ኢትዮጵያ ከመቶ ሰላሳ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ይዛ ምን ያህል በስጋት ቀጠና ውስጥ እንደምትገኝ ለመገመት ከበርካታ ምልክቶች በተጨማሪ ሰሞኑን ጅቡቲ ውስጥ ለተከታታይ ሦስት ቀን ስራ በመቋረጡ ምክንያት የተከሰተው የነዳጅ እጥረት በቂ ትምህርት ሰጭ ነው። (ሰሞኑን ስለ ነዳጅ እጥረት በመንግስት የተሰጠው መግለጫ እውነት ከሆነ ማለቴ ነው።)
ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ምክንያት የተነጠቀቸው ትልቅ ፋይዳ ለኢኮኖሚያዊ የበላይነት የሚረዳትን አቅሟን ብቻ አይደለም፤ በተለይ ሉዐላዊነቷ፣ የሕዝቦቿ ሕልውናና ጂኦ ፖለቲካዊ አቅሟን ጭምር ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ በትንንሽ ሀገራት ግራና ቀኝ ተወጥራና ታፍና የተያዘች ሚስጥር አልባ ሀገር ሆናለች።
ጅቡቲ ላይ ለረጅምም ሆነ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ውስጣዊ ግርግር፣ አለመረጋጋትና አመጽ ቢከሰት ኢትዮጵያ መፈተኗ ሳይታለም የተፈታ ነው። ጅቡቲን የደለለ መንግስት፣ ቡድን፣ ድርጅት ስለ ኢትዮጵያ ሚሊተሪ አቋም፣ ለመታጠቅ ስላሰበችውና ስለታጠቀችው ጦር መሳርያ ያሻውን ያህል መረጃ ለማግኘት እድሉ ሰፊ ነው።
ኢትዮጵያ ስለደረሰችበት የቴክኖሎጂ አቅምና ራስን የመከላከል ብቃት ወይም የደህንነት መረጃ አብጠርጥሮ የማወቅ እድሉም ሊገመት የሚችል ነው። ስለ ትኩረት አቅጣጫዋና በሚስጥር መገንባትም ሆነ ማደራጀት ስለአቀደችው ፕሮጀክት፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን መሰወርም ሆነ ማድበስበስ እንዳትችልም ሆና ተገድባለች።
ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ነባርም ሆነ ወቅታዊ ጠላቶቿ ጋር በሆነ ምክንያት ብታብር ነዳጅ፣ ጦር መሳርያ፣ መለዋወጫና የመሰረታዊ ፍጆታ አቅርቦቶች፤ መድሐኒትንና ማዳበርያን ጨምሮ ለአጭርም ሆነ ለተራዘመ ጊዜ ቀጥ ማድረግ ትችላለች። ጅቡቲ የግጭቶችን ባሕርይም ሆነ ውጤት ኢትዮጵያን በሚጠቅምም ሆነ በሚጎዳ መልክ ለመለወጥ የሚያስችል አቅም በሚፈጥርላት ስትራቴጂክ ሁኔታ ላይ እንድትገኝ ኢህአዴግ ከፍተኛ ግድፈት ( Blunder) ፈጽሟል።
ኢዴፓ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ ያደረገውንና እድሉ እያለ (ጉግል በማድረግ የሔርማን ኮህንን ቃለ መጠይቅ ማዳመጥ ይቻላል) የመደራደርያ ክፍተት ሳይተው ያዳፈነውን የኢህአዴግ ውሳኔ በመቃወም፣ የባህር በር ጥያቄ (Accesses to Sea) በዲፕሎማሲ፣ በሕግና በድርድር መፈታት አለበት የሚል አቋም ይዞ ከ20 ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ የታገለው፣ ይህንን ቀጠናዊና ሀገራዊ ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር።
ዛሬ የባህር በር ጥያቄ (Accesses to Sea) ተዳፍኖ እንዳይቀር ኢዴፓ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ፒቲሽን (የድጋፍ ፊርማ) በማስፈረምና ለተባበሩት መንግስታት በግንባር በማቅረብ፣ ሕዝብን በማንቃትና አጀንዳው ሕያው እንዲሆን በማድረግ ታላቅ ባለውለታ እንደነበር፣ ህሊና ላለው ሰው ሁሉ የሚገለጥ ሀቅ ነው።
ብልጽግና ይህንን አጀንዳ ወደ መድረክ ያመጣበት ጊዜ፣ ምክንያትም ሆነ ሰበብ ጥያቄ ላይ የወደቀ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በድርድር ላይ ተመስርታ የባህር በር (Accesses to Sea) የማግኘት መብቷ በሰላማዊ፣ በዲፕሎማሲያዊና በሕጋዊ ትግል አማካኝነት፣ በቅብብል ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ሙሼ ሰሙ- (የቀድሞ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ም/ል ሊቀመንበር)
ምንጭ addisadmasnews.com