አቶ ጌታቸው ከቢቢሲ ካደረጉት ቃለ መጠይቅበትንሹ፦
ቢቢሲ- በሥልጣን ዘመንዎ የመጨረሻዎቹ ቀናትና ወራት፣ ኤርትራ ከተፎካካሪዎ አመራር አጋር እንደሆነች ሲከስሱ ነበር። በኤርትራና በተፎካካሪው አመራር ላይ ለሚያቀርቡት ለዚህ ውንጀላ ምን ማስረጃ ያቀረባሉ?
አቶ ጌታቸው ረዳ- እንደ የሕግ ፍርድ ቤት ማስረጃ መጠየቅ የጋዜጠኛ ኃላፊነት መሆኑን አላውቅም። ግን ይህንን ልነግርህ እችላለሁ።
ቢቢሲ- ለንግግርዎ ግን ማብራሪያ ማቅረብ አለብዎ?
አቶ ጌታቸው ረዳ- ማብራሪያዬን አቅርባለሁ። ስም ልጠቅስልህ አልችልም። ይህንን ግን አውቃለሁ፤ በእኔ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ ሰዎች የተወሰኑት በሕጋዊ፣ የተወሰኑት ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ ከኤርትራ ጋር ለመገናኘት ሲሞክሩ ነበር። የግመሉን ጀርባ የሰበረው የመጨረሻ ሰበዝ [የመጣው] ግን ደስተኛ ያልሆኑ የህወሓት አካላት ውስጥ ነው፤ ሁሉም የህወሓት አንጃ አመራር ማለቴ አይደለም። ግምገማቸው ምንም ይሁን ምን፤ በህወሓት ውስጥ ያሉ የተወሰኑ አካላት በጋራ ጠላታቸው ላይ ለማበር ይህንን እድል መጠቀም ጀመሩ። ስም ልሰጥህ አልችልም፤ ነገር ግን የተፈጠረው ይህ እንደሆነ ለማረጋገጥ በቂ ማስረጃ አለኝ።
ቢቢሲ- በሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የኋላ ታሪክ ላይ ያነሱትን ስጋት በተመለከተ አለመካከትዎን በአግባቡ መረዳት እፈልጋለሁ። አዲሱ ፕሬዝዳንት ከቀደመው አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች አካል ለመሆናቸው ማስረጃው ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ- የእኔ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበር። የራሱን የስራ ዝርዝር መፈጸም አልቻለም። [ኃላፊነቱን] መወጣት ላለመቻሉ ታደሰን ብቻ እየወቀስኩ አይደለም። እኔ እርሱን በተመለከተ ምንም አላደረግኩም። እርሱን ማንሳት አልያም መተካት [አለመቻል] የእኔ ውድቀት ነው። ብዙ ማስረጃ አለኝ፤ ዛሬ ጠዋትም ይህንኑ ተናግሯል። የእኔ ምክትል ነበር፤ እናም ለጸጥታ ጉዳዮች ኃላፊነት ነበረበት፤ በብዙ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነት ነበረበት። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ የእርሱ የስራ ዝርዝር በውድቀት የተሞላ ነው። የእርሱ ውድቀቶች ግን የእኔም ውድቀቶች ናቸው።
ቢቢሲ- ከፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ ሲቀበል እንደነበረ አልተናገረም? አንዳንዶች እንደሚናገሩት እንደ መሪ የጠቀስካቸው ጉዳዮች የሚወድቁት በአንተ ትክሻ ላይ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ- ሞኝ አትሁን።
ቢቢሲ- ጥያቄ ብቻ እየጠቅኩ ነው?
አቶ ጌታቸው ረዳ- አይደለም፤ ይህ አይነቱ ትዕዛዝ. . . ታውቃለህ፤ የትግራይ ፖለቲካ አስቸጋሪ ነው። ይቅርታ ለተጠቀምኩት…
ቢቢሲ- ይቅርታ አያስፈልግም፤ ይቀጥሉ
አቶ ጌታቸው ረዳ- የትግራይ ፖለቲካ በጣም አስቸጋሪ ነው። ራሱን፤ በራሱ የሚመራ አካል አድርጎ የሚቆጥር የሚመስል የተደራጀ ሠራዊት ያለበት ብቸኛ ክልል የእኛ ነው። የፕሪቶሪያ ስምምነት ይህንን ያልተለመደ ሁኔታ እንዲፈታ ይጠበቅ ነበር። ታደሰ ግን እንደ ሠራዊቱ አዛዥ፤ የተወሰኑትን የእኔን ውሳኔዎች መቃረን እንደሚችል ያስባል። አንተ ባለህበት የዓለም ክፍል ለሚገኙ ሰዎች ይህንን ለመረዳት በጣም ከባድ ነው። ታውቃለህ፤ ፕሬዚዳንቱ ውሳኔ የሚያሳልፍበትና ውሳኔውም በምክትሉ በቁም ነገር የሚወሰድበት ሁኔታ አልነበረም።
ይህ አንዱ የችግሩ አካል ነበር። እርግጥ ነው፤ አንዳንዶቹ የእኔ ውሳኔዎች ተፈጽመዋል። አሁንም ግን፤ ለስኬቶቹ ኃላፊነት እንደምወስደው ሁሉ ለውድቀቶቹም ተጠያቂነቱን እወስዳለሁ።
በእኛ ጉዳይ ፖለቲካውን ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው በስልጣን ላይ ያልሆነ ፓርቲ ሁሉንም ጠቅልሎ ለመውሰድ፤ የመንግሥት ሀብትምን ለመቆጣጠር የሚሞክር መሆኑ ነው። በመንግሥት ስር መሆን የነበረበት ሰራዊት ደግሞ ራሱን የሚቆጥረው ራሱን እንደቻለ አካል ነው። ትንሽ የተወሳሰበ ነው። ለመረዳት ያስቸግራል።
via : Addis insider