረስ እዚያው ሀሳብ ላይ የተቸከሉ የወቅቱ ዕብዶች መስማት የማይፈልጉትን የትህነግ ስህትተ ኬሪያ ተናግረዋል።
ከብልጽግና የቀረበ ግብዣና ምሥጢር ማሾለክ
ኬሪያ ኢብራሒም በታሰሩበት ወቅት ለብልጽግና ምሥጢር ሰጥተዋል፤ የድርጅታቸውን መረጃ ሰጥተው ነው የተፈቱት በሚል በስፋት ተሰድበው ነበር። ለዚህም ይመስላል “ለብልጽግና መረጃ ትሰጪ ነበር፣ በረሃ ለምን ከሌሎቹ ጋር አልወረድሽም፣ ለምን ቀረሽ፣ ወጣት እየተሰዋ አንቺ ግን አባቴ ታሟል ብለሽ ቀረሽ” ሲል ጠያቂው ያነሳላቸው።
ሲመልሱ “ሁሉም ታግሏል ማለት አይቻልም፤ አርሶ አደር ቤት ቆይቶ የመጣ አለ፤ ከዓቅሜ በላይ የሆነ ችግር ገጥሞኝ ነው የቀረሁት” ሲሉ የበረሃ ትግሉ አርሶ አደር ቤት መደበቅ እንደነበር አቃልለውና ሃሜቱን አራክሰው ገለጸዋል። ምሥጥር ማቀበላቸውን አስመልክቶ ሲናገሩ “የፌዴራል መንግሥት የምሥጢር ዕጥረት ነበረበት ወይ?” ብለው ይጠይቃሉ። አክለውም “እነሱ ምሥጢር አይፈልጉም ነበር” አሉ። እንደውም መረጃ ከመንግሥት ያገኙ እንደነበርና ከበቂ በላይ መረጃ እንደነበራቸው፣ በሽሽቱ ወቅት ከመኪኖችና ከየቢሮው ኮምፒውተሮች ወዘተ ዘርዝረው ብልጽግና መረጃ የሚባል ነገር እንዳልጠየቃቸው መሰከሩ። “ታዲያ ካንቺ ምንድነበር እነሱ የፈለጉት” ለተባሉት “እነሱ የፈለጉት ሚዲያ ላይ እንድወጣና እንድናገር ነበር” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የአንቀጽ 39 አስተምሮ
ትልቁና የቃለ ምልልሳቸው አንኳር ጉዳይ አንቀጽ 39ን አስመልክቶ የነበራቸውን አስተምሮ፣ ስልጠናና ግምት የገለጹበት አግባብ ነበር። አንቀጹ ለከፉ ቀን እንዳላዳናቸው በቁጭት ሲገልጹ “ከጦርነት አላደነንም” በሚል ነው።
“ስለ ሕገመንግሥት እኛ በየጊዜው ሲነገረን የኖርነው ከእንግዲህ ወዲህ ዳግመኛ ደም መፋሰስ እንዳኖር፤ ማንም የፈለገ ከዚህ ወጥቶ (ከፌዴሬሽኑ) ወደፈለገው ይሂድ ተብለን ነው ስለ አንቀጽ ፴፱ ሲነገረን የኖርነው” በማለት አንቀጹ ጦርነትን የሚከላከል እንደሆነ ተደርጎ ሲነገራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህን ካነሱ በኋላ “ታዲያ ለምን ትግራይ ጦርነት ውስጥ ገባች፤ እንዴትስ አልተከላከላትም” ሲሉ ይጠይቃሉ።
“አንዳንዴ ሕግም ሆነ ሕገመንግሥት የምታወጣው በሥልጣን ላይ እያለህ ይጠቅመኛል ብቻ ብለህ ሳይሆን ስወርድም ይጠቅመኛል ብለህ መሆን አለበት” ሲሉ ይህ ባለመደረጉ ቁጭት እየታየባቸው የተናገሩት ኬሪያ ኢብራሂም፣ “ፌዴራል ሆነን ብዙ ዓመት እንሠራለን፤ ኢህአዴግ ውስጥም የምንከተለውን አዲዮሎጂ እስከ ፶ ዓመት ይቆያል የሚል አመለካከት ስለነበር አብዛኛው ፌዴራሉን የሚያፈረጥም ነገር ነበር የምንሠራው እንጂ ክልሎች እንደፈለጉ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን አልገነባንም፤ እንዲሆኑም አላደረግንም፤ ተቋማቱ (የፖሊስ፣ የፍርድቤት ወዘተ ማለታቸው ነው) በፓርቲው ሳምባ ነበር የሚተነፍሱት፤ ባይሆንማ ኖሮ ለምን ይህ ሕገመንግሥት እያለ ለምን ጦርነት ውስጥ ገባን” ሲሉ የቁጭት ትንታኔያቸውን አቅርበዋል።

እዚህ ላይ ኬሪያ የተናገሩት ወይም ይፋ ያደረጉት ቁልፍ እና ወሳኝ ሃሳብ ቢኖር፤ “ሕገመንግሥቱ ያልፈለገ በሰላም ይሰናበታል” ብለው አለቆች ባስተማሩት መሠረት ትግራይ ከፌዴሬሽኑ መቀጠል አልፈልግም ስትል ይህንኑ ለምን ተግባራዊ አላደረገችም? ለምን ጦርነት ውስጥ ገባች? ምን ተፈልጎ ነው ወደ ጦርነት የተገባው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አለመኖሩ የኬሪያ ኢብራሒም ጥያቄ ነው። አንቀጽ 39 ተጠቅሶ መገላገል እንደሚቻል በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ የነበረ ድርጅት፣ ለዚሁ ህግ ጠበቃና ብቸና ሞግዚት ሆኖ የኖረ ፓርቲ ለምን ይህን ሁሉ ወጣት በነጻነት ሰበብ አስጨረሰ? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ለማይፈልጉና ለሚያድበሰብሱ ኬሪያ “አስቡና መልሱን ወዲህ በሉኝ” የሚል እንደምታ ያለው መረጃ ሰንዝረዋል። ጦርነቱን አስመልክቶ የትህነግ ጠበቃና ተከላካይ ሆኖ የዘለቀው ጠያቂያቸው ዝም ብሎ ተጨማሪ ማብራሪያ ሳይጠይቅ ያለፈው ይህ አንኳር ነጥብ ውሎ አድሮ አጀንዳ እንደሚሆን ይታመናል።
“የሁለቱም ምክር ቤቶች አወቃቀር ብዝሃነትን መሠረት ያደረገ ነው እንጂ ክልሎች ፌዴራሉን ተው፣ አትግፋን የሚሉበት አልነበረም፤ ሁለቱም ምክር ቤቶች ከብዙሃን ውክልና የተመሠረቱ ነበር፤ ይህ ደግሞ ትክክለኛ አይደለም” ሲሉ ሲነገራቸው የነበረው ሁሉ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል እንደሆነ ያመለከቱት ኬሪያ ኢብራሒም ይህን ስህተት የሠራው ድርጅታቸው እንደሆነ አስመረውበታል።
ትህነግና እግሩና አናቱ
“ትህነግ ከታች ሆኖ ሲታይ በጣም የሚያጓጓ የሆነ ድርጅት ነው (እኔ ከታች ነው የተነሳሁት)፤ ሃሳባችን ልማትን እናፋጥን፣ ዴሞክራሲያዊነትን እናሳድግ የሚል ይሆንና በተለይ ወደ መካከለኛና ከዚያም ከፍ እያልህ ወደ ከፍተኛ ከዚያም ወደ ማዕከላዊ ከዚያ ወደ ሥራ አስፈጻሚ ስትሄድ ግን ሁኔታው እየተቀያየረ ይሄዳል፤ ለሥልጣን ያለህ አተያይ ይለያያል፤ ለዱሮ ሕዝባዊና ለዓላማ ጽናት የነበረው ድርጅት ለሥልጣንና ለጥቅሙ ሲሆን፣ ምንድነው? ይህንን ነውንዴ የፈለግነው? ትላለህ፤ ከታች በጣም እየጓጓህለት የመጣኸው ድርጅት ወደ ላይ ስትመጣ ግን በጣም የምትጠላው ድርጅት ይሆናል። በተለይ አመራሩ እርስበርሱ የማይተማመን፣ የሚጠላላ፣ የማይከባበር፣ የማይደማመጥ፣ የሚናናቅ ሲሆን በጣም ነው የሚያምህ፤ ህወሃት የትግራይ ሕዝብ የሚያውቃት ሌላ ነው፤ ወደ ላይ ከፍ እያልህ ስትሄድ ደግሞ ሌላ ነው፤ ጆሮ የሌለው ህወሃት ነው ወደላይ ያለው” ሲሉ በንግግራቸው መካከል ደጋግመው የሚናገሩት የቀድሞዋ የፌዴሬሽ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በድርጅታቸው መሸማቀቃቸውን ይጠቁማሉ።

ይህ ከሆነ የመልቀቅ ውሳኔ ለምን እንዳልያዙ ተጠይቀው “የእኔ እምነት መልቀቅ ወይም ሪዛይን ማድረግ ሳይሆን የነበረው ድርጅቱ እየተለወጠ እየተቀረፀ እየተስተካከለ ይሄዳል የሚል ነበር፤ በጣም ጥሩ የሆነ መተካካት ብለን ያስቀመጥነው አሠራር ነበር፤ 2008/2009 እኔና ጌታቸው ረዳ ሥራ አስፈጻሚ ገባን፤ ከዚያ ግን እዚያ ስትገባ መግባትህ ነው የሚያስጠላህ፤ ሃሳብህ ዋጋ የማይሰጠው፤ ሪዲክል ነው የሚደረገው፤ እዚያ ስትገባ ሌላ ዓለም ነው፤ እዚያ ስትገባ ድርጅቷ የለችም ነው የምትለው፤ መደማመጥ የለም፤ የራሳቸውን ብቻ ነው የሚዳምጡት፤ እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት” በማለት እየመለሱ ሳለ ጠያቂው ቴዎድሮስ አቋረጧቸው “እነማን ናቸው እነዚህ?” አለ። “ሥራ አስፈጻሚ ከአዲሶቹ ውጪ ያሉት ብዬሃለሁኮ” ሲሉ መለሱ። አክለውም “እነሱ ብቻ ናቸው ዓዋቂ፤ እነሱ ብቻ ናቸው ለትግራይ ሕዝብና ለህወሃት ጥብቅና የሚቆሙት፤ ለካስ አገሩ በሙሉ የተበላሸው በዚህ ምክንያት ነው፤ ይሄ እኔነት፣ አደገኛ አካሄድ ነው” ሲሉ ሐዘናቸውን ገለጹ።
አምልኮ ትህነግ እና ወላዋይነት
“ህወሃት የትግራይን ሕዝብ ወደራሱ ማንነት ቀይሯታል። የትግራይ ብራንድ አድርጎ ቀይሯታል። እኔ ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ባልገባ ማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም ከፍተኛ አመራር ደረጃ ብሆን ኖሮ (ስለ ህወሃት) የሕዝቡ መንፈስ ይኖረኝ ነበር። ሥራ አስፈጻሚ ስገባና በአገር ደረጃ ያለው ሁኔታ ካወቅሁ በኋላ ግን ሕዝቡ አመራሩን እንደማያውቀው ነው የተረዳሁት” ሲሉ አስደንጋጭ ልማዳቸውንና በተገባር ያዩትን ኬሪያ ተናገሩ።
በዚሁ ስሜት ሆነው “ምን ዓይነት ችግር እንዳለባቸው ሕዝቡ አያውቅም። ወጣት ታጋይ ካልሆነ ታማኝ አይደለም፤ ምሁር ከሆነ ደግሞ ወላዋይ ነው የሚባለው፤ ወጣትም ጥርጣሬ ውስጥ ነው። ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስለኛል። ወጣቱና ምሑሩ ወደ አመራር እንዳይገባ ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስለኛል። ሁሌ ክፍተት ሲፈጠር ግን ይህቺ ነገር ነች የምትመጣው፤ አላልንም ወይ እነዚህ ያጠፉናል። ወጣቱ እንዲሰጋ፣ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የተደረገ ይመስለኛል” በሚል የትህነግን አመራሮች ማንነት ያስረዳሉ።

“ህወሃት አገር ስትመራ ነበር፤ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚ፣ ወዘተ ጉዳይ ምን ሚና አለው ለችግሩ፤ የዚያን ጊዜ መደረግ የነበረበት የሥልጣን ጉዳይ ሳይሆን ምን ተሳሳትን፤ ምን አደረግን፤ ምንድነው የተፈጠረው ችግር የሚል መሆን ነበረበት። ለምን ይህ ችግር ይፈጠራል ተብሎ ፎርካስት አልተደረገም፤ ለምን ይህ ሁሉ ጠላት ተፈጠረብን ተብሎ ግምገማ መደረግ ነበረበት” ሲል ትህነግ በአምልኮ መልክ ተቀርጾ እንዴት ትግራይንና ህዝቧን ይዞ ወደ ጥሻ እንድከተተታቸው በድፍረት ይናገራሉ። ዳንኤል ብርሃኔ ትህነግ ታቦት ያልተቀረጸለት የትግራይ ሃይማኖት ነው እንዳለው።
የቁጭት ስሜታቸውን መደበቅ ያልቻሉትና ጣልቃ በመግባት ተጠያቂዎቹን ወደ ራሱ ፍላጎትና አጀንዳ ሲጎትትና ሲገፋ የሚታወቀውን ቴድሮስን ዝም ያሰኙት ኬሪያ፣ “አሁን ወጣ ብለህ ስታየው፤ አሁን ቁልጭ ብሎ ይታይሃል። ሕዝቡ ሌላ፣ ድርጅቱ ሌላ፣ አመራሩ ሌላ፣ ምንም መናበብ የለም” ሲሉ ለትግራይ ሕዝብ አምልኮ የሆነውና ምሁራንን “ወላዋይ” በማለት የሚፈርጀው ትህነግ ጎማው ተንፍሶ በቸርኬ የሚሄድ ድርጅት እንደሆነ ያስረዳሉ።
አሳባቸውን ሲያጠናክሩ “ህወሃት ችግር ሲያጋጥማት ወደ ሕዝቡ ነው የምትሮጠው። ሲመቻት ግን ወደ ሥልጣኗ፣ ወደ ክብሯ ነው የምትሮጠው። ትልቁ ተሞክሮ የምለው ይህ ነው። ችግር ወደ ሕዝብ ምቾት ወደ ሥልጣን” ሲሉ ከላይ የነተበ ድርጅት ህዝብን እንዴት እንደሚያምታታ ያናገራሉ።
“ህወሃትን ሕዝቡ ይገመግማታል፣መረጃ ከሕዝብ ይመጣል፣ የግምገማ ችግር የለም፤ ሁልጊዜ በስብሰናል ነው ግምገማው፤ ሁሌ ታድሰን ወጥተናል ነው ውሳኔው። በስብሰናል ያላልንበት፣ የኔትዎርክ ሥራ ነው ያላልንበት፣ መጠቃቃት ነበር ያላልንበት በግምገማ ላይ ጊዜ ነበር ለማለት ብዬ አላስብም። ገምተናል ስንል ሕዝቡ አንቅሮ ቢተፋን ኖሮ፣ በቃ ቢለን ኖሮ” ሲሉ ኬሪያ ኢብራሂም ትህነግ ሊቀጣ የሚገባው ድርጅት እንጂ አሁንም ይህን ሁሉ ጥፋት ሠርቶ የሚቀጥልበት ዕድል ሊሰጠው እንደማይገባ ይገልጻሉ።
ቀጣይ ውሳኔና መፍትሔ ኬሪያ
ወደፊት በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ እንደሚፈልጉ ሲያስታውቁ፣ “የትግራይ አጠቃላይ ሁኔታ እንዲቀየር እፈልጋለሁ፤ የፈጠርነው መጥፎ ባሕርይ ስላለ ያ ባሕርይ እንዲቀየር አጠንክሬ እታገላለሁ ብዬ አስባለሁ” ሲሉ የተደመጡት ኬሪያ መፍትሔ ያሉትንም ጠቁመዋል።
“ሁሉ ነገራችን ኪሣራ ውስጥ ነው፤ እንደ ድርጅትም፣ እንደ ሕዝብም ኪሣራ ውስጥ ነን፤ በጦርነትም ከስረናል፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትነ በማስተግበርም ኪሣራ ውስጥ ነን። ሁለት ዓመት በኪሣራ አሳልፈናል፤ አሁን ይበቃናል። የትግራይህን ሕዝብ ከችግር ለማውጣት አንዲት መንገድ ብቻ ነች ያለችን፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት…” ኬሪያ ሁሉም በዜሮ እንደተጣፋና ሕዝቡ መከራ እንዲታቀፍ መደረጉን “ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል ነበር፣ አንድ ዓመት መታገስና ምርጫ ማድረግ ይቻል ነበር” በማለት ጦርነቱን መነሳቱን በነቀፉበት ስሜት ውስጥ ሆነው ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት ብቻ አማራጭ እንደሆነ ያስመሩበት ወ/ሮ ኬሪያ፣ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ functional እንዲሆን ማድረግ ይገባል። እርስበርስ መጠቃቃት ጊዜው አልፏል። የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል ሕዝብ ነው፤ መልሶ ግንባታው እንዲፈጸም በፌዴራል ላይ ጫና ማድረግ ነው። ለውጡ መቆም የለበትም እላለሁ” የሚል የመፍትሔ አሳባቸውን ከሰጡ በኋላ፣ ለውጡ እንዴት ሊቀጥል እንደሚገባ ጥቆማ ሰጥተዋል።
“ለውጡ መሪ፣ አደረጃጀት፣ ወዘተ የሚመራው አካል ያስፈልገዋል ከሌለ ዋጋ የለውም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተጠናክሮ ሕዝባዊና ሕጋዊ መስተዳደር ይኑረን” ሲሉ ኬሪያ የሰጡት አቅጣጫ አሁን በትግራይ “በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ሞጋች ማኅበረሰብ ተፈጥሯል፤ ወንበሩን ብረት ምጣድ የሚያደርግ ትውልድ ተፈጥሯል” ሲሉ የጠቀሱትን ለውጥ ፈላጊ ትውልድ መምራትና ማደራጀት አግባብ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህ ጥቆማቸው አቶ ጌታቸው በትግራይ ለውጥ የሚያቀጣጥሉ ኃይሎች ተፈጥረዋል ከማለታቸው ጋር የሚስማማ ሆኗል። ከምንም በላይ ትህነግን እየከዳ እየሸሸ ያለው ሠራዊትና ወጣት መልሶ የሚደራጅበትን አግባብ እያመላከቱ ካሉ ወገኖች ጋርም የሚያያዝ ሆኗል።
ከምንም በላይ የኮነኑት ከሻዕቢያ ጋር የሚደረገው ግንኙነት ነው። “ ማንን ለመምታት፣ ማንን መልሶ ለማጥቃት” በሚል ጥያቄ አስቀምጠው አካሄዱ ስህተት እንደሆነ የገለጹት “ሕዝብ ጦርነት አንፈልግም” በማለት በአደባባይ መቃወሙን በማጉላት፣ ጦርነቱ ያደረሰውን ሰቆቃና ውድመት በማስላት ነው። እናም ማሰብ የተሳነውና ጠያቂያቸው ቴዎድሮስ “ድንጋይ ራሶች” የሚላቸው ውስን የትህነግ አመራሮች እጃቸውን ሊሰበስቡ እንደሚገባ በመጠቆም ነው።
በእርግጥም ወ/ሮ ኬሪያ እንዳሉት ትህነግ ብትንትኑ ወጥቷል። የጌታቸው ቡድን እና የደብረጽዮን ቡድን በመባባል የተከፋፈለው ትህነግ እንደገና በሌላ የመከፋፈል ሒደት ውስጥ ይገኛል። የደብረጽዮን ቡድን በሁለት መከፈሉን እየሰማን ሲሆን አንዱ ከኤርትራ ጋር ወግነን እንሥራ ያሉቱ ሲሆኑ ሌላኞቹ ደግሞ ሃሳቡን የተቃወሙ ናቸው። በትግራይ ብሔረተኝነትን የጀመረው ትህነግ አሁን ላይ ወደ አውራጃዊነት እየወረደ መጥቷል። በዚሁ ከቀጠለ ወደ ቤተሰባዊ ክፍልፍል በሚደርስ የሚሰነጣጠቅ እንደሚሆን ይገመታል። ይህንን ክስተትና በወቅቱ ደብረብርሃን ደርሶ ተዋርዶና ተሸንፎ የተመለሰሰውን ትህነግ ወቅታዊ ሁኔታ ከዱቄት ጋር በማመሳሰል ትህነግ ተበታትኗ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ አባባላቸው በህወሃቷ ወ/ሮ ኬሪያ “ብትንትናችን ወጥቷል” በሚል መደገሙ ሳይጠቀስ የማይታለፍ ሐቅ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter