” የዶላር ባንክ ሒሳብ ለመክፈት የዶላር ምንጭህ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚሁ በጥቁር ገበያ እየለቃቀምክ ማስገባት አትችልም፡፡ ይህ ህገወጥ ነው ” ይላሉ ባለሙያው።
- ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ምንዛሬ መገበያያት ይቻላል ወይ ?
- አገልግሎት ሰጪዎች በዶላር ማስከፈል ይችላሉ ?
- ከአንድ የባንክ ሒሳብ ወደሌላ የባንክ ሒሳብ ዶላር ማስተላለፍ ይቻላል ?
- ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ግብይት መቼ ሊጀመር ይችላል ? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ማብራሪያ ማቅረቡ በመጥቀስ ቲክቫህ ከላይ ባለምያው ያሉትን የአሰራ መርሃ ያብራራል።
ቀደም ሲል አስተያየት የሰጡትን ባለሙያ፣ ከሌላ የባንክ ባለሙያ ጋር በማቀናጀት የተለያዩ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን በማንሳት ቲክቫህ ያዘጋጀውን ማብራሪያ በመረጃነቱ ይጠቅማል በሚል አትመነዋል።
ለውጭ ጉዞ ዶላር/የውጭ ምንዛሪ እንዴት ነው የሚሰጠው ?
” ለጉዞ ከሆነ ከራስህ ዶላር አካውንት ወይም ዶላር አካውንትም ባይኖርህ ከባንኮች ወይም ከተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሪ ሱቆች በግዢ እስከ 10 ሺህ ዶላር ይዘህ መውጣት ትችላለህ፡፡ ለዚህ ግን ማሳየት ያሉብህ ማስረጃዎች ይኖራሉ፣ የጉዞ ሰነዶች ማለት ነው፣ ለምሳሌ ቪዛ እና የአየር ቲኬት የመሳሰሉት፡፡ “
የባንኮች ቪዛ ካርዶች እንዴት ነው የምንጠቀምባቸው ?
” የንግድ ባንኮች ቪዛ/ማስተር ካርዶች ሁለት አላማ አላቸው፡፡ አንደኛው፣ ዳያስፖራዎች ከካርዳቸው በቀጥታ ወደ ሀገር ቤት በቀላሉ ዶላር እንዲልኩ ያስችላቸዋል፡፡ አሜሪካ ያለው ዳያስፖራ የአሜሪካ ባንክ ካርድ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተቀባይ ደግሞ የንግድ ባንክ ማስተር ካርድ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ተቀባይ በካርዱ በቀላሉ ዶላር ሊያስተላልፍለት ይችላል፡፡ ተቀባዩ ደግሞ ከውጭ ዶላር ሊላክልኝ ስለሆነ የዶላር አካውንት ክፈቱልኝ ይላል፡፡ ከዛም ላኪው ከካርዱ በቀጥታ ወደ ተቀባዩ አካውንት ዶላር ያስተላልፍለታል፡፡
ሁለተኛው ጠቀሜታ፣ ከዚህ ወደ ውጭ ስትወጣ እስከ 10 ሺህ ዶላር መውሰድ ትችላለህ፡፡ ይህን በካሽ ከሚሰጡህ ይልቅ በካርድ ቢሰጡህ ይሻላል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ከባንክ ወደ ውጭ ይዘህ ለመውጣት የተፈቀደልህ ዶላር ማስተር ካርዱ ላይ ይጫናል ማለት ነው፡፡ ከዛም ካርዱን ይዘህ በመውጣት እንደ ኤቲኤም ትጠቀምበታለህ፡፡ “
ማስተር ካርዱን በውጭ ሀገራት ብቻ ነው የምንጠቀምበት ?
ስለዚህ ጉዳይ ያብራሩልን ማንነቴ አይጠቀስ ያሉን ሁለተኛ የባንክ ባለሙያ ፥ ቪዛ ካርዱ የሚጠቅመው ዶላር ይዞ ለመውጣት እና እዛው እንደ ኤቲኤም ለመጠቀም ነው ብለዋል፡፡ ካርዱ ላይ የሚጫነው ዶላር/የውጭ ምንዛሪ በባንክ የተፈቀደ ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ካርዱን ስላወጣህና አካውንትህ ውስጥ ዶላር ስላለህ ብቻ ካርዱ ላይ አይጫንም፡፡ አሳማኝ በሆነ ምክንያት የውጭ ጉዞ መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ይዘህ እንድትወጣ የተፈቀደልህን ዶላር ካርዱ ላይ ይጭኑልሃል፡፡
ከውጭ ሀገር ከተመልስክ በኋላ፣ ካርድህ ውስጥ የተጫነውን ዶላር ካልጨረስከው ያልተጠቀምክበት ዶላር ካርዱ ውስጥ ካለ እዚህ ሀገር ካለ ኤቲኤም ማሽን ልታወጣው ትችላለህ፡፡ ግን ኤቲኤም ማሽኑ ዘርዝሮ ነው በብር የሚሰጥህ በዶላር አይሰጥህም፡፡
ለሀገር ውስጥ ግብይት ልትጠቀምበት አትችልም፡፡ ምክንያትም ቪዛ ካርድ የሚጠይቅ ግብይት የለም እዚህ ሀገር፡፡ ነገር ግን ካርድህ ውስጥ ያለውን ዶላር (ያልተጠቀምክበትን) ለውጭ ግብይት ልትጠቀምበት ትችላለህ፡፡ የካርድ ቁጥርህን በመናገር የፈለከውን ክፍያ ትፈፅምበታለህ፡፡ ለምሳሌ የቪዛ ክፍያ የሚጠይቁ ኤምባሲዎች አሉ ‘ በዶላር ክፈል ‘ ይሉሀል፡፡ ቪዛ ካርድ ካለህ (ቀድሞ ዶላር የተጫነበት) የካርድ ቁጥሩን ትነግራቸውና ከዛ መቀነስ ይችላሉ፡፡ “
የባንኮች ቪዛ ካርዶች በሀገር ውስጥ የምንጠቀምበት ዕድል አለ ?
” ቪዛ ካርዶቹ ብርም ሊጫንባቸው ይችላል፡፡ ንግድ ባንኮች ካርዶቹን ከዶላር በተጨማሪ ብርም ከጫኑባቸው እዚህ እንደ ኤቲኤም ልትጠቀምባቸው ትችላለህ፡፡ እንደዛ የሚያደርጉ ባንኮች አሉ፡፡
ለምሳሌ ፦ አንዳንድ ባንኮች በቪዛ ካርዳችሁ መጥታችሁ በፖስ ማሽን ተጠቀሙ የሚል ማስታወቂያ ሲያስነግሩ እንሰማለን፡፡ ይህ ማለት ቪዛ ካርዳቸው ከዶላር በተጨማሪ ብርም ተጭኖበታል ማለት ነው፡፡ ሁለቱንም አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል ቪዛ ካርዱ፡፡
ፖስ ማሽኑ እና ኤቲኤም ማሽኑ ቪዛ ካርዶችን ያነብባል፡፡ ይህ ግን እንደ ባንኩ ምርጫ ይወሰናል፡፡ ሁለቱንም እንዲያገለግል (ዱዋል ማለት ነው ብርም ዶላርም እንዲጫንበት) ሊያደርግ ይችላል ወይም ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ብቻ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል።
ቪዛ ካርዱ ዱዋል (ለሁለቱም የሚያገለግል) ካልሆነ ግን አንዴ ከተጠቀምክበት በኋላ ከጥቅም ውጪ ነው የሚሆነው፡፡ ሁሌም ወደ ውጭ አትመላለስም፡፡ “
የዶላር አካውንት/የውጭ ምንዛሪ የባንክ ሒሳብ ለመክፈት ቅድመ ሁኔታ አለ ?
” የዶላር ባንክ ሒሳብ ለመክፈት፣ የዶላር ምንጭህ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚሁ በጥቁር ገበያ እየለቃቀምክ ማስገባት አትችልም፡፡ ይህ ህገወጥ ነው፡፡ ከውጭ የሚገባልህ የደመወዝ ወይም የስጦታ አለያም የክፍያ ዶላር እንዳለህ ማስረዳትና ለዚያ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅብሀል፡፡
በካሽ ይዘህ ስትሔድ ደግሞ ከውጭ ያስገባኸው ዶላር ስለመሆኑ፣ በጉምሩክ በህጋዊነት የገባ መሆኑን የሚያሳይ ሰነድ ማቅረብ አለብህ፡፡ ምክንያቱም ከውጭ ስትገባ አስመዝግበህ ነው እስከ 10 ሺህ ዶላር ድረስ ይዘህ የምትገባው፡፡ ስለሆነም የዶላር የባንክ ሒሳብ/ዶላር አካውንት ለመክፈት ቅድመ ሁኔታው፣ የዶላር ምንጭህን ማሳወቅ ነው፡፡ “