የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ/አብን/ 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በድምቀት በማካሄድ፤ ዶ/ር በለጠ ሞላን የፓርቲው ሊቀመንበር፣ አቶ መልካሙ ጸጋዬን ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሰይሟል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ዛሬ መጋቢት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ 3ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ያካሄደ ሲሆን ጉባኤውን በድምቀት በመጸፈም ልዩልዩ ውሳኔወችን አሳልፏል።
ጉባኤው በንግግር የከፈቱት የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር በለጠ ሞላ ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች፣ የተደረጉ ትግሎችን እና የተገኙ ድሎችን አውስተዋል። ሊቀመንበሩ በመክፈቻ ንግግራቸው ድርጅታቸው የአማራን ህዝብ መዋቅራዊ ጥያቄዎችን አንግቦ የፈጠረው ንቅናቄ እንደ ታላቅ ስኬት ሲያነሱ ከውጭና ከውስጥ የገጠሟቸውን ፈተናዎችም ዘርዝረዋል።
ዶ/ር በለጠ በንግግራቸው ከጠቀሷቸው ችግሮች ዋነኛው የሰኔ 15፣ 2011 ዓ.ም. ክስተትን ሲሆን የአማራ ህዝብ የትግል አንድነት ላይ ጥቁር ነጥብ የጣለ ነው ብለውታል።
ከውስጥ በኩልም አመራሩና አባሉ በመደማመጥ እና መከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ባለመዳበሩ ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተፈትኗል ብለዋል። አያይዘውም ለጉባኤውተኛውና ለመላው የአማራ ልሂቅ ካለፉት ችግሮች በመማር በሀሳብ ልዩነት ማመን፣ በልዩነቶች ዙሪያ በሰለጠነ መንገድ መዋያየትና መከራከር፣ ከሁሉም በላይ እርስበርስ መከባበር እና መደማመጥ ይኖርብናል የሚል መልዕክት አፅንኦት ሰጥተው አስተላልፈዋል።
ሌላው የሊቀመንበሩ ንግግር ላይ ከተጠቀሱ አብይት ጉዳዮች የህወሓት ወረራን ለመመከት ድርጅታቸው ያደረገው ተጋድሎ ታሪካዊነት ነው።
ዶ/ር በለጠ ህወሓት በአማራ ህዝብ ላይ ያለው ጥላቻ ከገደብ ያለፈ መሆኑን በህዝብ ትግል ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በፈጸመው ወረራ ወቅት የተፈጸሙ ግፎችን በማስታወስ ወረራውን ለመቀልበስ ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የተደረገውን የተባበረ ትግል ሊለመድ የሚገባው ሲሉ አሞካሽተውታል።
ቀጥለውም ከህወሓት ጋር ሲደረግ የነበረው ጦርነት ፕሪቶሪያ ላይ በተኩስ አቁም ስምምነት ከቆመ በኋላ በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር አንስተው በግጭቱ የክልሉ ህዝብ እየደረሰበት ያለውን መከራ ለማስቆም “መንግሥት ይሁን የታጠቁ ወንድሞቻችን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመስጠት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው መነጋገር ይገባቸዋል” ሲሉ የሰላም ጥሪም አቅርበዋል።
ከሊቀመንበሩ የመክፈቻ ንግግር በኋላ ጉባዔው የድርጅቱን ሪፖርት አዳምጦ ያጸደቀ ሲሆን በመቀጠልም ለቀጣይ ጊዜ የድርጅቱን የቁጥጥር ኮሚሽን እንዲመሩ ዶ/ር አያሌው ታለማን በሰብሳቢነት መሰየም የምክትል ሰብሳቢና የአባላትን ሹመት ሰጥቶ የድርጅቱን 40 ቋሚና 5 ተለዋጭ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አጸድቋል።
ከሰዓት በቀጠለው ጉባኤው ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በከፍተኛ ትኩረት ውይይቶች ተካሂደዋል። አዲስ የተመረጠው ምክርቤት በበኩሉ ዶ/ር በለጠ ሞላን ሊቀመንበር አቶ መልካሙ ፀጋዬን ምክትል አድርጎ የሰየመ ሲሆን አጠቃላይ ዘጠኝ አባላት ያሉት የአስፈጻሚ ኮሚቴን አጽድቋል። በዚሁ መሠረት:-
1) ዶ/ር በለጠ ሞላ ጌታሁን ሊቀመንበር
2) አቶ መልካሙ ፀጋዬ ምክትል ሊቀመንበር
3) ረዳት ፕ/ር ዳምጠው ተሰማ ፖለቲካ ጉዳይ
4) አቶ የሱፍ ኢብራሂም ህግ ጉዳዮች
5) አቶ ጋሻው መርሻ ህዝብ ግንኙነት
6) አቶ ሀሳቡ ተስፋ አደረጃጀት
7) አቶ ጥበበ ሰይፈ ጸ/ቤት
8) አቶ ማሩ ጃኔ ስትራቴጂና ስልጠና
9) አቶ አንዷለም አላምረው ውጭ ግንኙነት
አድርጎ የሰየመ ሲሆን ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ ምሽት አንድ ሰአት ላይ ተጠናቋል።