ዘንድሮ በተጀመረው የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን መሠረት ከመጠነኛ ስህተት እስከ ከባድ የንግድ ጥሰት ያከናወኑ ከ250 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርገዋል ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ዘንድሮ የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሥራ ተጀምሯል፡፡ ይህም ማለት የተወሰደው የንግድ ፈቃድ እየዋለ ያለው ለምን አይነት ተግባር ነው በሚል የንግድ ፈቃዱ ቁጥጥር (ኢንስፔክት) የሚደረግበት አሠራር ነው፡፡ በዚህም የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሥራ ከመጠነኛ ስህተት እስከ ከባድ የንግድ ጥሰት የፈጸሙ ከ250 ሺህ በላይ ነጋዴዎችን ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ካሣሁን (ዶ/ር)፣ ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን የሚደረገው ዋናው ምክንያት አጭበርባሪነት፣ ሌብነትን እና በዚህ ደረጃ የሚደረጉ የንግድ ማጭበርበሮችን ማስወገድ ስለሚያስችል ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ካሣሁን (ዶ/ር) ገለጻ፤ ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን እስከ 2016 በጀት ዓመት ድረስ በኢትዮጵያ ሲከናወን ቆይቷል፤ ሲከናወን የነበረው ግን በፌዴራል ደረጃ የተሰጠ ንግድ ፈቃድ ብቻ ላይ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከመቶ ሺህ የማይበልጥ ነጋዴ ቁጥር ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የንግድ ማኅበረሰቡ ዘንድ በመድረስ የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ማከናወን ተችሏል፡፡
በዚህም የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሥራ ከፈቃድ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮችን ማስተዋል ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህም የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ ከ250 ሺህ ነጋዴዎች በላይ ከመጠነኛ ስህተት እስከ ከባድ የንግድ ጥሰት በማከናወናቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህ አሠራር በ2016 በጀት ዓመት ላይ ያልነበረ እና በ2017 በጀት ዓመት ላይ የተከልነው የንግድ ፈቃድ ኢንስፔክሽን የተወሰዱት ፈቃዶች ለምን አገልግሎቶች እየዋሉ ነው የሚለውን የመለሰ ትልቅ ሥራ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ካሣሁን (ዶ/ር) ተናግረዋል፤ ይህ የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን ሥራ ከፈቃድ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ አሠራርን በማዘመን፤ ግልጽ፣ ተደራሽ እና ፍትሐዊ ውድድር የሰፈነበት እንዲሆን በማድረግ፤ ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር፤ ወጪ ንግድን በማስፋፋትና በማሳደግ፤ የእቃዎችን የጥራት ደረጃ በማዘጋጀትና በመቆጣጠር የሸማቹን፣ የንግዱን ማኅበረሰብና የሀገርን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የንግድ ሥርዓት መገንባት ተልዕኮው አድርጎ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter