የአፍ ምሬት ከምን ይመጣል? ይህን ጥያቄ ወደ እኛ በመላክ የህክምና ባለሙያ ማብራሪያ እንድናፈላልግ ምክንያት የሆኑን ከዶቼ ቬለ አድማጮች አንዱ ሥዩም በለጠ ናቸው። ጠያቂያችን የአፍ ምሬት መንስኤው ምንድነው መፍትሄውስ? በማለት ጠይቀዋል። በቅድሚያ የተከበሩ አድማጫችን በዚህ ጉዳይ የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያን በመጠየቅ መንስኤ ሊሆኑ ስለሚችሉ ተያያዥ ጉዳዮች ለሌሎችም ጠቃሚ የጤና መረጃ እንድናፈላልግ ምክንያት በመሆንዎ በአድማጮች ስም እናመሰግንዎታለን።
የአፍ ምሬት ሊያስከትሉ የሚችሉ ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን ነው የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያዎች የሚናገሩት። ከህመም ጋር የተያያዙ መንስኤዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በአፍ ንጽሕና እንዲሁም በትንባሆ ማጨስ ምክንያት የአፍ ምሬት ሊያጋጥም እንደሚችልም ያመለክታሉ።
ከ15 ዓመታት በፊት ይህንኑ ርዕሰ ጉዳይ አንስተን ያነጋገርናቸው የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም ዶክተር ቶሌራ ወልደየስ በተለይ ከህመም ጋረ በተያያዘ ሁኔታ የአፍ ምሬት እንደሚያጋጥም በመጠቆም፤ በምሳሌነትም የደም ማነስ፣ የስኳር ታማሚዎች የአፍ ምሬት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ገልጸውልን ነበር።
የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ንብረት ገዳሙ በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህርና በደብረ ታቦር ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ይሰጣሉ። ለመሆኑ የአፍ ምሬት በቋሚነት ሲከታተል የሚያጋጥመው በምን ምክንያት ይሆን ያልናቸው፤ ዶክተር ንብረት የአፍ ምሬትን የሚያመጡ በጣም ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውን ነው የገለጹልን። የውስጥ ደዌ ሀኪሙ እነዚህን ምክንያቶች ገሚሶቹ እዚያው አፍ ውስጥ በሚከሰት ምሬትን የሚያስከትሉ፤ ገሚሶቹ ደግሞ ከሌላው ሰውነታችን ክፍል ችግሮች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በማስገንዘብ በሁለት ይከፍሏቸዋል።
በተለይ አፍ ውስጥ ከሚከሰቱ መቆጣቶችም ሆነ ቁስለቶች ጋር የሚከሰቱት የአፍ ውስጥ ጽዳትና ጤንነቱን ያካትታሉ። በሁለተኛነት የዘረዘሯቸው ከሌላኛው የሰውነት ክፍል ችግሮች ጋር የተያያዙትን መንስኤዎች ከጨጓራ በምግብ ቧንቧ በኩል የአሲድ ምልሰትን ጨምሮ ከተለያዩ ህመሞች ጋር ይገናኛሉ።
ይህ ብቻም አይደለም በተለያዩ ምክንያቶች የሚወሰዱ መድኃኒቶችም ሆኑ የቫይታሚን ተጨማሪ ምግብ የሆኑ እንክብሎችም የአፍ ምሬትን ሊያስከትሉ ይችላሉ ነው የሚሉት ዶክተር ንብረት።
ሌላው አለርጂ ማለትም የምንመገበው ወይም ሰውነታችንን የነካ ነገር ከአካላችን ተቃውሞ ሲፈጥር የአፍ ምሬት ሊያጋጥም እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
አፍ ውስጥ ድንገት የሚያጋጥም ምላስን በኃይል የመንከስ አለያም ጥርስን ማፋጨት፣ በኑሮም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ለጭንቀትና መብከንከን መዳረግም የአፍ ምሬትን ሊያስከትል ከዚህ ቀደም ያነጋገርናቸው የውስጥ ደዌ ህክምና ባለሙያ ዶክተር ቶሌራ ወልደየስ ገልጸውልናል።
እናም የአፍ ምሬት ተብሎ በአጭሩ ይገለፅ እንጂ መነሻ ምክንያቱ የተለያየና ብዙ መሆኑን ነው ከህክምና ባለሙያዎች ማብራሪያ መረዳት የቻልነው። መፍትሄም በየፈርጁ ነው። ዶክተር ንብረት ከአፍ ውስጥ ጽዳት ጋር የተገናኘውን በግል በቤት ውስጥ ለማስተካከል እንደሚቻል፤ ሆኖም ግን ችግሩ የማይለወጥ ከሆነ ወደ ሀኪም መሄድ እንደሚገባ ያሳስባሉ። ከአፍ ውጭ ባለ ህመም ጋር የሚገናኙት ምክንያቶች የየዘርፉን ሀኪም እርዳታ የሚሹ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። Via – DW