ብሄራዊ ባንክ የብድር ጣሪያ የጣለበትንና ባንኮች ያላቸውን ሃብት በአብዛኛው በቁጥር ሊዘዘሩ ለሚችሉ “ሃብታሞች” ማበደሩ ፍትሃዊነት የሌለው መሆኑን ጠቅሶ ይህ እንደማይቀጥል አስታውቆ ነበር፡፡ በአገሪቱ ዜጎች ብድር የማግኘት መብታቸው ተገፎ የግል ባንኮች በዘመድና በትስስር የሕዝብ ገንዘብን ይቀራመቱ እንደነበር ጠቅሶ አሰራሩን ለማረቅ የብድር አሰጣጥ ሂደት እንዲተብቅ መደረጉን ጠቅሶ ብሔራዊ ባንክ ከጣላቸው ገደቦች አንዱ የብድር ጣሪያ ነበር።
የብሔራዊ ባንክ፣ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ፣ ባለፈው ሳምንት ሁለተኛ ስብሰባውን በማካሔድ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን መስጠቱን አስታውሶ ቲክቫህ ያነጋገራቸው ባለሙያ የተባሉ አካላት መንግስት በቀጥታ ለውሳኔው መነሻነት የሰጠውን ምክንያት እየነቀሱ ሳይዘረዙና ማጣፊያ ሃሳብ ሳያቀርቡ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። እንዳለ ያንብብቡት።
በኮሚቴው ውሳኔዎ ተፅዕኖ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው አንድ የፋይናንስ ባለሙያ፣ “ ውሳኔው በስራ ፈጠራና በገቢ ማመንጨት በኩል ዋጋ ያስከፍለናል ” ብለዋል፡፡
በቡና ባንክ ዋና የስትራቴጂ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ሙሉነህ አያሌው በሰጡን የግል አስተያየት፣ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መምጣቱን እንደገለፀ አውስተው፣ ነገር ግን፣ “ መልሶ ያንሰራራል ” የሚል ስጋት ስላለው፣ ቀድሞ የነበሩትን ገደቦች አላነሳም ይላሉ፡፡
ከኮሚቴው ውሳኔዎች አንዱ፣ ቀደም ሲል በባንኮች የብድር ዕድገት ላይ የተቀመጠው የ18 በመቶ ገደብ በነበረበት እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ የባንኮችን የማበደር ዕድል ይቀንሳል ይላሉ፡፡
ይህን በምሳሌ ሲያስረዱም ፥ “ አንድ ባንክ ባለፈው ሰኔ ወር 2016 ላይ የብድር መጠኑ 100 ቢሊዮን ከደረሰ፣ የሚቀጥለው ሰኔ ላይ 2017 ላይ 118 ቢሊዮን ነው ማድረስ የሚችለው ማለት ነው፡፡ ለዛውም፣ የሰበሰበው ብድር ተቀንሶ፣ ያልሰበሰበው ብድር ተደምሮ ነው እዛ መድረስ አለበት የሚባለው፡፡ በዚህ ስሌት ባንኩ ባለፈው አመት የሰጠው ብድር ብቻ ሳይሆን ከተመሰረተ ጀምሮ የሰጠው ብድርም ሊሆን ይችላል፡፡ እስካልተሰበሰበ ድረስ በብድርነት ይያዛል፡፡ ባንኩ ያልሰበሰበው ነባር ብድርና የሰጠው አዲስ ብድር ተደምሮ ነው የሚሰላው፡፡ በብድር ወለዱ ብቻም ጣሪያው ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ አንድ ባንክ፣ ባለፈው አመት 100 ቢሊዮን ብድር ከነበረውና የዚህ ወለዱ 18 ከመቶ ከሆነ፣ በዚህ አመት ምንም ብድር ሳይሰጥ የአምናው ብድር ብቻውን 118 ቢሊዮን ይሆናል፡፡ ሳያበድርም ሳይሰበስብም ጣሪያውን ሊደርስበት ይችላል ” ብለዋል።
አቶ ሙሉነህ አያሌው የዚህ ተፅዕኖው ምን እንደሆነ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል።
“ ይህ ውሳኔ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ያቀዘቅዘዋል፡፡ በስራ እድል ፈጠራ እና በገቢ ማመንጨት በኩል ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ የብድር አቅርቦት መኖር፣ ሰዎች ተበድረው ስራ እንዲሰሩና የስራ እድል እንዲፈጥሩ ያበረታታል፡፡ የብድር አቅርቦት ከሌለ ኢንቨስትመንት ይዳከማል፣ የስራ ዕድል አይኖርም፣ ሰዎች ገቢ አያመነጩም ማለት ነው፡፡ ያ ባለመሆኑ ይህንን ዋጋ ነው እየከፈልን ነው ያለነው፡፡ ”
የብድር አቅርቦቱ ውስን ስለሆነ፣ ባንኮች የብድር አሰጣጥ ላይ ጠበቅ ያሉ መስፈርቶችን ይጠቀማሉ ብለዋል፣ ባለሙያው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ አንድ እቃ ከገበያ ሲጠፋ፣ አለያም አቅርቦቱ ሲቀንስ ዋጋው እንደሚወደደው፣ የባንኮች ብድርም በተመሳሳይ አቅርቦቱ ሲቀንስ ዋጋው (ወለዱ) ይወደዳል፡፡ አቶ ሙሉነህ ይህን እንዲህ በማለት አብራርተዋል፡፡
“ ገበያው ውስጥ የሚኖረው ብድር ትንሽ ነው፣ የተበዳሪ ብዛት ደግሞ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ባንኮች ያለቻቸውን ትንሽ የብድር ገንዘብ ለጨረታ ያቀርቡዋታል ማለት ነው፡፡ ያለቻቸውን ውስን ብድር ለመስጠት ጠበቅ ያለ መመዘኛ ያስቀምጣሉ፡፡
አንደኛው መመዘኛ የብድር ዋጋ (ወለዱን) ማስወደድ ነው፡፡ ሌላኛው መስፈርት ደግሞ “አስተማማኝ ተበዳሪ ” የሚል ይሆናል፡፡ ብድራቸውን በእርግጠኝነት ይመልሳሉ ለሚባሉ፣ ለተመረጡ ተበዳሪዎች ብቻ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ማለት የስጋት መጠኑ ወደ ዜሮ ለተጠጋ ተበዳሪ ነው፡፡ ትንሽ ስጋት ላለበት ተበዳሪ አይሰጡም፡፡ ስጋቱን የምትቀንሰው ለብድር መያዣ በሚቀርበው ዋስትና (ለምሳሌ ቤት ወይም መኪና) ነው፡፡
የቤትና የመኪና ዋስትና ይዘው ከሚመጡ ተበዳሪዎች መካከል፣ የቤት ዋስትና የሚያቀርበው ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ መሬት ላይ ያለ ነገር ወድቆ አይወድቅም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ መኪና ዋጋው እየቀነሰ ስለሚሔድና አደጋዎችም ስለሚኖሩ ከቤት በላይ ተመራጭ ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ፣ የንግድ ፍላጎታቸውን ያያሉ፡፡
ለምሳሌ ዳያስፖራ ለሆኑና በኤክስፖርት ንግድ ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪዎች በውጭ ምንዛሪ ስለሚከፍሉ ቅድሚያ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ብድሬን በብር እከፍላለኹ የሚለው ተመራጭ አይሆንም፡፡ ባንኮቹ ያላቸው የብድር ገንዘብ ውስን ስለሆነ፣ ከንግድ አንፃር የትኛው ያዋጣናል ይላሉ፣ ጠበቅ ያለ የብድር መመዘኛም ያወጣሉ፡፡ ”
በዚህ ኹኔታ ተጎጂ የሚሆኑት ዘርፎች የትኞቹ ናቸው ?
“ የአምራቹ ዘርፍ የትርፍ ህዳጉ ጠባብ ነው፡፡ እንደ ግብርና እና ማኑፋክቸሪንግ የመሰሉ ዘርፎች በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ብዙ ኢንቨስትመንት ስለማይስቡ ይጎዳሉ፡፡ ይህን ውስን የብድር አቅርቦትን የመሳብ ዕድል አይኖራቸውም፡፡ ሰፊ የትርፍ ህዳግ ያላቸው ቢዝነሶች ግን አሁንም አዋጭ ስለሆኑ ብድር ሊያገኙ ይችላሉ፡፡”
መፍትሔውስ ምንድነው ?
“ የብድር ጣሪያው ገንዘብ እንዳይፈጠር አድርጓል፡፡ ብድር ተሰጥቶ ወለድ ካልተሰበሰበ ገንዘብ አይፈጠርም፣ ባንኮች ተቀማጭ አያገኙም፡፡ የብድር ጣሪያውን ማንሳት ብቻም መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ የብድር ጣሪያው ቢነሳም ባንኮች በቂ ብድር ያቀርባሉ ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት አለባቸው፡፡ ለእጥረቱ ትልቁ መነሻ የሆነው የቁጠባ አቅም መዳከሙ ነው፡፡ ጥቅል የሀገር ውስጥ ቁጠባ በተከታታይ አመታት እየቀነሰ ነው የመጣው፣ ገንዘብ እየተቆጠበ አይደለም ማለት ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ምክንያቶችንም መጥቀስ ቢቻልም፣ የቁጠባ መዳከም የባንኮችን የጥሬ ገንዘብ ክምችት አቅም አዳክሞታል፡፡ ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ባንኮች የሚመጣው ተቀማጭ ገንዘብ የቁጠባ ውጤት ነው፡፡ ይህ ካልተስተካከለ ችግር ነው፡፡”
ብሔራዊ ባንክ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ግብይት በመፍቀድና፣ ንግድ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ የአጭር ጊዜ ብድር እንዲወስዱ በመፍቀድ፣ ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት እየሰራ ቢሆን፣ ይህ ግን ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም ብለዋል፡፡
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ