ሚኔሶታ በተካሄደ ስብሰባ በኦሮሚያና አማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ወደ ደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያ ለማስፋት ዕቅድ ተያዞ ነበር። ዕቅዱ የተያዘው በኦሮሚያ በጃል ሰኚ የሚመራው የኦነግ ሸኔ ሰፊ ቁጥር ያለው ታጣቂ ሃይል እጅ መስጠቱን ተከትሎ ሲሆን ሰብሳቢው ከጀርባ ሆነው ዕቅዱን በነደፉት ተወክለው የተገኙ ናቸው።
ትህነግ ስልጣን ላይ እያለ ሶማሌ ክልልን አቶ አብዲሌን ከስልክ እንጨት ላይ አውርዶ መሪ ማድረጉን፣ ከራሱ ማህጸን የተወለዱ ጀነራሎች መድቦ ሲያስተዳድርና ጄል ኦጋዴን የሚባል የምድር ሲኦል እስር ቤት አቋቁሞ እንዳልነበር፣ ወደ መቀለ ከሄደ በሁዋላ በትግራይ ቲቪ ቢቢሲን ጠቅሶ “ለሰላሳ ዓመታት ለነጻነት ሲታገል” የኖረ ሲል ኦብነግን አሞካሽቶ እንደነበር አይዘነጋም።
ይህን በማስታወስ ስለ አዲስ ስብሰባ የጠቆሙን እንዳሉት በኢትዮጵያ ትጥቅ ያነሱ፣ ተኩስ ለመክፈት ዳር ዳር እያሉ ያሉ በዕቅዱ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በደቡብ ክልልና በደቡብ መእራብ ተኩስ የሚከፍቱ ኃይሎችን ማደራጀት ላይ ሊሰራ እንደሚገባው በስብሰባው ላይ ተነስቶ ነበር።
ስብሰባው ላይ የተካፈሉና አካሄድ ያላማራቸው ለኢትዮሪቪው ” ሜኖሶታ ያለው ህብረት አካሄዱ ቢሳካ ውጤቱ ያስደነግጣል” በማለት በኢትዮጵያ በየአቅጣጫው ጦርነት ለማስፋት የተያዘውን ዕቅድ አብራርተው ነበር። ይሁን እንጂ ህብረቱ አሁን ላይ የቀድሞው እንቅስቃሴው ባሰበው መልኩ ባለመሄዱ ተቀዛቅዞ መልኩን በመቀየር የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረገ ነው። በተለይም በሚዲያ ፕሮፓጋንዳና ሴራ ማምራተ ላይ ትኩረት ሰጥተውና በጀት መድበው እየሰሩ እንደሆነ አመልክተዋል።
በዚሁ ዕቅድ መሰረት በምስራቅ በኩል ጀርባውን ሶማሊያን በማድረግ ጦርነት እንዲከፍት ስምምነት የደረሰው ” ሰላም ይሻላል” በሚል ጠመንጃውን ያወረደውና ራሱን የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር በሚል ስያሜ ከሚጠራው ድርጅት ያፈነገጡት ሊቀመንበሩ ናቸው።
“የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ አነሳ” ሲል አሁን ዶናልድ ትራምፕ እንዲዘጋ ያደረጉት ቪኦኤ አማርኛ ለዚሁ ዕቅድ ሲባል ያፈነገጠውንና ኬንያ የተቀመጠውን አንድ አመራር ጠቅሶ መዘገቡን የሚያስታውሱት የመረጃው ምንጭ፣ ኬንያ ያለው ይህ የኦብነግ ፍንካች በስም ከሚታወቁና ናይሮቢ ከነበሩ የተቃዋሚ አመራሮች ጋር ግንኙነት እንደነበረው በስብሰባው ወቅት ተነስቶ ነበር። በጥቅሉ የተጠቀሱትን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ማንነት ግን አልጠቀሱም።
በቅርቡ ራሳቸውን በ2010 ሰላም መርጦ ከገባው ድርጅታቸው የለዩትና የጦርነት አማራጭ እንደሚከተሉ ያስታወቁት አብዱራህማን ማህዲ፣ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ ግብጽ ወደ ክልሉ መምጣቷን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ሞክረው እንደነበር አይዘነጋም።
በዚሁ የተቀነባበረ ስልት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ድንበር አካባቢ ተከማችቶ ጥቃት ሊፈጽም ያደባ ኃይል በአገር መከላከያ ሰራዊት ድንገተኛ ጥቃት ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን፣ ይህንንም መንግስት በቪዲዮ አስደግፎ ማሳየቱን የሚዘነጋ አይደለም።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የኦሮሞ ተቃዋሚ ድርጅት አመራር ” በቅርቡ ኦብነግ በምስራቅ በኩል ጦርነት ለመክፈት መዘጋጀቱን ሰምቻለሁ። መንግስት ባስቸኳይ ከሶማሊያ ጋር የገባበትን ንትርክ ማቆም አልበት” ሲሉ የአገር መከላከያ እርምጃ ከመውሰዱ ቀደም ብለው የግል አስተያየታቸውን ጨምረው ገልጸው ነበር።
ፓርቲውን ይዞ ኢትዮጵያ የተቀመጠው አመራር “በኦብነግ ሊቀመንበር አብዱራህማን መሀዲ የወጣውንና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቀውን ደብዳቤ አወግዘዋለሁ” በማለት ያወጣው መግለጫ ፒዲኢኤፍ ከስር ያንብቡ።
የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር (አብነግ) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ባወጣው መግለጫ ነው በ2010 ዓ.ም የተደረሰውን ስምምነት አክብሮ ለመቀጠል መወሰኑን ይፋ ያደረገው።
የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከፌደራል መንግሥት ጋር የተደረሰውን የሰላምስምምነት ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን እና በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ በሰላማዊመንገድ መሳተፉን እንደሚቀጥል ይፋ አድርጓል።
በማከልም በፈረንጆቹ መጋቢት 30 በኦብነግ ሊቀመንበር አብዱራህማን መሀዲ የወጣውንና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቀውን ደብዳቤ አወግዘዋለሁ ብሏል።
መግለጫው ሲቀጥል – ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ሕዝብን የሚከፋፍል ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆነ አመፅና ሁከትን የሚፈጥር ማንኛውም አይነት አመለካከት ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ለተጎናፀፈው የሶማሌ ክልል ህዝብ የሚጠቅም ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብሏል። የቀረበውን የአመፅ ጥሪም የሊቀመንበሩን የግል አመለካከት እንጂ የድርጅቱን አቋም እንደማይወክል ነው የሞገተው። የኦብነግ መግለጫ ሲቀጥል “የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ በመንግስት በኩል ቁርጠኝነት አለ” ብሏል።
በመሆኑም “በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ አገራት የሚገኙ ወገኖች የክልሉ ሰላም አሁን ባለበት ሁኔታ ተረጋግቶ እንዲቀጥልና ልማት እንዲፋጠን በሚችሉት መንገድ ሁሉ አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርቧል።
መግጫውን ሲደመደምም ፀረ ሰላም አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች በፓርቲው ስም በሚፈፅሙት ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ምክንያት በፓርቲው ህጋዊነት እና በሚያደርገው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ተሰብስቦ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል። ጉዳዩን የሚከታተሉ እንዳሉት ያፈነገጡት ሊቀመንበር ከድርጅቱ ይባረራሉ።
የሶማሌ ክልል ከለውጡ በሁዋላ ችግሩን ፈቶ በልማት ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሳይቀሩ እየመሰከሩ ነው። በክልሉ ታይቶ የማይታወቅ የሩዝና ስንዴ ምርት በከፍተኛ ደረጃ መመረት መጀመሩ አርብቶ አደሮች ወደ ሰብል ምርት እንዲዛወሩና ቀለብና ውሃ ፍለጋ ከብቶቻቸውን ይዘው ከቦታ ወደ ቦታ ከመዘዋወር ተገላግለዋል።የመኪና መገጣጠመያን ጨምሮ በርካታ ኢንደስትሪና ስፋፊ ኢንቨስትመንት በክልሉ መገንባቱን ዳታዎች ያስረዳሉ። ከምንም በላይ ግን የክልሉ ዲያፖራዎች በብዛት ኢንቨት ያደረጉበት ክልል ነው።
