ስርዓተ ቀብራቸው በዝነኛው የቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን አልተፈፀመም። ስለማይገባቸው ሳይሆን እሳቸው ስላልፈለጉ ነው። በኑዛዜያቸው መሠረት ስርዓተ ቀብራቸው ከቫቲካን ወጣ ብላ በምትገኘው ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን [ Santa Maria Maggiore ] ውስጥ ተፈፅሟል።
ይህ ዘላቂ ማረፍያቸው እንዲሆን የመረጡት ቦታ በሮማን ኢምፓየር ዘመን [ባሮች] የሚቀበሩበት ስፍራ ነበር። እሳቸውም ከባለጠጎች እና ከዕውቅ ሰዎች ጎን ከማረፍ ይልቅ ከባሮች እና ከ[ተራ] ሰዎች ዘንድ መሆንን ነው የመረጡት።
ዛሬ የተፈፀመው ኑዛዜያቸው የሙሉ ሕይወታቸው ነፀብራቅ ነው። የኖሩት ከድሆች ጋር ነው። የጮኹት ለድሆች ነው። ያረፉትም በድሆች መሐል ነው።
ጆርጅ ማሪዮ በርጎግሊዮ….ሊቀ ጳጳስ ፍራንቺስኮስ…
አባ ፍራንሲስ…[ተራ]የምሽት ክበብ ጋርድ…የኬሚስትሪ ምሩቅ…የፋብሪካ ሰራተኛ…ፍልስፍናን፣ ሥነ ጽሑፍ እና ሥነ ልቦናን አከታትሎ ያጠኑ ብርቱ…በስነ መለኮት ጥናት የላቁ ሊህቅ…!
ከ[ተራ] ቦታ ተነስቶ በዓለም ቁጥር አንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ ቤተዕምነትን የመሩ ጀብደኛ…ከአውሮፓ ተወላጆች ውጪ በቫቲካን የተቀቡ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ…ከምንም ተነስቶ ደማቅ ወርቃማ አሻራን ያኖሩ ካህን..ለሰፊው ሕዝብ መቆምን በንግግር ሳይሆን በተግባር የኖሩ መምህር…ስለ ጋዛ እልቂት እንባ የሚተናናቃቸው …ዘር ማፅዳት ነው ብሎ ደፍሮ በስሙ የጠሩ ልባም…ለአፍሪካ ያለቀሱ ሩህሩህ…በሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አውሮፓውያን ያልሆኑ 140 ካርዲናሎችን በመሾም አካታችነትን አካቶ ያሳዩ…በታሪክ አጋጣሚ ቤተክርስቲያኒቱ ለፈፀመችው ጥፋት በይፋ ይቅርታ የጠየቁ…የአሜሪካም ሆነ የቢሪታኒያ መሪዎችን ለመተቸት የማይፈሩ…
ሰው ሰው መሽተት ምንድነው ቢባል እሳቸው ናቸው። ሁልጊዜ የሚጋባ ፈገግታ ይቸሩሃል። ከማንኛውም ሰው ጋር ያወጋሉ። ከወጣቶች ጋር ስለ ኳስ ያወራሉ።
ከታችኛው መደብ መሐል መሆንን በተግባር አሳይተዋል። በንግግራቸውም ደግሞ ደጋግሞ እንዲህ ይላሉ…[ ለድሆች የምትቆም ኩርምት ያለች ቤተ ክርስቲያን ልቤን ትማርከዋለች ]።
የወጡበትን ማሕበረሰብም አልዘነጉትም። በአርጀንቲና ዕድር ቢኖር ቫቲካን ገብቻለሁና ከአባልነት ሰርዙኝ አይሉም። ከቫቲካን ሆኖ የዕድሩን ገንዘብ ይልካሉ። ጥቃቅን የሚመስሉ ማሕበራዊ ሃላፊነቶችን ጥንቅቅ አድርጎ የሚወጡ አባት ናቸው።
ለሚደግፉት የሳን ሎሬንዞ እግር ኳስ ክለብ ሳይቀር እስከ ሕልፈታቸው ድረስ የአባልነት ግዴታቸውን የሚወጡ…መኮፈስ እና መጀነን ያልፈጠረባቸው የምር ሰው ሰው የሚሸቱ [ ሰው! ] የሆኑ አባት ናቸው።
ከሁሉ በላይ ከምንም ተነስቶ በዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ስልጣኔ እና ታሪክ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪና ጉልህ ሚና የነበራትን ሮማን ካቶሊክን መምራት መቻል ብቻውን ትልቅ የታሪክና የትርክት እጥፋት ነው። የሚታይ አሻራን አኑሮ ማለፍና በርካታ ሪፎርሞችን መከወን መቻል ደግሞ ተጨማሪ ፀጋ ነው።
በዚህ ሁሉ ያለፉት 12 ዓመታት በፈፀሟቸው ገድሎች…ለድሃ የወገነ ልቦን…ከግፋአን ጎን የቆመ ስብእናዎን..እውነትን ያለፍርሃት የተናገረ..ስለ ሰላም የጮኸ አንደበትዎን..ሰዋዊ የሆነ ሰውነትዎን…አብዝቼ…አብዝቼ.. እወደዋለሁ።
ቢሆንም…. ቢሆንም ሳልል ይህንን ፅሑፍ ቢደመደምም ምንኛ ደስ ባለኝ። ቢሆንም በአንድ ውሳኔዎ ብቻ ልቤን አሳዝኖ ቅር አሳኝቶኛል። አሁን እርሰዎ አልፎ..ነፍስዎ የእውነት ስፍራ ደርሳለችና እኔም ነገሩን በዝምታ ልለፈው።
መልካም እረፍት…..! Telaye yami
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ –
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter