በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ነው ያለው፣ ከኢትዮጵያዊ ቀጥሎ የመኖች ናቸው፡፡ ግን ሁሌም ውጡ የሚባሉት ኢትዮጵያውያኖች ናቸው፡፡ ምክንያቱን አላውቅም፡፡ በፖሊስ ሁሌም አፈሳ አለ፣ የሚታፈሱት ኢትዮጵውያን ናቸው፡፡ ሌሎች ዜጎች ላይ እንደዛ ሲደረግ አይታይም፡፡ ከዚህ በፊትም እንደዚሁ ሰዎችን የመያዝ፣ የማሰር፣ ገንዘብ ተቀብሎ የመልቀቅ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡
” 30 እና 40 አመታት የኖረ፣ ቤት ንብረት ያፈራ፣ ቤተሰብ የመሰረተ ሰው ብዙ ነው፡፡ ኑሮውን ሁሉ በ3 ቀን ውስጥ ማቋረጥ አይችልም ” – በጅቡቲ የሚኖር ኢትዮጵያዊ
የጅቡቲ መንግስት በሀገሩ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያውያንን በፈቃዳቸው ለቀው እንዲወጡ፣ እንደዛ ካልሆነ ግን የግዳጅ አፈሳ እንደሚጀመር ማስታወቁ ይታወሳል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ውሳኔውን አስመልክቶ በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምን ላይ ይገኛሉ ሲል የተለያዩ ኢትዮጵያዊያንን አያነጋገረ ይገኛል።
አስተያየታቸውን የሰጡንና የጅቡቲ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊ አቶ ኑሩ አስፋው መንግስት የዜጎችን ስቃይ ለመቀነስ በዲፕሎማሲያዊ አካሔድ ጣልቃ መግባት አለበት ባይ ናቸው፡፡
እሳቸው በጅቡቲ በህጋዊ መንገድ እየኖሩ መሆናቸውን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው፣ ነገር ግን ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እጅግ በርካቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 30 እና 40 አመታት የኖረ፣ ትላልቅ የንግድ ድርጅቶችን የከፈቱ፣ ሀብትና ንብረት ያፈሩ፣ አግብተው የወለዱ ኢትዮጵያውያን አሉ ብለዋል፡፡
” በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ነው ያለው፣ በሦስት ቀናት ውስጥ የሚይዘው የሚጨብጠው ነገር የለም ” ብለዋል አቶ ኑሩ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ ከጅቡቲ መንግስት ጋራ ተነጋግሮ ዜጎቹን ከጭንቀት እንዲታደግም ተማፅነዋል፡፡
አቶ ኑሩ በዝርዝር ምን አሉ ?
” በተገለፀው ማስታወቂያ መሰረት መመዝገብ የጀመሩ አሉ፣ በመኪና መውጣት የጀመሩም አሉ፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም፡፡ አሁን 3 ቀን ብቻ ነው የቀረው፡፡ በአውሮፕላንና በባቡር መውጣት አትችልም፣ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ካልያዝክ፡፡ ከጅቡቲ ውጡ የሚለው ጉዳይ የተሳሳተ ይመስለኛል፡፡
በጣም ብዙ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ነው ያለው፣ ከኢትዮጵያዊ ቀጥሎ የመኖች ናቸው፡፡ ግን ሁሌም ውጡ የሚባሉት ኢትዮጵያውያኖች ናቸው፡፡ ምክንያቱን አላውቅም፡፡ በፖሊስ ሁሌም አፈሳ አለ፣ የሚታፈሱት ኢትዮጵውያን ናቸው፡፡ ሌሎች ዜጎች ላይ እንደዛ ሲደረግ አይታይም፡፡ ከዚህ በፊትም እንደዚሁ ሰዎችን የመያዝ፣ የማሰር፣ ገንዘብ ተቀብሎ የመልቀቅ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡
አንዳንዴ ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ (ኢትዮጵያዊው እርስ በርሱ ይጋጫል አንዳንዴ)፣ ወንጀል በሚፈፀምበት ጊዜ እንደዚህ ውጡ ምናምን ስለሚባል፣ ሰው ትኩረት አልሰጠውም ነበር፡፡ እንደዚህ በይፋ ለቃችሁ ውጡ ተብለን አናውቅም፡፡ በዚህ ምክንያት ችላ ብሎት ተዘናግቷል፡፡ የአሁኑ ለየት የሚያደርገው በመንግስት ደረጃ በይፋ መገለፁ ነው፡፡
ሰው በጣም ተደናግጧል፡፡ ቀነገደቡ ይራዘማል የሚል ተስፋ ነበረው፡፡ አሁን 3 ቀን ቀርቶታል፡፡ መፍትሔ ከመዘየድ ይልቅ ዝም ብሎ መጨነቅ ላይ ነው ያለው ስደተኛው፡፡ የንግድ ተቋማት ያሉዋቸው ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ በ5 ቀን ምን ማድረግ ይችላሉ ? ” ብለዋል።
ንብረት ያፈሩ ሰዎች እንዴት ህጋዊ ሰነድ የላቸውም ?
አቶ ኑሩ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ” ሰው ጅቡቲ ሀገሬ ናት ብሎ ነው እስካሁን የሚያስበው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ይመጣል ብሎ አያስብም፡፡ ኢትዮጵያና ጅቡቲ እንደ አንድ ሀገር ነው የሚታሰቡት፡፡
ራሳቸው ጅቡቲዎችም እንደዛ ነው የሚሉት፣ አሁንም በመንግስታቸው ውሳኔ ደስተኞች አይደሉም፡፡ በዚህ ተዘናግተው ነው ለአመታት ያለ ህጋዊ ሰነድ የሚኖሩት፡፡ ጅቡቲንና ኢትዮጵያን ለያይቶ ማየት አይቻልም፡፡ ” ብለዋል
አክለውም ” ለሚባረሩት ዜጎች መንግስት ሊደርስላቸው ይገባል ” ሲሉ ተማጽነዋል።
” እዚህ ያለው ህዝብ ንብረቱን ሸጦ፣ በራሱ ተመዝግቦ፣ ተረጋግቶ የሚወጣበት እድል ሊመቻችትለት ይገባል፡፡ በ3 ቀን ውስጥ ለቃችሁ ውጡ ማለት አግባብ አይደለም፡፡
በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን ስቃይ የሚቀንስበትን መንገድ ማመቻቸት አለባቸው፡፡ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱም በኋላ የሚቋቋሙበት ዕድል መመቻቸት አለበት፡፡
አፈሳ ከተጀመረ አደገኛ ነገር ነው፡፡ ተይዘህ ወደ ማቆያ ትገባለህ፣ ከዛም በግድ ተጭነህ ትባረራለህ፡፡ ንብረት አትይዝም፣ ገንዘብህን አትሰበስብም፣ ቤተሰቦችህን የመሰናበት ዕድል አይኖርህም፡፡ ካለህበት ሁሉ ተለቅመህ ነው የምትወሰደው፡፡
የቤት ሰራተኞች አሉ፣ ደመወዛቸውን እንኳን በወቅቱ አይሰጡዋቸውም፣ ደመወዝ ሳይዙ ሊባረሩ ነው ማለት ነው፡፡ መንግስት እንዲደርስላቸው ነው የምማፀነው፡፡ ” ሲሉ ተናግረዋል።
ቲክቫህ ኢትጵያ
