የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ “ሲም ካርድ በመጠቀም ፈንጂዎችን በማፈንዳት የህብረተሰቡን ሰላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ሶስት ተጠርጣሪዎች” ይዣለሁ ሲል ገለጸ።
ተጠርጣሪዎች ገበያ ስፍራዎች በትምህርት ቤቶችና እንዲሁም ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ፈንጂዎችን በማጥመድ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ዝግጅት እንደነበራቸው ባደረገው ምርመራ ማረጋጋጡን የመምሪያው ኃላፊ አቶ አለልኝ ዓለም ትላንት ሚያዚያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ፍንዳታውን የሚያካሂደው በፈንጂው ላይ በሚታሰር የሞባይል ቀፎና ሲም ካርድ በመታገዝ ወደ ሲም ካርዱ በመደወል ፍንዳታውን በርቀት ሆነው እንደሚያካሂዱ እንደተደረሰበትም አስረድተዋል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አለልኝ ዓለም በመግለጫቸው ተጠርጣሪዎቹ ከቀናት በፊት ምሽት ላይ በከተማው አንድ ፖሊስ ጣቢያና በክፍለ ከተማ ጽህፈት ቤት ላይ ፈንጂ በማፈንዳት ተሰውረው የቆዩ ናቸው ማለታቸውን ከከተማዋ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
የፀጥታ መዋቅሩ ባደረገው ጥብቅ ክትትልና ስምሪት ተጠርጣሪዎቹ ሌላ የሽብር ተልእኮ ለመፈጸም በአንድ የግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በድብቅ ካዘጋጁዋቸው የፈንጂ መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል ማለታቸውንም መረጃው አካቷል።
Source አዲስ ስታንዳርድ
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter