21 ሚያዚያ 2025
በጠና ታምመው ሰንብተው ሰኞ ሚያዝያ 13 2017 ዓ.ም. ሕይወታቸው ያለፈው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ታሪካቸው ደማቅ እና ጉራማይሌ ነው።
ይህንን ቦታ ለመያዝ ከደቡባዊ ንፍቀ ክበብ መሆናቸው እንዲሁም ከአሜሪካ ክፍለ አህጉር መምጣታቸው የመጀመሪያ ያደርጋቸዋል።
ከአርጀንቲና ናቸው።
አውሮፓዊ አለመሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።
በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ከሶሪያ ተወላጁ ግሪጎሪ ሣልሳዊ በኋላ እርሳቸው ናቸው የመጀመሪያው ከአውሮፓ ያልሆኑ ጳጳስ።
ሶሪያዊው ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪያ ሳልሳዊ ያረፉት በ741 ዓ.ም. ነበር።
ለቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ጀስዊትስ ወይም ኢየሱሳዊያን ከሚባሉት ጎራ የመጡ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ናቸው። ኢየሱሳዊያን በቤተ ክርስቲያኒቱ በጥርጣሬ ነው ሲታዩ የኖሩት።
ከሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በፊት ርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳት የነበሩት ቤኔዲክት 16ኛ ናቸው። እሳቸውም በ600 ዓመት ታሪክ በገዛ ፈቃዳቸው ከጵጵስና የለቀቁ የመጀመሪያው ሊቀ ጳጳስ ነበሩ።
በቫቲካን አፀድ ለዘጠኝ ዓመታት ከኖሩ በኋላ ነበር በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት።
ታዲያ እርሳቸውና ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በአንድ ግቢ ኖረዋል። በተደጋጋሚ እየሄዱ ይጠይቋቸውም ነበር።

ቅልጥ ያሉ የ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ ነበሩ
ርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስ የጵጵስና ስማቸው ነው።
የመታወቂያ ስማቸው ጆርጅ ማሪዮ በርጎሊዮ ይባላል።
ትውልዳቸው ከአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦነስ አይረስ ነው። ወላጆቻቸው ጣሊያናውያን ናቸው። የጣሊያን ፋሺዝም ሲፋፋም ያን ሽሽት ነው ወደ አርጀንቲና የመጡት።
ከአምስት ልጆች መካከል ለወላጆቻቸው የበኩር ልጅ ናቸው።
ጆርጅ ማሪዮ በርጎግሊዮ (የአሁኑ ሊቀ ጳጳስ) በጉርምስና ዘመናቸው የሳን ሎሬንዞ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊ ነበሩ።
ታንጎ ዳንስ ነፍሳቸው ነበር።
ድሮ ክፉኛ ሳንባ ታመው ነበር። ከሞት ነው የተረፉት። ይሄ የሳምባ በሽታ ታዲያ ሕይወታቸውን ሙሉ ሲከተላቸው ነው የኖረው።
ጎረምሳው ጆርጅ ማሪዮ በርጎግሊዮ በአንድ ወቅት የምሽት ክበብ አሳላፊ ሆነው ሠርተዋል። ሥራቸውም በር ላይ ማስተናበር እና ክበቡን ማጽዳትን ይጨምር ነበር።
ከዚያ በኋላ በኬሚስትሪ ባለሙያነት ተመረቁ።
በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ከዝነኛዋ ባዮኬሚስ ኤስቴር ባሌስትሪኖ ጋር ሠርተዋል። ይቺ ሴት የአርጀንቲናን ወታደራዊ አገዛዝ በመቃወም ትታወቃለች።
በኋላ ብዙ ስቃይ ደርሶባት ተገድላለች። አስከሬኗ ደብዛው አልተገኘም።
ከዚህ በኋላ በርጎግሊዮ (ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ) ጀስዊት (ኢየሱሳዊ) ሆኑ።
ፍልፍናን፣ ሥነ ጽሑፍን እና ሥነ ልቦናን አጠኑ።

ሕይወትን ቀለል አድርገው የሚመለከቱት ጳጳስ
ገና ወደ ጵጵስናው ሲመጡ ጀምሮ ነገሮችን በተለየ መልኩ እንደሚተገብሩ ይናገሩ ነበር።
ለምሳሌ ጵጵስና ሲቀበሉ በመንበር ላይ ቁጭ ብሎ ከመቀበል ይልቅ ቆመው ነው የተቀበሉት። ይህ የተለመደ አልነበረም።
በአውሮፓውያኑ ኅዳር 13/2013 ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በቅዱስ ጴጥሮስ የቫቲካን ሰገነት ብቅ ብለው ታዩ።
ቀለል ያለ ነጭ መጎናጸፊያ ለብሰው ነበር። ለጵጵስና የመረጡት ስም በ13ኛው ክፍለ ዘመን ሰባኪ እና የእንሰሳት ወዳጅ የነበሩትን የቅዱስ ፍራንሲስ አሲሲስን ስም ነበር።
ጆርጅ ማርጎሪዮ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ ተብለው ተቀቡ።
ሽብርቅርቅ-ሽቅርቅር፣ ከልክ ያለፈ ድግስ ምቾት አይሰጣቸውም። ሰው ሰው የሚል ነገር ይመርጣሉ። ወደ ነዳያን ይቀርባሉ።
ለምሳሌ ቫቲካን ለጳጳሳት የምታቀርበውን ውድ ሊሙዚን ፊት ነስተውታል። ይልቅ ሌሎች ካርዲናሎችን በሚያመላልሰው ‘የሕዝብ አውቶቡስ’ መሳፈርን መርጠዋል።
በዚህ ቀለል ያለ የሕይወት ዘይቤያቸው ከ1.2 ቢሊዮን ለሚልቁ ምዕመኖቻቸው ምሳሌ ለመሆን ሞክረዋል።
“ለድሆች የምትቆም ኩርምት ያለች ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደምትማርከኝ” በሚለው አነጋገራቸው ይታወቃሉ።

በሊቀ ጳጳሱ ላይ የተሰነዘሩ ነቀፌታዎች
ተወዳጅ የሆኑትን ያህል ነቀፌታም አላጣቸውም።
የወግ አጥባቂነታቸውን ያህል ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተገፉትን በማቅረብም ይታወቃሉ።
ጥብቅ የቤተ ክርስቲያን ሕግጋትን በሚከተሉት ጳጳሳት የሚመረጡትን ያህል ለዘብ ያለ አመለካከታቸውም ልዩ ያደርጋቸዋል።
ለምሳሌ ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ያሳዩት ርህራሄ እዚህ ይጠቀሳል።
በታሪካቸው ጥቁር ጠባሳ ተብሎ የሚነሳው አርጀንቲና ካርዲናል ሳሉ ለወታደራዊው መንግሥት አጎብድደዋል የሚለው ክስ ነው።
በተለይም በወታደራዊው አገዛዝ ታፍነው ለተወሰዱት እና ብዙ ስቃይ ላሳለፉት ሁለት ቀሳውስት የፍራንሲስ እጅ አለበት እየተባሉ ይከሰሳሉ።
ይህ በአርጀንቲና ”ቆሻሻው ጦርነት” (Dirty War) ዘመን የሆነ ነው። እንደ አውሮፓዊያኑ ከ1976 እስከ 1983 ብዙ ሺህ አርጀንቲናውያን ደብዛቸው ጠፍቷል።
ሁለቱ ቀሳውስት ግን ከፍተኛ ስቃይ ከደረሰባቸው በኋላ ከፊል እርቃናቸውን ሆነው ተጥለው ተገኝተዋል።
በርጎግሊዮ (የአሁኑ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ) ያኔ ዝምታን መርጠዋል በሚል ነው የሚተቹት።
እርሳቸው ግን ከመድረክ ጀርባ ብዙ ሠርቻለሁ እንዲለቀቁ፣ አልሆነልኝም እንጂ ይላሉ።
ለምን በይፋ አልተናገሩም ሲባሉ ደግሞ ”ያኔ በይፋ መናገር በጣም ከባድ ነበር” ሲሉ ይመልሳሉ።
ይሁንና በዚያ ዘመን ብዙ ሰዎች ከአሰቃቂው ወታደራዊ አገዛዝ እንዲሸሹ ዕድሎችን አመቻችተዋል።
ፍራንሲስ ቀለል ያለ ሕይወት ነው የሚመርጡት።
ከድሮም ጀምሮ ለምሳሌ በአውሮፕላን ሲጓዙ በአንደኛ ደረጃ ማዕረግ ክፍል ውስጥ አይበሩም። ከተራው ሕዝብ ጋር (ኢኮኖሚ ክፍል) ነው የሚሳፈሩት።

ለድሃው ድምጽ በመሆንም ይታወቃሉ
ከዚህ ባሻገር ከአንግሊካን ሉተራን እና ሜቶዲስት እምነት መሪዎች ጋር በጋራ መሥራታቸው ያስመሰግናቸዋል።
የእስራኤል እና የፍልስጤም መሪዎችም በመሩት ፀሎት ላይ በጋራ እንዲገኙ ማደረጋቸውም ተደንቆላቸዋል።
በአክራሪ ሙስሊም ጥቃቶች ምክንያት እስልምናን ማውገዝ ልክ አለመሆኑን መናገራቸውም የሚጠቀስ ነው።
“ስለ ኢስላማዊ ጥቃት ከተናገርኩ ካቶሊካዊ ጥቃቶችም ስላሉ እሱንም መናገር ይኖብኛል” በሚለው አገላለጻቸው ብዙዎች አይዘነጓቸውም።
ማንኛውም ጥቃት፣ ጥቃት አድራሹን እንጂ ሃይማኖትን እንደማይወክል አስተምረዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ ወግ አጥባቂም ናቸው።
ልክ እንደ ሊቀ ጳጳስ ዳግማዊ ጆን ፖል በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የማያወላዳ አቋም አላቸው። ለምሳሌ በሐኪም እርዳታ በፍቃድ የሚፈጸም ሞት (euthanasia) እና ጽንስ ማቋረጥን በመቃወም ጽኑ አቋም አላቸው።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንንም ቢሆን እጇን ዘርግታ ነው መቀበል ያለባት ይላሉ።
ይሁንና በሁለት ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ልጅን በጉዲፈቻ ማሳደግ ሕጻናትን መበደል ነው ይላሉ።
ሴት ቀሳውስት ጳጳሳት ሆነው ሊሾሙ አይገባም የሚል አቋምም አላቸው።
የእርግዝና መከላከያ መጠቀምንም ያወግዛሉ።
በአንድ ወቅት በፍሊፒንስ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር “የእርግዝና መከላከያ ቤተሰብን የሚያፈርስ ነው” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በዘመናቸው ትልቁ ፈተና የሆነባቸው በዓለም ዙርያ በቀሳውስት ተፈጽመዋል የሚባሉ የሕጻናት መደፈሮችን በበቂ አልተከላከሉም የሚል ነው።
ይህን በተመለከተ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ የቆዩት የአሜሪካው ካርሎ ማሪያ ቪጋኖ በጳጳሱ ላይ የውግዘት ደብዳቤ እስከመጻፍ ደርሰው ነበር።
ጳጳሱንም በኑፋቄ እስከመክሰስ ደርሰው ያውቃሉ።
ይህን ሊቀ ጳጳሱ በሕጻናት ደፋሪዎች ላይ ፈጣን እና ተገቢ እርምጃ አልወሰዱም በሚል ነበር።
ሊቀ ጳጳስ ቪጋኖ ከአውሮፓውያኑ 2011 እስከ 2016 በዋሽንግተን የጳጳሱ መልዕክተኛ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ የቤተክርስቲያኗ ቀደምት አባት ነበሩ።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ 140 ካርዲናሎችን ከዚህ ቀደም ባልተመደ ሁኔታ ከአውሮፓ ውጪ ከሆኑ አገራት ሾመዋል።
የድሆች አባት የሚባሉት ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ለበርካታ ሳምንታት በጽኑ ታመው ሆስፒታል የሰነበቱ ሲሆን፣ ከሳምንት በፊት ነበር አገግመው ወደ መኖሪያቸው የተመለሱት።
በሕክማናቸው ወቅት ከሕዝብ ዓይን ርቀው የሰነበቱት ጳጳሱ የፋሲካ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ቃለ ቡራኬ ሰጥተው የትንሳዔ ምልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በበፋሲካ ማግስት በ88 ዓመታቸው ማረፋቸውን የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማዕከል ከሆነችው ቫቲካን ሰኞ ረፋድ ሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም. ይፋ ተደርጓል።
ቢቢሲ አማርኛ
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview / ኤክስ ፡ twitter