የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የት ናቸው? የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ምነው ዝም አሉ? የሰው ልጆች ሁሉ ደህንነት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ወዴት ናቸው? ሌት ተቀን በዩቲዩብ ትንሹንም ትልቁንም ጉዳይ ያለማሳለስ የሚያቀርቡ ሚዛናቸው ምንድን ነው? የህትመት ውጤቶችና የኦንላይን ሚዲያዎች መስፈሪያቸው ምን ይሆን? በረባው ባልረባው ሰእር እየለዩ የሚጮሁ የማህበራዊ ሚዲያ ፊት አውራሪዎች የት ደረሱ? ከምንም በላይ ለኦሮሞ ሕዝብ እንደሚታገሉ፣ ለኦሮሞ ህዝብ ሰላም ሲሉ እንቅልፍ እንደማይተኙ የሚናገሩት የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው እንዲሁም ጃዋር መሐመድ የት ናቸው? ወዘተ ጥያቄ ይነሳሉ።
ይህን ጥያቄ የሚያነሱት በወለጋ ሆሮ ሊሙ አካባቢ ካሉ ነዋሪዎች መካከል ለሕይወታቸው ሰግተው በመሸሽ ራሳቸውን ያተረፉ ናቸው። የኦነግ ሰራዊት በተጠቀሰው አካባቢ የቡድኑ መሪ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) “የቅርብ ሰው” የነበሩት ሾዴ የሚባለው የአማጺው ኃይል ከፍተኛ አመራር መገደሉን ተከትሎ ታጣቂዎች በወሰዱት የበቅል እርምጃ ምስኪኖች አልቀዋል።
“ከህጻናት ጀመሮ እድሜ ሳይመርጡ ጨፈቸፉን” የሚሉት ወገኖች ለኢትዮሪቬው ተባባሪ እንዳሉት ከአንድ ቤተሰብ እስከ ስድስት ሰው ተገድሏል። እያፈኑ በመውሰድ ጫካ ውስጥ እንደሚገድሏቸው የሚጠቁሙት እነዚህ ወገኖች ለአዲስ ስታንዳርድ የተሰጠው መረጃና የሟቾች ዝርዝር ትክክል መሆኑን ጠቁመው ” አንድም የፖለቲካ ድርጅት ራሱ ኦነግን ጨምሮ ድርጊቱን አለማውገዙ ተስፋ አስቆርጧቸዋል። ለሰላማዊ ዜጎች የማይሟገቱ ፖለቲከኞች ምን ይፈይዳሉ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በጅምላ ጫካ ተወስደው በድባ ጫካ የተገደሉት አምስት ሰዎች ቤተሰብ እንደሆኑ የሚናገሩት እነዚህ ወገኖች ” ድርጊቱን ለማውገዝ ምን መስፈርት እንዳላቸው አይገባንም። ነገሮች ቢመቻቹና የሰላማችን ጉዳይ አስተማማኝ ቢሆን ኖሮ በአደባባይ እንሞግታቸው ነበር” ሲሉ በተለይም በኦሮሚያ የኦሮሞ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ውቅሰዋል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ሚዲያዎችን፣ የማህበራዊ ሚዲያ ንቂቅዎችን ነቅፈዋል።
” ሌሎች ዝም ቢሉን እንኳ፣ ኦሮሚያ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ሚዲያዎች ውስጡን መርመረው ቢሰሩት ሸኔ ክማን ጋር ሆኖና እንዴት ንጹሃንን እያጠፋ እንደሆነ ይፋ ያደርጉ ነበር። ግን ግልጽ ባልሆነ መልኩ ይህን ለማድረግ ፈቃደናነቱ የላቸውም” ብለዋል። አሁን ላይ ያሉበትን ስፍራ መናገር እንደሚያሰጋቸው ጠሰው እንዳሉት ሕዝብ በታጣቂዎች እጅግ ተማሯል። ግፉ ከልክ አልፏል።
በአማራ ክልልም በተመሳሳይ የሚነሳ የንጹሃን አፈና፣ ግድያና ሽሽት በስፋት በናስረጃ ጭምር እየታየ ነው። በሁሉም ወገን ማግበራዊ ሚዲያ ላይ ከራስ ፍላጎት ጋር በማያያዝ ዜናና ሪፖርት ከመስማት በዘለለ ገለልተኛ ሆነው የሚዘግቡ አካላት አይታዩም። የመንግስት የሚባሉት ሚዲያዎችም በተመሳሳይ የአንድ ወገን ዘገባ ላይ ያተኮሩ ናቸው። በዚሁ መነሻ የሕዝብን ስቃይ ከሙያና ከሞራል አንጻር አጥርቶ በማሳየት ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ ጫና ለማሳደር የሚደረግ ሙከራ የለም።
ይልቁኑም በህዝብ ሞትና ስቃይ “ሰበር መረጃ” በሚል የንግስ ይዘት ያለው ጩኸት ማሰማት ቅድሚያ ማግነቱን ሃዘን የሚሰማቸው ይናገራሉ። ወደ ሰላም የሚያስቡትን፣ የሰላም መንገድ ለማመቻቸት የሚሞክሩትን ማሸማቀቅ ይመረጣል። በዚህ አካሄድ ህጻናት ትምህርት አቁመዋል። ጤና ኬላዎች አገልግሎት አይሰጡም። ስርዓት አልበነት ነግሷል። ዓላማውና መዳረሻው የተዘባረቀ መረጃ በየአቅጣጫው እየተሰማ ህዝብ ግራ ተጋብቷል። ሁሉም መሪ ሆኖ ክልሉ እየፈረሰ ነው። ሚዛንና በሚዛን ማየት በመጥፋቱ ” ውሃ ሲወስድ እያሳሰቀ” እንደሚባለው አማራ ክልል ወደማይወጣው ቀውስ እየተነከረ ነው። በትግራይም ከችግር መማር፣ ከጥፋት መመለስ ያልቻሉ ለዳግም ጦርነት እያሟሟቁ ነው። ያሳዝናል።
ከሆሮ ሸሽተው ለኢትዮሪቪው መረጃ የሰጡት ወገኖች እንደሚሉት የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት በደረሰባቸው ሽነፈት ሳቢያ የተሰላቸውንና ጀርባቸውን የሰታቸውን ሕዝብ እየጨረሱት ነውና ለፍትህ የሚሟገቱ ሁሉ ድምጽ ሊሆኗቸው ይገባል። ከስር አዲስ ስታንዳርድ ከስፍራው የሰላባ ቤተሰቦችን አነጋግሮ ስም በመጥቀስ ያወጣው ዘገባ እንዳለ አትመነዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሐሮ ሊሙ ወረዳ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል እና የቡድኑ መሪ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) “የቅርብ ሰው” የነበሩት ሾዴ በመንግስት የጸጥታ አካላት መገደላቸውን ተከትሎ በተፈጸመ የበቀል ጥቃት 29 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የሟች ቤተሰቦች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።
እንደ ነዋሪዎች እና የሟች ቤተሰቦች ገለጻ፣ መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም በሐሮ ሊሙ ወረዳ ጎርባ ጉዲና እና ሱጌ ቀበሌዎች የተፈጸሙት ጥቃቶች “የሾዴን ሞት ለመበቀል በኦነሠ ታጣቂዎች ተፈጽመዋል” ብለዋል።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እና በጋብቻ ከሟች ቤተሰቦች ጋር ዝምድና እንዳላቸው የገለጹልን በጎርባ ጉዲና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት፣ ከመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ የአሥር ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስረድተዋል።
አክለውም ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ በቅርቡ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ከድቷል” ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ የተወለደበት ቦታ እንደሆነ ገልጸው፤ ታጣቂዎቹም ይህ ግለሰብ የቀድሞ የቡድኑ አባል የነበረው ሾዴን በመግደል “ተሳትፎ” እንዳለው ነው የተናገሩት ተብሏል።
አዲስ ስታንዳርድ ባሳለፍው ሳምንት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትን ምንጭ አድርጎ በመጥቀስ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል የነበረው ሾዴ መገደሉን መዘገቡ ይታወሳል።
ሾዴ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሃሮ ሊሙ ወረዳ ገንጂ አካባቢ ከኮርማ ወንዝ ወደ ሱጊ በሚወሰደው መንገድ ላይ በሞተር ሳይክል ተደብቆ ሲጓዝ የፀጥታ ኃይሎች ባገኙት መረጃ መጋቢት 26 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ላይ መገደሉን በዘገባው ተመላክቷል።
ነዋሪው የመከላከያ ሰራዊቱ ዘመቻ ከተጠናቀቀ በኋላ ያለውን ሁኔታ ሲያስታውሱም “የኦነሠ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደም ከነሱ የተለየውንና ከመንግሥት ጋር እየሠራ የነበረውን የቀድሞ አባላቸውን የሾዴን ግድያ ፈጽሟል ብለው ወዲያውኑ ከሰሱ፤ ጥቃቱ በአካባቢው ሂርፖ ተብሎ በሚታወቀው በአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ ያነጣጠረ ነበር” ብለዋል።
እኚሁ ነዋሪ ቀጠል አድርገውም መጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም. የኦነግ ታጣቂዎች ገርባ ጉዲና የተባለች ቀበሌ ገብተው በግምት ከቀኑ 12:00 ላይ የ12 ዓመት ልጅን ጨምሮ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ሰዎችን ከቤታቸው በግድ ወሰዷቸው ብለዋል። አክለውም “ታጣቂዎቹ ሰዎቹን አፍነው ከወሰዱ በኋላ ድባ ደን ወደሚባልና ባሽር በመባል ወደሚታወቅ ቦታ ወስደው ገደሏቸው” ብለዋል።
ዘመድ አዝማድ ስለ ግድያዎቹ ያወቁት እሳቸው እና ሌሎች ጥቂት ሰዎች በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ወደ ጫካ ሄደው አስከሬኖችን ካገኙ በኋላ መሆኑን ገልጠዋል። ሟቾች ማሞ ሁንዴ ሂርፖ፣ ሌሜሳ ቦኮሬ ሂርፖ፣ አዲሱ ተሰማ ሂርፖ፣ ፋይሳ ተሳማ ሂርፖ እና የ12 ዓመቷ ባዳሳ ታደሰ ጌታቸው ቦኮሬ ሂርፖ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ የሟች ቤተሰቡ ገለጻ፣ ተጨማሪ የሂርፖ ቤተሰብ አባላትን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በድጋሚ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ከጥቂት ቀናት በኋላ የኦነግ ታጣቂዎች ወደ ተጎጂዎቹ ቤት ተመልሰው ከ11 ዓመት በታች የሆኑ ሶስት ህጻናትን ጨምሮ አምስት ተጨማሪ ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውን ገልጸዋል። በተመሳሳይ ተጎጂዎቹን ወደ ዲባ ጫካ ከወሰዱ በኋላ ገድለዋቸዋል ብለዋል።
የሁለተኛው ጥቃት ሰለባዎችም ዳጊቱ እጄታ ዲባባ (የማሞ ሁንዴ ሂርፖ ባለቤት)፣ ሶራ ማሞ (የ10 ዓመት ልጃቸው)፣ ቡልቻ ማሞ (ሌላ የሰባት ዓመት ልጅ)፣ ተረፈ ባባ ላሚ እና የሰባት ዓመቷ ናሞ አብዲሳ ተብለው ተለይተዋል።
አክለውም ማሞ ሁንዴ ሂርፖ በቅርቡ መንግስት ባቀረበው የሰላም ጥሪ ቤተሰቡን ከመቀላቀሉ በፊት የኦነግ አባል ነበር ብለዋል።
ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉ ሌላ ምንጭ በበኩላቸው በገርባ ጉዲና የተከሰቱት ሁለቱን ጥቃቶች መፈጸማቸውን ገልጸው ተጎጂዎች ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. መገደላቸውን አረጋግጠዋል።
“የቀሩት የቤተሰብ አባላትና ነዋሪዎች አሁንም በከፍተኛ ሀዘን ላይ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። “በጥቃቱ የተረፉት የሂርፖ ቤተሰብ አባላት በታጣቂው ቡድን ተጨማሪ ጥቃት በመፍራት አካባቢውን ለቀው ሄደዋል”ሲሉም አክለዋል።
አንድ የአካባቢው ነዋሪ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረጉት ቆይታ በምስራቅ ወለጋ ዞን በሀሮ ሊሙ ወረዳ በምትገኘው ሱጌ ቀበሌ በ”ኦነግ ታጣቂዎች” ተፈጽሟል የተባለ ሌላ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ጥቃቱ ከታጣቂው ቡድን በመክዳት ተጠርጣሪ ተደርጎ የተወሰደው እና ሾዴን በመግደል “ተሳታፊ” ነው የተባለው የፋይሳ ደሳለ ቤተሰብ ላይ ያነጣጠረ ነበር።
አያይዘውም መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም “የኦነግ ታጣቂዎች ከሱጌ ቀበሌ የሸሸ የቀድሞ ታጣቂ የቤተሰብ አባላትና ዘመዶች ናቸው ብለው ያመኑትን ንጹሃን ዜጎች መግደል ጀመሩ” ሲሉ ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የሁለት ዓመት ህጻን፣ ሴቶችና ወንዶችን ጨምሮ ስምንት የቤተሰቡ አባላትና ዘመዶች መገደላቸውን ጠቁመዋል።
የአካባቢው ነዋሪ አክለውም በ”ኦነግ ታጣቂዎች” የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአካባቢው እንደቀጠሉና በዚህም ምክንያት የአቶ ፋይሳ ተጨማሪ ሰባት ዘመዶች መገደላቸውን ገልጸዋል። “እነዚህ ሰዎች ሾዴን ለመያዝ የጸጥታ ኃይሎችን ረድተዋል ተብለው ስለተጠረጠሩ ነው ኢላማ የተደረጉት” ሲሉም አክለዋል።
በሱጌ ቀበሌ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያረጋግጥ ሌላ ምንጭ በበኩላቸው የአንዳንድ ተጎጂዎችን ማንነት ለአዲስ ስታንዳርድ ጠቁመዋል። ከእነዚህም ውስጥ ናቾ ደሳሌ፣ አዳሜ ዘለቀ፣ ዳባ ዘለቀ፣ ብቅልቱ ዲሪባ፣ ኢፍቱ ዲሪባ፣ ገመዳ ዲሪባ፣ ዲሪባ ተስፋዬ እና ሹካሬ ገመቹ ይገኙበታል።
አክለውም በአቅራቢያው በሚገኝ መንደር ሁለት ተጨማሪ ግለሰቦች በቀለ ጎንዶር ጋማዳ እና ጆቴ በቀለ መገደላቸውን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ ግድያው በትክክል ከምን ጋር እንደሚገናኝ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
በኦነግና በመንግስት መካከል በዳሬሰላም በተካሄደው ድርድር ላይ የተሳተፉ አንድ ከፍተኛ የኦነግ ተወካይ እንዳሉት፣ ሾዴ በታንዛኒያ የጃል ማሮ የግል ጠባቂ በመሆን በሰላም ንግግሩ ተሳትፈዋል።
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter