ከተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች የዱባይ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ኃላፊ ሌ/ኮለኔል አብደላ መሃመድ የተመራው የምርመራ ቡድን አዱስ አበባ ገብቶ የጋራ የወንጀል ምርመራ ስራ እየሰራ ነው። የቡድኑን አዲስ አበባ መምጣት ተከትሎ ይፋ በሆነ ዜና የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድን ለተመሳሳይ ስራ ወደ ዱባይ ያመራል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዱባይ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ጋር በወንጀል ምርመራ፣ ወንጀለኞችን አሳልፎ በመስጥትና መቀበል ዙሪያ መወያየታቸውን ያስታወቀው የፌደራል ፖሊስ ነው።
በዜናው እንደተመለከተው የአረብ ኤምሬቶች የዱባይ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ኃላፊ በሆኑት በሌ/ኮለኔል አብደላ መሃመድ የተመራው የምርመራ ቡድን አዲስ አበባ የተገኘው በዱባይ ወንጀል ሠርተው በኢትዮጵያ የተሸሸጉና በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ነው።

በዱባይ ወንጀል ሠርተው በኢትዮጵያ የተሸሸጉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተከናወነባቸው እንደሆነ ያስታወቀው የፌደራል ፖሊስ ዜና፣ ይህንኑ አስመልክቶ ስራው እየተሰራ ያለው በጣምራ የወንጀል ምርመራ በኢትዮጵያ ፈደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት ነው።
ግንኙነቱን አስመልክተው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል መግለጫ ሰጥተዋል። ከወንጀል ምርመራ ቡድኑ ጋር ባደረጉት ውይይት በዱባይ ወንጀል ሠርተው በኢትዮጵያ የተሸሸጉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተው በቀጣይ በሁለቱም ሀገራት ተፈላጊ የሆኑ ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠት በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በጋራ የወንጀል ምርመራ ቡድን በማቋቋም እና የልምድ ልውውጥ በማድረግ እንደሚሠራ ተነጋግረዋል።
ሌ/ኮለኔል አብደላ መሃመድ በበኩላቸው በቀጣይ ለሚከናወኑ የጋራ የወንጀል ምርመራ ሥራዎች ወደ ዱባይ የሚሄዱትን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ኃላፊዎችን ለመቀበል ዝግጁነታቸውን ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ዘርፈው ወደ ውጭ የሸሹ ተጠያቂ የሚሆኑበት፣ የዘረፉትም ሃብት ወደ አገቤት የሚመለስበት አግባብ በጥናት እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀው እንደነበር አይዘነጋም። በውቅቱ ቱርክና ዱባይ በርካታ ሃብት መጋዙን የሚያውቁ የመንግስት ትኩረት በሁለቱ አገሮች ላይ ሊሆን እንደሚችል ማስታወቃቸውም የሚታወስ ነው።