በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በየጊዜው በመምህራን ላይ የሚያደርሰው ኢ ሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ የሚወገዝ መኾኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
በክልሉ ተማሪዎች የመማር መብታቸው እንዲከበር ወላጆች እና የትምህርት ማኅበረሰቡ ድርጊቱን ማውገዝ እና መታገል እንደሚገባቸውም ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ.ር) ማኅበሩ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያሉትን አባላቱን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ እየተጋ መኾኑን ገልጸዋል።
የመምህራን መብታቸው እና የሙያ ክብራቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም አንስተዋል።
የመምህራንን ሙያዊ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ኢ ሰብዓዊ ተግባር ሲፈጸም እንደሚስተዋል የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በመምህራን ላይ የሚፈጽማቸውን ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች ለአብነት አንስተዋል፡፡
ማኅበሩ ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚያወግዘው ገልጸዋል። ድርጊቱ ትምህርት ቤቶች ደኅንነታቸው የተረጋገጠ መኾን አለበት የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርህን በእጅጉ የጣሰ ነው ብለዋል።
በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች የተቋረጠውን የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ወደ መደበኛ ሥራ እንዲመለስ ከሚመለከታቸው ጋር በኅብረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
መምህራን የማስተማሪያ ቁሳቁስ ባልተሟላበት ሁኔታ የሚሠሩ መኾናቸውን ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ ይህን ተቋቁመው ሙያዊ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ማድረስ ኀላፊነት የጎደለው ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በቅርብ እየተከታተልን ነው ብለዋል። “በማንኛውም ወቅት መምህራን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቀን እንቃወማለን” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ አጠቃላይ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ጽንፈኛው የመማር ማስተማር ሂደት ማስተጓጎሉ የማኅበረሰቡንም ኾነ የክልሉን የትምህርት ሁኔታ ወደ ኋላ የሚጎትት መኾኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ክፍት መኾን አለባቸው ብለዋል። ኢዜአ እንደዘገበው ሁሉም ማኅበረሰብ በተለይ ወላጆች የቅድሚያ ተጎጂ በመኾናቸው ጽንፈኛውን በቃህ ሊሉት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶች ያሉት በየቀበሌው በመኾኑ ወላጆች እና የትምህርት ማኅበረሰቡ ተማሪዎች የመማር መብታቸው እንዲከበር እና የመማር ማስተማሩ በተሟላ መልኩ እንዲካሄድ መምከር፣ መገሰጽ እና መታገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአሚኮ
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter