የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ አቋም አለመውሰድ እጅግ ጥብቅ ጥንቃቄ መሆኑን ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆነ የህግ ባለሞያ አቶ ሙሉአለም ጌታቸውን አስታወቁ። አሜሪካዊ ሚስት ያገባ ኮሎምቢያዊ ዜጋ በቅርቡ ሃማስን በመደገፉ ምክንያት ወደ ዲቴንሽን ማዕከል እንዲገባ ምሳሌ አቅርበው ነው ባለሙያው ምክር የሰጡት።
የጥገኝንነት ጥያቄ ያቀረቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ይታወቃሉ ነገር ግን እነዚህ ተመላሽ ናቸው ለማለት አያስችልም ” ያሉት የህግ ባለሞያ ያም ቢሆን አሁን ላይ እየወጡ ባሉ አዳዲስ አሰራሮችና መመሪያዎች ሳቢያ ጥንቃቄ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ መውሰድ እጅግ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ በርካታ ውሳኔዎችን እያስተላለፈ የሚገኝ ሲሆን አብዛኞቹ ውሳኔዎች በተለይም በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ የተለያዩ ሃገራት ዜጎችን ስጋት ላይ የጣለ ጉዳይ እንደሆነ በተከታታይ የሚወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ።
ህጎቹን ተከትሎ በተወሰዱ እርምጃዎችም በህገ ወጥ መንገድ አሜሪካ የገቡ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ወደ መጡበት የመመለሱ ሂደት በርካቶች ወደ ዲፖርቴሽን ወይም ማጎሪያ ማዕከል እንዲጋዙ አድርጓል።

ይህንኑ የዲፖርቴሽን ትግበራ ተከትሎ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ መግባት፣ ቪዛ ለማግኘት መዋሸት፣ ያለ ህጋዊ የስራ ፍቃድ ስራ መስራት ፣ የቪዛ ጊዜ ካበቃ በኋላ በአሜሪካ መቆየት ከባድ ቅጣት ያስከትላል እንደሚያስከትል መግለጹ የሚታወስ ነው።
አምባሳደር ኤሪቪን ማሲንጋ ቅጣቶቹ እስርን፣ ወደ ሃገር መመለስን እና ዳግም ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከልከልን እንደሚያካትት የተናገሩ ሲሆን ” በህገ ወጥ መልኩ በአሜሪካ የሚኖር ቤተሰብ ወይም ጓደኛ ካላችሁ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የምትነግሩበት ጊዜ አሁን ነው ” ብለውም ነበር።
ከትራምፕ አስተዳደር በኋላ የወጡ አዳዲስ ህጎች ሳቢያ በርካታ የህጋዊነት ጥያቄዎች እና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ሂደት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ስጋት ውስጥ ከወደቁት የተለያዩ ዜጎች መካከል ይካተታሉ።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ያደረጉት የህግ ባለሞያውን አቶ ሙሉአለም ጌታቸው ከስራቸው ጋር በተያያዘ ሰለገጠማቸውና ወቅቱን ተመልክቶ መደረግ ያለበትን ሙያዊ አስተያየታቸውን ከዚህ እንደሚከተለው አስፍሯል።
አቶ ሙሉአለም ጌታቸው ” የትራምፕ አስተዳደር የሚያወጣቸው የተለያዩ Executive ኦርደሮች ወይም ህጎች አሉ። እነዚህ ህጎች የኢሚግሬሽን አማራጩን የሚያጠቡ ናቸው። ማለትም ከዚህ ቀደም ብዙ እድሎች ካሉ እነዛ ኦፖርቹኒቲዎች ጠበዋል” ይላሉ።
“ከባድ የሆነ ማጣራት የሚደረግበት ወቅት ነው ። ፋይሎች ይመረመራሉ። ስራችን ላይ በጣም ከፍተኛ የሆነ ጫናን አሳድረዋል። ደንበኞቻችንም ብዙዎቹ ተጨንቀዋል” ሲሉም ስላለው ሁኔታ መረጃ ሰጥተዋል። አክለውም ምን ሊፈጠር እንደሚችል እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሚመለከት ከሌሎች ሃገሮች አንጻር ትልቅ የሚባል የጥገኝነት ጥያቄ እንደሌለ፣ በጣም ትልልቅ የጥገኝነት ጠያቂ ሃገሮች ኢኳዶር ፣ጓቲማላ፣ ኤልሳልቫዶር እና ሜክሲኮ የህግ ባለሙያው አመልክተዋል። ከዓለም ደግሞ ከቻይናና ህንድ የሚመጡ ስደተኞች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ፣ ከአፍሪካም የምዕራብ አፍሪካውያን ቁጥር ከምሥራቅ አፍሪካውያን ቁጥር እንደሚበልጥ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ቁጥር ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የማይባል ቢሆንም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በኢትዮጵያ ካሉ ግጭቶች ጋር ተያይዞ ቁጥሩ መጨመሩን ገልጸዋል። ትልልቅ አቅም ያላቸው ሰዎች እንኳን ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ችግር ውስጥ እየገቡ በመሆኑ ጥገኝነት የመጠየቅ ሂደት ውስጥ መገባታቸውን ጠበቃው አስታውቀዋል።
“በማንኛውም ሰዓት ብዙ ነገሮች ሊቀየሩ ይችላሉ። ከአንድ ወይም ሁለት ዓመት በኋላ ምናልባትም ለጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ አሁን ከምንጠብቀው በላይ እጅግ ከባድ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አሁን ያለው ሲስተምም ሊቆም ይችላል” ሲሉ ግምታቸውን ያኖሩት የህግ ባለሙያ፣ “እቅድ እና ፖሊሲያቸው ለህዝብ ይፋ ሆኖ ከዚህ በኋላ እንዲህ ይሆናል የሚባልበት ሁኔታ ላይ አይደለም ” ሲሉ መረዳታቸውን ከገለጹ በሁዋላ ይበጃል ያሉትን ምክር ለግሰዋል።
የግሪን ካርድ (ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ) ጥያቄ አቅርበው በመጠባበቅ ላይ ያሉ አካላት ሁልጊዜ ህጋዊ በሆነ መንገድ አሜሪካን ውስጥ መቆየት፣ ከወንጀል መራቅ እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል።
ከዚህ ቀደም የግሪን ካርድ ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎች ጠጥተው የመንዳት ጥፋት ቢገኝባቸው ወደ ዲፖርቴሽን አይወሰዱም ነበር። አሁን ግን በቀጥታ ወደ ዲፖርቴሽን ሊወስዱዋቸው እንደሚችሉ የባለሙያው ገለጻ ያስረዳል። እሳቸው ብቻብቻ ሳይሆን በርካታ የአሜሪካ ነዋሪዎች ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ለባለደረቦቻቸው ሲያስታውቁ ተሰምቷል።
ጠጥቶ ማሽከርከር በብዛት የሚታየው ተማሪዎች ላይ መሆኑን፣ በትምህርት ቪዛ የመጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የቀን ፓርቲዎች ውስጥ ተሳትፈው ፓርቲው ሲያልቅ መኪና እንዳያሽከረክሩ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ መክረዋል።
“ሌላው የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ አቋም አለመውሰድ ወሳኝ ነው” ሲሉ ያስታወቁት የህግ ባለሞያውን አቶ ሙሉአለም ጌታቸው “አሜሪካዊ ሚስት ያገባ ኮሎምቢያዊ ዜጋ በቅርቡ ሃማስን በመደገፉ ምክንያት ወደ ዲቴንሽን ማዕከል እንዲገባ ተደርጓል” ሲሉ ለኝዛቤ እንዲረዳ በቅርብ የሚያውቁትን ጉዳይ በማንሳት አስጠንቅቀዋል።
“የጥገኝንነት ጥያቄ ያቀረቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ይታወቃሉ።ነገር ግን እነዚህ ተመላሽ ናቸው ለማለት አያስችልም። አብዛኞቹም ፕሮሰሳቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው። ያላቸውን እድል በሙሉ አሟጠው እስከሚጠቀሙ ድረስ ይህን ያህሉ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ ብሎ መናገር አይቻልም ” ሲሉም አቶ ሙሉአለም ጌታቸው ተናግረዋል።