ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 ሀገራት ሩሲያ እና ቻይና ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ የጨረቃ ምርምር ጣቢያ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት መቀላቀላቸውን፤ የብሪክስ ሀገራት (BRICS) የጠፈር ኤጀንሲ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ ለጠፈር እንቅስቃሴዎች የሩሲያ ግዛት ኮርፖሬሽን (ሮስኮስሞስ) ዋና ዳይሬክተር ዲሚትሪ ባካኖቭ አስታውቀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በስብሰባው ላይ፤ “ዓለም አቀፉን የጨረቃ ምርምር ጣቢያ ለማቋቋም ከቻይና ጋር ያለን የጋራ ተነሳሽነት በንቃት እያደገ ነው” ብለዋል፡፡
አክለውም 13 ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ሴኔጋል፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ቤላሩስ፣ ፓኪስታን፣ አዘርባጃን፣ ቬንዙዌላ፣ ታይላንድ፣ ሰርቢያ፣ ኒካራጓ፣ እና ቦሊቪያ ፕሮጀክቱን መቀላቀላቸውን ስለመግለጻቸው፤ የሩሲያ ሚዲያዎች በዛሬው ዕለት ዘግበዋል፡፡
ባካኖቭ በፕላኔቶች ፍለጋ ላይ ሩሲያ ልዩ ሳይንሳዊ አቅም እንዳላት በመጥቀስ፤ “በተለይም በቬነስ ተልዕኮዎች ላይ ሀገሪቱ ያላትን እውቀት እምቅ ነው” ብለዋል፡፡
ሩሲያ ቬኑስ፣ ጨረቃ እና ማርስን ለማጥናት ልዩ ሳይንሳዊ ትምህርት ቤቶች ያሏት ሲሆን፤ በጨረቃ ላይ ማረፊያ ቴክኖሎጂዋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አክለውም ጨረቃን እና ማርስን በማጥናት የሩሲያ ልምድ ለወደፊቱ በብሪክስ ለሚመራው ዓለም አቀፍ የጠፈር መርሃ ግብሮች የቴክኖሎጂ መሠረት ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ጠቁመዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ቻይና፣ ህንድ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በጥልቅ የጠፈር ምርምር አቅማቸው እያደገ መምጣቱን በማንሳት፤ ወደ ማርስ ያደረጉትን የተሳካ ተልዕኮ እና የጨረቃ ፍለጋ ልምድን ጠቅሰዋል። “ይህም የበለጠ ቀልጣፋ እና ኢኮኖሚያዊ የጋራ ፕሮግራሞችን ለማሳደግ ያስችላል” ብለዋል፡፡
የሩሲያ መንግሥት የሕግ አውጭ ኮሚሽን ዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ የጨረቃ ጣቢያ (አይኤስኤስ) ማቋቋሚያ ላይ ከቻይና ጋር የተደረገውን ስምምነት እ.ኤ.አ. ሕዳር 29 ቀን 2023 አፅድቋል።
እ.ኤ.አ. በግንቦት 8 ቀን 2024 የሮስኮስሞስ የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዩሪ ቦሪሶቭ፤ ሩሲያ ከቻይና ጋር በጋራ የጨረቃ ጣቢያ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ለመፍጠር ዝግጅት መጀመሯን ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ፕሮግራም በምርምር እና በመሬት የተፈጥሮ ሳተላይት ላይ ከተተገበሩ ፕሮጀክቶች ጋር ሲተገበር ቴክኒካል እና የገንዘብ እጥረት ችግሮችን ይፈታል ተብሎለታል፡፡
ከዓመት በፊት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት በህዋ ኤጀንሲዎች ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ በተሳተፈችበት ወቅት፤ ከሩሲያ ጋር በህዋ ትብብር ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም እና በጋራ ጉዳዮች ላይ ፍኖተ ካርታ ለመቅረፅ እየሰሩ መሆናቸውን የቀድሞው የሮስኮስሞስ ኃላፊ ዩሪ ቦሪሶቭ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በእዮብ ውብነህ ahadu
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter