የቤት ውስጥ ባሪያው ማን ነው? በእውነት አቶ አንዳርጋቸው ይህን የማለት ሞራል አለውን?
የውጭ ባሪያውስ…?
“ትቸው ረስቸው” ይላል ጋሽ አሰፋ ጫቦ አንድን የቆየ ነገር አስታውሶ ሲተርክ። ጋሽ አሰፋ ስለ ጋሞ በአጠቃላይ ስለ ጨንቻ እና ብርብር ማርያም በተለይ በገራሚ ብዕሩ ያስኮመኮመን “ትቸው ረስቸው” እያለ ነበር። በአሰፋ ጫቦ ትረካ የጨንቻን ጉም ለመጨበጥ ያልቋመጠ አንባቢ ካለ አሰፋን ያላነበበ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። የአሰፋን ትረካ ለሌላ ጊዜ እናቆየውና ትቸው ረስቸው ያስባለኝን ጉዳይ በአዲስ አንቀፅ ልቀጥል..!
አንዳርጋቸው ፅጌ በጣም እልኸኛ ሰው ነው። ከእልሁ የተነሳ ምላጭ ሊውጥ የሚችል ሰው እንደሆነ “የታፋኙ ማስታወሻ” የሚለው መፅሃፉ አስረጅ ነው። በዚህ አጋጣሚ መፅሃፉን እንድታነቡት እጋብዛለሁ። ድንቅ መፅሃፈ ነው።
አንድ ቀን ጋሽ አንዳርጋቸው ይደውልልናል። በአስቸኳይ ላገኛችሁ እፈልጋለሁ አለን። በለጠ እኔ እና የሱፍ ሆነን ኃያት ሪጀንሲ ሆቴል አገኘነው።
ሰውየውን በአንድ ወቅት አድናቂው እና ተከታዩ ሆነን ህይዎታችን ሊያስነጥቀን የሚችል እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉ ገብተን ነበር። ከየመን ተይዞ በመጣ ወቅት ማለቴ ነው። እንደተገናኘን ብዙም ሳንቆይ ሰውየው መብሰክሰኩን ቀጠለ። ባሏ ትቷት የሰፈር ኮረዳ እንዳፈቀረ ሴት ያለ መብሰክሰክ። ምን እንደሚያብሰከስከው እና ለምን በአስቸኳይ ላግኛችሁ እንዳለን ለማወቅ ጓጉተናል። ስለሆነ ወንበር እንደያዝን በቶሎ ጠየቅነው…ምንድን ነበር የተገናኘንበት ጉዳይ ጋሽ አንዳርጋቸው?
“የሰውየውን አደገኛ አካሄድ ለአንዳንድ ሰዎች በወቅቱ ነግሬያቸው ነበር። ሰውየው መልዕክት ልኬለት አይመልስም። መልዕክቴንም አይቶታል። የዋትስ አፕ ሜሴጁ ሰማያዊ ቲክ ያሳያል። ከዚህ በፊት ሁለቱን መፅሃፎቹን ኤዲት ያደረኩለት እኔ ነበርኩኝ። ሶስተኛውን ግን እኔ ሳላየው ነው ያሳተመው። አንድ ምክር አዘል ፅሁፍ ልኬለት አልመለሰልኝም። ይኸን ሰው በጊዜ ማባረር አለብን” አለ። ጋሽ አንዳርጋቸው የሚያወራው ስለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ነው።
እርስ በርስ ተያየን…። እውነት ለመናገር የማላከብረው ሰው ቢሆን ኖሮ ሳቄን ለማፈን አልታገልም ነበር። ከትከት ብየ ሆቴሉን የሞላው ሰው ሁሉ እስኪታዘብ እስቅ ነበር።
ጋሽ አንዳርጋቸው በዚያ ሰሞን የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ከአንዳንድ ሰዎች ሰምቸ ስለነበረ ብዙም አዲስ አንሆነብኝም። ከዚህም ተነስቸ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሰነዘርኩኝ።
የአንተን ፅሁፍ ስላልመለሰ ብቻ ነው የሚባረረው ጋሸ? አልኩት በአግራሞት እና በትዝብት፣
ወዲያውኑም ህይዎታችንን የሚያስነጥቅ እንቅስቃሴ ውስጥ የከተተን ሰው እንዲህ ግለሰባዊ በሆነ ደም ፍላት እንደሚወስን ባወቅኩኝ ጊዜ እንዲህ ያለውን የግለሰቦች ስሜት ለማስተናገድ ስንት የሐገሬ ልጆች ህይዎታቸውን ገብረው ይሆን? እያልኩኝ ተብሰለሰልኩኝ። ሃተታውን ቀጠለ ጋሽ አንዳርጋቸው…! አንዳች ፍርሃት እና አለመረጋጋት ተጭኖታል። He was extremely desperate. ቢሆንም ቀጠለ…!
“አንዳንድ በመዋቅሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች አብረውን ይሰራሉ። እነዚህን ሰዎች ይዘን መንግስትን መጣል አለብን። ሻውቢያዎች በደንብ አኩርፈዋል። ከኤርትራ ጋር ጦርነት የማይቀር ጉዳይ ነው። ሻዕቢያ በቀላሉ ሞብላይዝ የሚደረግ ኃይል አለው። የእኛ ኃይል ሲጨመር ነገሩ የጥቂት ቀናት ጉዳይ ይሆናል” አለን። ከሻዕቢያ ሰዎች ጋር ተነጋግሬያለሁ። ውጭ አገር እንድንገናኝ ተቀጣጥረናል። ከሰሞኑ ከሐገር እወጣለሁ። እዛ ተገናኝተን በሚያደርጉልን እርዳታ ሁኔታ ላይ እንነጋገራለን።
ኢትዮጵያ እኮ ትልቅ አገር ነች፣ ኤርትራን በምታክል እዚህ ግባ በማትባል ድሃ አገር እንዴት ልትሸነፍ ትችላለች? ብለን ጠየቅነው። የሰውየው መልስ “ኤርትራ በቀላሉ ሞብላይዝ ማድረግ የምትችለው ህዝብ አላት። ኢትዮጵያ ግን የላትም” ነበር። እኔ በደንብ አውቃቸዋለሁ አይነት ነገር። ከዚህ ተነስቸ “የቤት ባሪያ” ለሚለው ከሽማግሌ የማይጠበቅ ዘለፋው የውጭ ባሪያ ማለት አልሻም። ምክንያቱም ጋሽ አንዳርጋቸው ትልቅ ሰው ስለሆነ…! ፍርዱን አንባቢ ይስጥ።
የጋሽ አንዳርጋቸውን አብን እና ኢዜማን ይዘን ህዝቡን ሞብላይዝ በማድረግ በሻዕቢያ እርዳታ የኢትዮጵያን መንግስት መውጋት አለብን የሚለውን እቅዱን አልተቀበልነውም። “ኢዜማ ከሰሞኑ ብርሃኑን ያባርረዋል። ከውስጥ ያሉ ሰዎች ጋር ጨርሰናል። ለኢዜማ ሰነድ የምፅፍላቸው እኔ ነኝ። ብርሃኑን እንዴት ማባረር እንዳለባቸው እና ከህዝብ ጋር እንዴት መወገን እንዳለባቸው ሰነድ አዘጋጅቸላቸው ተመካክረውበት ተስማምተናል” አለን። ይቺን ነገር ከኢዜማ አመራሮች በኋላ ላይ ባደረኩት ውይይት አንድም ሰነድ አዘጋጅቶ አያውቅም የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል። እዚሁ ስላሉ ሊጨምሩበት ይችላሉ።
ጋሽ አንዳርጋቸው በእልህ ብዙ ነገሮችን እያጠፋ እንዳለ የታወቀ ነው። ትልቅ ሰው ስለሆነ ከፍ ዝቅ አድርገን ባንናገረው እንኳን እየሄደበት ያለው መንገድ የጥፋት መንገድ መሆኑን ለታሪክ ማስመዝገብ ያስፈልጋል። እንደ መውጫ፣
መንግስትን መታገል ትክክለኛ እና አግባብ የሆነ ጉዳይ ነው። ከግለሰቦች ጋር ፀብ አለኝ ብሎ ጎረቤት አገር ድረስ ሄዶ ተለማምጦ አብረን እንውጋው ማለት ግን ዝቅ ሲል ነውር ከፍ ሲል ባንዳነት ነው። ለዚያውም ኢትዮጵያን በመጥላት ከተፈጠረው እና ከኖረው ሻዕቢያ ጋር። በመጨረሻም የምለው ነገር ቢኖር አንድ ቀን ወደ ቀልባችሁ ስትመለሱ ማፈሪያ ታሪክ ፅፋችሁ እንደሆነ እወቁት።
የቃላት መፍቻ:- ከባዕድ አገር ጋር አብሮ የራስን አገር መውጋት ባንዳነት ይባላል።

By Gashsw Mersha
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter