የፋይዳ ዲጂታል ብሄራዊ መታወቂያ ጥቅም ገና ያልተገለጸላቸው ብዙ ናቸው፤ ቢገባቸውን ፍላጎት የማያሳዩም በርካቶች ናቸው፤ ይህን ዓለም ድሮ የጨረሰውን አሰራር “ስለላ ነው” በሚል የሚቃወሙ ተቃዋሚዎችም አሉ፤ አውሮፓና አሜሪካ በተመሳሳይ መታወቂያ ወደውና ፈቅደው የሚኖሩ አይናቸውን አጥበው ሲተቹ ይሰማል።
” ከዚህ ቀደም አንድ ሰው አንድ ነው የሚለውን ማረጋገጥ ባለመቻላችን በሁለት በሦስት ማንነት መታወቂያ ማውጣት፤ የታክስ ማጭበርበር እንዲሁም በተጭበረበረ ማንነት የንብረት ቅሚያ ይከናወን ነበር ” ይላሉ በም/ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ለአገልግሎቶች ግንዛቤ ማስጨበጫ በተዘጋጀ መድረክ ላይ፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ስም መታወቂያ ያወጣ ሰው ዳግም በዛ ስም መታወቂያ የማያወጣበትን ሥርዓት መፈጠሩን አስታውቀው በሲቪል ምዝገባ ረገድ እየተሰራ ያለውን ስራ ጠቀሜታ አስመልክቶ ስለላው ግንዛቤ ያወሳሉ።
አብዛኛው ሰው የፋይዳ መታወቂያ የሚመዘገበው በአስገዳጅ መልኩ መሆኑን ሲገልጹ ኢንጂነር ወንድሙ ይህ መሆን ያልነበርበት እንደሆነ በማመላከት ነው፤ ” ለምንድነው ፋይዳ የማትመዘገበው ?” ሲባል “ምን ያደርግልኛል” የሚል ሰው በጣም ብዙ መሆኑን ያመለከቱት ባለስልጣኑ፣ ከፋይናንስ፣ ከታክስ፣ ከቤት ኪራይ፣ ከመንጃ ፈቃድ፣ ከንብረት ባለይዞታነት አገልግሎት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ የስበት ማዕከል መሆኗን በመጥቀስ ህጋዊ ያልሆኑ ፍልሰቶች መኖራቸው በከተማው መሰረተ ልማት ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
” አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን ሰው ማወቅ አለብን ፤ በአግባቡ የተመዘገበ መሆን አለበት። የአዲስ አበባ አስተዳደር አገልግሎት የሚያቀርበው ለምን ያህል ሚሊዮን ነዋሪ እንደሆነ መታወቅ አለበት” ብለዋል።
ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ሰዎች የተመዘገቡ መሆን እንድለባቸው ሲያወሱ፣ ” በአንድ ቦታ ወንጀል ሰርቶ የመጣ ሰው አዲስ አበባን መደበቂያ ማድረግ የለበትም፤ ከተማ አስተዳደሩ ያወቀው ነዋሪ መሆን አለበት። ያንን ማድረግ የሚያስችል ሥራ እየሰራን ነው ያለነው ” ሲሉ የፋይዳ መታውቂያን ጠቀሜታ ከአገልግሎት በዘለለም ገልጸዋል።
አስገራሚ ጉዳይ የተባለውና እሳቸውም በግልጽ ያነሱት በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እየተከናወነ ያለው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጉዳይ ነው። ለሚቀጥለው ዓመት የትምህርት ዘመን ምዝገባ የፋይዳ መታወቂያ በመስፈርትነት በማስቀመጥ ለዚህም በአንድ ወር ውስጥ 450 ሺ ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ ስራ ቢጀመርም መመዝገብ የተቻለው 130 ሺ የሚሆኑትን መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
” ወላጆች የተሟላ መረጃ አይልኩልንም ” ያሉት ኢንጂነር ወንድሙ አንዳንዶቹ ለራሳቸውም የፋይዳ መታወቂያ የሌላቸው መሆኑን በመጥቀስ የግንዛቤ እጥረት ለሥራው ፈተና መሆኑን አንስተዋል። ይህን መግለጫቸውን ተከትሎ አዲስ አበባ አድራሻ የሌላቸውና መታወቂያ እንዲያወጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ያልሰጡ በመጪው ዓመት ምዘግባ ምን ምላሽ ሊሰጡ ነው?
በተመሳሳይ ከሞት እና ጋብቻ ሰርተፊኬት ጋር ተያይዞ የማስመዝገብ ባህሉ ደካማ መሆኑን በማንሳት በተለይ ከሞት ምዝገባ ጋር ተያይዞ ከሃይማኖት ተቋማት ጋር አብሮ በመስራት እዛው ሰርተፊኬት የሚያገኙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው ብለዋል።
የጀርመን ድምጽና ቲክቫህ ከዘገቡት ተዋህዶ በተጠናከረው ዘገባ ለማሳየት የተሞከረው የፋይዳ መታወቂያ አስመልክቶ ያለውን መንሸዋረር ነው፤ ፋይዳ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ዲጅታል መታወቂያ በተለመደው መንገድ በካርድ መልክ የሚቀርብ ሳይሆን ዲጅታል በሆነ የመለያ ቁጥር ማንነትን ለመለየት የሚያስችል ነው። ይህ ፋይዳ ቁጥር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግል መረጃዎችን አንድ ላይ የያዘ እና እያንዳንዱን ግለሰብ ማንነት የሚለይ ነው።

ፋይዳ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ
በነጮቹ አቆጣጠር 1983 ዓ/ም በዓለማችን የበይነመረብ መምጣትን ተከትሎ በርካታ አገልግሎቶች ከነባሩ የወረቀት አሰራር ወደ ዲጅታል ተለውጠዋል።ከነዚህም መካከል ዲጅታል የሆነ የማንነት መለያ አንዱ ነው። የዲጅታል የማንነት መለያ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት ስራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ በኢትዮጵያም ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ ይህ ዲጅታል መታወቂያ በሙከራ ላይ ነበር።
በመጋቢት 2015 ዓ/ም ግን በአዋጅ ደረጃ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል። ፋይዳ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ዲጅታል መታወቂያ የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ ከሙከራ ወደ ትግበራ ተሸጋግሯል።በቅርቡ ደግሞ ይህን ዲጅታል መታወቂያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ዋና አስተባባሪ አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ ገልፀዋል።
ወደዚህ ዲጅታል ስርዓት ስንገባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰርተናል የሚሉት ሀላፊው፤ ኢትዮጵያ ይህንን መታወቂያ አገልግሎት ላይ በማዋል የመጨረሻ ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።
ምንም እንኳ ይህንን መታወቂያ ወደ አገልግሎት ለማምጣት ኢትዮጵያ የዘገየች ቢሆንም እንደ አቶ ዮዳሄ ገለፃ መታወቂያውን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተሳሰር ጥሩ እድል ፈጥሯል።

ግንዛቤ ከማስጨጥ በተጨማሪ አዋጁም ቢሆን ዲጅታል አገልግሎቶችን ከዚህ መታወቂያ ጋር ማስተሳሰርን እንደሚፈቅድ ሃላፊው ጠቅሰዋል።ከተወሰነ ወራት በኋላ ብሄራዊ ባንክ ከነባር እና ከአዲስ ደንበኞቹ የባንክ አካውንት ጋር ለማስተሳሰር በአራት የተከፈለ የአተገባበር መርሃ ግብር ማውጣቱን ገልፀዋል።
አዲስ አበባ ከተማ አዲስ ለሚከፍቱ የባንክ ደንበኞች ዲጅታል መታወቂያ የግድ ሲሆን፤ከሶስት ወር በኋላም ክልሎች ይሄው ግዴታ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።በአጠቃላይ ከአንድ አመት በኋላ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ የባንክ አካውንት ማውጣት እና አገልግሎት ማግኘት ያለዚህ መታወቂያ ቁጥር የማይቻል ይሆናል።ይህም እንደ አቶ ዮዳሄ ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ስርዓት እንዲኖር ጠቃሚ ነው ።
የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ በተለመደው መንገድ በካርድ መልክ የሚቀርብ ሳይሆን ዲጅታል በሆነ የመለያ ቁጥር ማንነትን መለየት የሚያስችል ነው። ይህ ፋይዳ ቁጥር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግል መረጃዎችን አንድ ላይ የያዘ እና እያንዳንዱን ግለሰብ ማንነት የሚለይ ነው።ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥነት ያለው ነው። ፋይዳ መታወቂያ በአዋጁ መሰረት የአንድን ሰው ማንነት ለማረጋገጥ እንደ ሕጋዊ እና በቂ ማስረጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ያም ሆኖ በየአካባቢው ከሚሰጡ የቀበሌ መታወቂያዎች በአገልግሎቱ የተለዬ መሆኑን አስረድተዋል።ነገር ግን ሁለቱን ማስተሳሰር እንደሚቻል ገልፀዋል።
አቶ ዮዳሄ እንደሚሉት ፋይዳ በዕድሜም ሆነ በዜግነት ገደብ ያልተደረገበት ዲጅታል መታወቂያ ነው።በመሆኑም ይህንን ዲጅታል መታወቂያ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች እንኳ ወላጆቻቸው ሊያወጣላቸው ይችላል።ከአምስት ዓመት በላይ ለሆኑት ግን አሻራቸውን ሰጥቶ የፋይዳ ቁጥር ማግኘት ይቻላል። ከ18 ዓመት በላይ ሲሆኑ ደግሞ ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ መሠረታዊ የግል መረጃን በመስጠት ማንኛውም ሰው ይህንን ዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት ያለው ቢሆንም፤ ቋሚ አድራሻ የሌላቸው ሰዎች ግን መውሰድ አይችሉም።
በሌላ በኩል ይህ መታወቂያ የአንድን ሰው ስም እና የመኖሪያ አድራሻን ጨምሮ በርካታ የግል መረጃዎችን የያዘ በመሆኑ ለመረጃ ምንተፋ እና ባልተገባ ሁኔታ ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል የመረጃ ደህንነት ስጋት ይነሳል።አቶ ዮዳሄ ግን በህግም በቴክኖሎጅም በሁለት መንገድ የመረጃ ጥበቃ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
ዲጅታል አገልግሎት ሲነሳ የበይነመረብ እና የዲጅታል መሰረተ ልማት እጥረት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት የሚነሳ ችግር ነው።አቶ ዬዳሄ እንደሚሉት ግን ያለበይነመረብ መስራት የሚያስችል በመሆኑ በዚህ ዲጅታል መታወቂያ ምዝገባና አገልግሎት ላይ እንቅፋት የለም።
በኢትዮጵያ አሁኑ ወቅት 13 .5 ሚሊዮን ሰዎች የመታወቂያው ተጠቃሚ ናቸው። ከተለያዩ አጋሮች ጋር የምዝገባ ስራው በተለያዩ አካባቢዎች የእየተካሄደ መሆኑን የሚገልፁት ሀላፊው፤ እስከ 2018 ዓ/ም መጨረሻ የተጠቃሚውን ቁጥር ቢያንስ 70 ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ ተይዟል።
ፋይዳን ፤መውሰድ በአዋጁ መሰረት አስገዳጅ ባይሆንም በርካታ ተቋማት አገልግሎታቸውን ከፋይዳ ጋር መታወቂያ ጋር የሚያስተሳስሩ ተቋማት እየጨመሩ በመጡ ቁጥር ግን ያለዚህ ዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ይመጣል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ተቋማት አገልግሎታቸውን በማስተሳሰር አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳ መታወቂያን አስገዳጅ ማድረግ ጀምረተዋል።በመሆኑም ተጠቃሚዎች መታወቂያውን ከወዲሁ እንዲያወጡ አቶ ዬዳሄ አሳስበዋል።