የሩዋንዳ የዘር ፍጅት እጅግ አስከፊ የኾነ የጅምላ ጭፍጨፋ ነው። በ1994 በሩዋንዳ ውስጥ በዚህ ሳምንት በጽንፈኞች የተጀመረ ክስተት ነበር።
በ100 ቀናት ውስጥ ከ800,000 በላይ የሚገመቱ ሰዎች፣ በአብዛኛው የቱትሲ ብሔረሰብ አባላት በሁቱ አክራሪዎች እንደተገደሉ ይታመናል። የዘር ፍጅቱን የተቃወሙ መጠነኛ የሁቱ ሰዎችም ዒላማ ተደርገው ተገድለዋል።
ይህ የዘር ፍጅት የተቀሰቀሰው የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሃብያሪማና በአንድ ሁቱ ሚያዝያ 1994 አውሮፕላናቸው በጥይት ተመትቶ ሲወድቅ ነበር። የዚህ ክስተት ትክክለኛ ኹኔታ አሁንም አከራካሪ ቢኾንም፣ የሁቱ አክራሪዎች በፍጥነት የቱትሲ አማጺ ቡድን የኾነውን የሩዋንዳ አርበኞች ግንባርን (አርፒኤፍ) ተጠያቂ አድርገው ይህንን እንደ ምክንያት በመጠቀም የጅምላ ግድያውን ጀምረውታል።
ግድያው እጅግ በጭካኔ የተከናወነ ነበር። ተጎጂዎች ብዙውን ጊዜ በሰይፍ እና በሌሎች ቀላል መሣሪያዎች ይገደሉ ነበር። ዜጎች በሬዲዮ እና በሌሎች ሚዲያዎች በተሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ግድያውን እንዲሳተፉ ይበረታቱ ነበር።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዚህ የዘር ፍጅት የሰጠው ምላሽ ዘግይቷል እና በቂ አልነበረም ተብሎ በሰፊው ተተችቷል። በወቅቱ በሩዋንዳ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኀይልም ሥልጣን እና በቂ ሀብት ስላልነበረው ውጤታማ በኾነ መንገድ ጣልቃ ለመግባት ሳይችል ቀርቷል።
የዘር ፍጅቱ የተጠናቀቀው በሐምሌ ወር አጋማሽ 1994 በአርፒኤፍ ፖል ካጋሜ መሪነት ሀገሪቱን በመቆጣጠር ወንጀለኞቹ እንዲሸሹ ባስገደደ ጊዜ ነበር።
የሩዋንዳ የዘር ፍጅት በሩዋንዳ ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት፣ ሰፊ የሥነልቦና ጉዳት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀልን ያስከተለ ቢኾንም በእርቅ ለመፍታት ውጤታማ ሥራ የተሠራበትም ነው።
አሁን ላይ ሩዋንዳውያን ከነበረው ኹነት ተምረው ዳግም ወደ እንደዚህ አይነት ኹኔታ ላለመመለስ ተማምለው ወደ ሀገር ማልማት ገብተዋል። በምንጭነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የተለያዩ የዓለማቀፍ ሚዲያዎችን ተጠቅመናል።
👉‹‹ድል ከሞት በኋላ››
የብዙ ሙያ ባለቤት የነበሩት ብርሃኑ ዘሪሁን በተለይም በመምህርነት፣ በትርጉም፣ በጋዜጠኝነትና በደራሲነት ሙያቸው ይታወቃሉ።
ከልጅነታቸው ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ የነበሩት ብርሃኑ ዘሪሁን በተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት አንደኛ በመውጣት ተሸልመዋል።
በዚያው ትምህርት ቤት መምህር ኾነው ያገለገሉ ሲኾን የውጭ መጻሕፍትን በመተርጎም እንዲኹም በተለያዩ ጋዜጦች በጋዜጠኝነት በመሥራት ሙያቸውን አዳብረዋል። በተለይም የአንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመኾን ትልቅ አበርክቶ ነበራቸው።
ብርሃኑ ዘሪሁን በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ያበረከቱ ደራሲ ሲኾኑ ከእነዚህም መካከል 11 ልብ ወለድ ድርሰቶች እና ሦስት ተውኔቶች ይጠቀሳሉ።
‹‹የእንባ ደብዳቤዎች››፣ ‹‹ድል ከሞት በኋላ››፣ ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› እና የማዕበል ተከታታይ ልብ ወለዶች (‹‹ማዕበል የአብዮት ዋዜማ››፣ ‹‹ማዕበል የአብዮት መባቻ›› እና ‹‹ማዕበል የአብዮት ማግስት››) ከታወቁ ሥራዎቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ። በተለይም ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› ስለ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ያልተነገሩ ታሪኮችን በማንሳት ትልቅ ተቀባይነትን አግኝተዋል።
የማዕበል ተከታታይ ልብ ወለዶች በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተከታታይ መጻሕፍትን በማሳተም ረገድ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ የመጀመሪያው ሥራ በመኾኑ ብርሃኑን ፈር ቀዳጅ አድርጓቸዋል።
እኝህ ባለውለታ ሰው በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 16/1979 ዓ.ም ነበር ያረፉት። ምንጭ፦ ኖርዌያዊው ሩዶልፍ ሞልቬር በኢትዮጵያ ደራሲያን ታሪክ ላይ ከጻፉት መጽሐፋቸው የተወሰደ።
👉”ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ”
ገጣሚ፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህር እና የሥነ ጽሑፍ ተመራማሪው ደበበ ሰይፉ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ሰፊ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰው ናቸው።
በግጥም ሥራዎቻቸው የታወቁ እና ተወዳጅ ገጣሚም ነበሩ። “የብርሃን ፍቅር” የተሰኘው የግጥም መድብላቸው እና “ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ” የተሰኘው ሁለተኛ የግጥም መጽሐፋቸው ለተወዳጅነታቸው በማሳያነት የሚነሳላቸው ነው።
በዘመናዊ የሂስ ጥበብ ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበሩት እኝህ ሰው ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ በመተንተን እና በመዳኘት የሂስ ጥበብን በማሳደግ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
በትያትር ጥበብ መምህርነት እና ተንታኝነታቸው የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። የመድረክ ሥራዎችን እና የትያትር ጽሑፎችን በመተንተን ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦም አድርገዋል።
አዳዲስ የአማርኛ የሥነ-ጽሑፍ ቃላት ፈጣሪም ነበሩ። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የነበሩ የሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በመተርጎም (“ገፀ ባህርይ”፣ “ሴራ”፣ “መቼት”፣ “ቃለ ተውኔት” ) የአማርኛን ሥነ-ጽሑፋዊ ቋንቋ አበልጽገዋል።
ለትያትር ትምህርት ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦም አበርክተዋል። “የቴአትር ጥበብ ከጸሐፌ ተውኔቱ አንፃር” የተሰኘውን መጽሐፍ በ1973 ዓ.ም. በማሳተምም ለትምህርቱ መሠረት ጥለዋል።
በርካታ ተውኔቶችን የጻፉ እና የተረጎሙ ድንቅ ፀሐፌ ተውኔትም ነበሩ። “ከባሕር የወጣ ዓሣ”፣ “እናትና ልጆቹ”፣ “ማክቤዝ” እና “ጋሊሊዮ ጋሊሊ” ከታወቁት ሥራዎቻቸው ጥቂቶቹ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ በመኾን በርካታ የምርምር ሥራዎችንም አከናውነዋል። እንዲሁም በሥነ-ጽሑፍ ማኅበራት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመኾን ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦም አድርገዋል። እኝህ ባለውለታ ሰው ሚያዚያ 16/1992 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር ያረፉት። ምንጭ፦ አዲዘመን ጋዜጣ
Via አሚኮ
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter