የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ”የሰባ ገብዣ” በሚል ርዕስ ስቅለት ዕለት ያቀረቡትን መልዕክት በተመለከተ እጅግ በርካታ ውግዘትና ፍረጃ ሲሰጥ እየተሰማ ነው። የሊቀ ጳጳሱን ስብዕና እና ማንነት ከማዋረድ ጀምሮ የሚሰጡት ስድብ አዘል “አስተያየቶች” ኢ-መንፈሳዊ፣ ጽንፈኛና አምባገነናዊ ናቸው።
ገና ከጅምሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪና ብዙ ተከታይ አለን የሚሉ በሚሰጡ አስተያየት ሊቀ ጳጳሱን ከመዝለፍና ከማዋረድ አልፈው ግለሰባዊ ማንነታቸውን በማጉላት ሲሳደቡ ተሰምተዋል። እነዚህ “መምህራን” ብለው ራሳቸውን የሰየሙ ወይም ጥቂት ጊዜያት በቤተ ክርስቲያኗ የትምህርት ደጃፍ በማለፋቸው ብቻ “መምህር” ተብለው የሚጠሩ፤ በአቡኑ ላይ ለርካሽ የፖለቲካ መጠቀሚያ የሚውልና ከወንጌል አስተምህሮ የለቀቀ እጅግ ጸያፍ ንግግሮች በማሰማት ከሊቃውንቱ ጉባዔና ሲኖዶሱ ውሳኔ በፊት የአደባባይ ፍረጃ እየበየኑባቸው ነው፤ የሲኖዶሱን እጅ እየጠመዘዙም ነው።

ድርጊቱ በዕቅድና በዘመቻ መልክ የሚካሄድ እንደሆነ አንዱ ማሳያ፤ ቪዲዮውን ያወጣው ፍኖተ ጽድቅ የተባለው ሚዲያ በዩትዩብ ቻናሉ ሲሆን ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ቀን ድረስ ቪዲዮው ከወጣ አራት ቀናት አልፈዋል። በእነዚህ አራት ቀናት ቪዲዮውን የተመለከተው ሰው ቁጥር 22ሺህ ብቻ ሲሆን አስተያየት ሰጪውና ነቃፊው ግን “22 ሚሊዮን” መድረሱ ዘመቻው ከዕውቀት የጸዳና ሌላ ስሁት ዓላማ ያለው መሆኑ አመላካች ነው።
አቡነ ገብርኤል ያደረጉት ፖለቲካዊ ወይም ተራ ንግግር ሳይሆን ሃይማኖታዊ መልዕክት ያለው ነው፤ የመልዕክታቸው ይዘት ደግሞ ነገረ መለኮታዊ ወይም ቲዎሎጂካል ነው። እርሳቸው የተናገሩትን ከቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ አንጻር ስህተት ነው ወይም አይደለም የማለት ሥልጣን ያለው ቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓቱን ጠብቃ ያዋቀረችው የሊቃውንት ጉባዔ ነው እንጂ የቲክቶክ ነጋድራሶች፣ የቴሌግራም ፊት አውራሪዎችና የዩትዩብ ተጧሪዎች መሆን የለባቸውም።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት በዚህ ዓመት የካቲት ወር ባወጣው መረጃ ይህንን ብሎ ነበር፤ “የሊቃውንት ጉባኤ በቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ኀላፊነት መሠረት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮ፣ ታሪክና ትውፊት፣ ልሳነ መጻሕፍትና የዕውቀት ሀብታት፣ ጥበባተ አበውና ባህለ ሃይማኖትን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ማስፋፋትና በአግባቡ እንዲተረጐሙ ማድረግ፣ ዐቂበ እምነትን ማጠናከር፣ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ልዕልና፣ ህልውና፣ የትምህርቷን ጥራትና ርትዐት መጠበቅ ዋንኛ የሥራ ድርሻው ነው።
“በቀድሞ ዘመን መናፍቅና ከሓዲ ሲነሣ፣ ሃይማኖትና ሥርዐት ሲጣስ፣ ዐላውያን የሐሰት ትምህርትን በዐውደ ጉባኤ ሲያሠራጩ፡ ሊቃውንት ከየአሉበት ተሰብስበው ዘርዐ ኑፋቄን አርመው፣ ኀይለ ክሕደትን አድክመው ርትዕት ሃይማኖትን አቆይተዋል። በእኛም ዘመን በርካታ ውይይትና ምክክር የሚያስፈልጋቸው ዐበይት ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ጥያቄዎች በመኖራቸው፤ ያለፈውን ለማጽናት፣ የሚመጣውን ለማቅናት የሊቃውንት መሰባሰብ እጅግ ተገቢ ሆኖ ይገኛል።”
ቤተ ክርስቲያኗ ይህንን የመሰለ በርካታ ዘመናትን የተሻገረ፣ እጅግ የዳበረ አሠራር እያላት ክብሯ በማኅበራዊ ሚዲያ ለሚገኝ ፍርፋሪና “ዕውቅና (ላይክ)” ቀን ተሌት “በሚለፉ” መጻጉ የዕውቀት ድኩማን መዳፍ ሥር መውደቁ አብሮ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
አቡነ ገብርኤል ያቀረቡት መልዕክትን በተመለከተ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ለረቡዕ” ቀጥሮት የነበረውን “የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በምልዓት የሚገኙበትን” ውይይት ወደ አርብ አስተላልፎታል።
በተለመደው አሠራርና በበርካታዎች ዘንድ እንደሚጠበቀው በዚህ ዕለት ሲኖዶሱ ይህንን ስነ መለኮታዊ ጉዳይ በሊቃውንት ጉባዔ እንዲታይ ያደርጋል። ቀጥሎም የሊቃውንቱ ጉባዔ የሚሰጠውን አስተያየት ተመርኩዞም በአቡነ ገብርኤል ላይ ሲኖዶሱ ውሳኔ ያስተላልፋል። እስከዚያ ግን ዝምታ ወርቅ ነው።
“ወኵሎ አመክሩ፣ ወዘሠናይ አጽንዑ።” “ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ” የሚለውን የቅዱሱን መጽሐፍ መመሪያ መከተል እየተቻለ (1ኛ ተሰሎንቄ 5:21) አስተዳደራዊውንም ሆነ አስተምህሮ ላይ ያነጣጠረውን ጉዳይ ሁሉ በግድ ለጥጦ ፖለቲካዊ ማድረግ፤ በተለይ ደግሞ ከርካሽ የዘር ፖለቲካ ጋር በማያያዝ በግድ እሳት ለማቀጣጠል መሞከር ወይ በሚያምኑት አስተምህሮ ላይ የዕውቀት እጥረት እንዳለ የሚያሳይ ነው ወይም አርነት የሚያወጣውን እውነት ማዳፈን ነው። ሁለቱም ያስኮንናል እንጂ አያጸድቅም።
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ™” አቋም ነው።
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter