ሩዋንዳ በአፕሪል ወር የዕልቂት ድግስ የተደገሰው በአንድ ቀን አልነበረም። ቀኑ ሲደርስ ዕድሜ ለአርቲኤልኤም “ጋዜጠኖች” ሊያስበሏቸው ያሰቡዋቸውን ስም ሰጡና በጥላቻ ቀብተው አሳረዷቸው። የሸሹ፣ የተፈናቀሉና በተዓምር የተረፉ ዛሬ ድረስ እየነዘራቸው ምስክርነት ይሰጣሉ።
በኢትዮጵያ በተመሳሳይ አንዱን በዳይ፣ ሌላውን ተበዳይና ግፍ ተሸካሚ አድርጎ የሳለው የሰሞኑ የኢቢኤስ ድራማ በርካቶችን ያስደነገጠው “ዓላማው ቢሳካ ኖሮ” ከሚል ድንጋጤ ነው። በተለይም ለኢትዮጵያ የማይተኛላት ሻዕቢያ የሴራው መጥመቂይና፣ የጠመቀውን ሴራ የሚረጭበት ሚዲያ ውስጥ እጁ መታየቱ ድንጋጤውን አጉኖታል። ይህንኑ ተከትሎ ሕዝብን ሳይሆን ሻዕብያን በመጠቀስ ወደሁዋላ በመመለስ ብዙ እየተባለ ነው።
ኢቢኤስን የሩዋንዳውን ፍጅት እንዲቀጣጠል ካደረገው ሬዲዮ RTLM (Radio Télévision Libre des Mille Collines) ተለይቶ ሊታይ እንደማይገባ ያመለከቱት ወገኖች፣ በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይ) በዋንኛነት ከሚጠቀሱት መካከል የሚዲያውን ኃይል በመጠቀም RTLM (Radio Télévision Libre des Mille Collines) በተሰኘው የሬዲዮ ማሰራጫ አማካኝነት የተነዛው የዘር ጥላቻ ተጠቃሽ እንደሆነ ማስረጃ አጣቅሰው ይናገራሉ።” ኢቢኤስም ኦሮሞና አማራ እንዲጫረስ ነው የሰራው” ሲሉ መመሳሰላቸውን በይዘት ያስረዳሉ።
ብርቱካን ተመስገንን በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን ከተላለፈው ሐሰተኛ ዘጋቢ ፊልም ጋር በተያያዘ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ለፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ መፈቀዱን ተከትሎና የኢቢኤስ መቀጣትን ተከትሎ ነው ተቃውሞው የተሰማው።
ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ የሰጠባቸው ተጠርጣሪዎች፤ ብርቱካን ተመስገን፣ ነብዩ ጥዑመልሳን የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ፣ ታሪኩ ኃይሌ የአዲስ ምራፍ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ፣ ደረጀ ሉቃሌ፣ ኅሊና ታረቀኝ፣ ንጥር ደረጀ እና መታገስ ዓለሜ ናቸው፡፡
በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል ስልጣንን በኃይል ለመያዝ ፣ የጦር መሣርያ በመታጠቅ፣ በሕገ-ወጥ መንገድ በመደራጀት፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ጽንፈኛና ፀረ ሰላም ቡድን አመራሮች ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ መንግሥት የሕዝብ ተቀባይነት እንዲያጣና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ እንዲደረግበት በማሰብ፣ ተዋድደውና ተከባብረው በሚኖሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል ቅራኔ በመፍጠርና ወደ ግጭት እንዲገቡ ለማድረግ፣ በውጭ ሀገር ከሚገኝ የፀረ ሰላም የቡድኑ አመራሮች ጋር በተለያዩ መገናኛ መንገዶች በመገናኘት እና ተልዕኮ በመቀበል የሥራ ባህሪያቸውን እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም የሚሉ የምርመራ የጥርጣሬ መነሻውን ለችሎቱ አቅርቧል።
ፖሊስም የምርመራ ሥራየን በሰውና በሠነድ ማስረጃ በስፋት ማጣራት እንድችል 14 ተጨማሪ ቀናት ይፈቀድልኝ ሲል ባሳለፍነው ዓርብ መጠየቁን ተከትሎ፤ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት የፖሊስን ጥያቄ በመቀበል 14 የምርመራ ቀን ፈቅዷል።
በተጨማሪም እስከ አሁን በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያሰባሰበውን መረጃና ቀሪ የምርመራ ሥራ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አቅርቧል።
በሌላ ዜና ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በኢ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ‘አዲስ ምዕራፍ’ በተሰኘ ፕሮግራም ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ፕሮግራሙ እሑድ መጋቢት 14 ቀን 2017 ዓ.ም ያሰራጨውን ፕሮግራም ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እና ከዘርፉ ሕጎች አንጻር መገምገሙን ገልጿል።
በዚሁ መሰረት በጣቢያው የቀረበው ፕሮግራም በሐሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ፣ ሕዝብን የሚያሳስትና ጥርጣሬን የሚፈጥር፣ የመገናኛ ብዘኃን አዋጅ 1238/2013፣ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ 1185/2012 እንዲሁም የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ-ምግባርን፣ መደበኛ የጋዜጠኝነት አሰራርን የሚጥስ የፓራጆርናሊዝም አሰራርን የተከተለ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል፡፡
ጣቢያውም በፕሮግራሙ ዙሪያ ተጠይቆ ለባለሥልጣኑ በሰጠው ምላሽ ያሰራጨው ፕሮግራም ሐሰተኛ መሆኑንና ስህተት መፈጸሙን ማረጋገጡን ባለሥልጣኑ ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
ባለሥልጣኑ ጉዳዩን መርምሮ በጣቢያው የሚሰራጨው “አዲስ ምዕራፍ” የተሰኘ ፕሮግራም በኤዲቶሪያል አሰራሩ ላይ አስፈላጊውን እርምት ወስዶ ለባለሥልጣኑ እስኪያሳውቅና ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ፕሮግራሙ ከስርጭት ታግዶ እንዲቆይ መወሰኑን እና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ መሆኑን ገልጿል።
አዲስ ምዕራፍ የሚተሰኘው ፕሮግራም መዘጋቱና የትጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ከታሰበው አደገኛ ቀውስ አንጻር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ጠቅሰው ዜናውን የሰሙ ተችተዋል። እንዳለ ኢቢኤስ መዘጋትና ከኢትዮጵያ መባረር እንዳለበትም ያመለከቱ አሉ፤
በሩዋናዳ አንድ የሬዲዮ ፕሮግራም ባሰራጨው ጥሪ ከፍተኛ የዘር እልቂት መፈጸሙን የሚያስታውሱ ኢቢኤስ ይህን ወነጀል በፈጸመ ቅጽበት እርምጃው ሊወሰድበት ይገባ እንደነበር አመልክተዋል።
ኢቢኤስን የሩዋንዳውን ፍጅት እንዲቀጣጠል ካደረገው ሬዲዮ RTLM (Radio Télévision Libre des Mille Collines) ተለይቶ ሊታይ እንደማይገባ ያመለከቱት ወገኖች፣ በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይ) በዋንኛነት ከሚጠቀሱት መካከል የሚዲያውን ኃይል በመጠቀም RTLM (Radio Télévision Libre des Mille Collines) በተሰኘው የሬዲዮ ማሰራጫ አማካኝነት የተነዛው የዘር ጥላቻ ተጠቃሽ እንደሆነ ማስረጃ አጣቅሰው ይናገራሉ።” ኢቢኤስም ኦሮሞና አማራ እንዲጫረስ ነው የሰራው” ሲሉ መመሳሰላቸውን በይዘት ያስረዳሉ።
ይህንን ተግባር ሲፈጽሙና ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ እንዲነሱ ያደረገውና ቱትሲዎችን “በረሮ” (“cockroaches”) እያለ በመጥራት “እንዲገደሉ” በሬዲዮው አማካኝነት “ትዕዛዝ” ሲሰጥ የነበረው ፌሊሲዬን ካቡጋ (Félicien Kabuga) ዋነኛ ተጠቃሽ እንደሆነ ይታውሳል።
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ዙሪያ ባደረገው ጥናት ካቡጋ እና የሬዲዮ ጣቢያው ልፈፋ ለ51ሺህ ሰዎች መገደል ቀጥተኛ ተጠያቂ አድርጓታል። ይህም በአጠቃላይ ከተጨፈጨፉት ሰዎች ውስጥ አስር በመቶ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል።
ኢቢኤስ ማለት ካቡጋ ነው! የተላለፈው ፕሮግራምም ልክ እንደ RTLM ሬዲዮ ዓይነት ነው። ከሸፈ እንጂ አሳቡ ይህ ለመሆኑ በመርዝ የተለወሰው የትርምስ ዶኩመንታሪ ይዘትና የሴራው ድር ያስረዳል።
“በርቱካን ባትያዝ ኖሮስ” የሚሉ ወገኖች ብርቱካን ባትያዝና ጉዳዩ በፍጥነት ሃሰት መሆኑ ባይገለጽ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ ሲሰላ ኢቢኤስን በአንድ ደብዳቤ ማስተንቀቅ ፍጹም የስላቅ ያህል ቆጥረውታል። ነገ በተመሳሳይ ሌላ ጉዳይን ላለመተላለፉ ዋስትና እንደሌለ ጠቅሰው መንግስትን ያስተንቀቁ ጥቂት አይደሉም።
በዚህ ዙሪያ የህዝብ አስተያየት አሰባስበን እንመለሳለን።