መንግስት በቀጣዮቹ ዓመታት የዳታ ሉዓላዊነት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ከቲክቶክ ዊዝ ሰለሞን” ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ መንግስት በቀጣዮቹ ዓመታት የዳታ ልውውጥ እና የዳታ ሉዓላዊነት ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግና የአገልግሎት ዘርፉን እንዲያግዝ የዳታ ማከማቻ ማዕከላት ይገነባሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ የሳይንስ ሙዚየም ግንባታ፣ የኮሪደር ልማት፣ የካፒታል ገበያ እንዲሁም ስታርት አፕ ዲጂታላይዜሽን ምቹ ለማድረግ ከተሰሩ ስራዎች መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከኢኮኖሚ አንጻር ያደጉ ሀገራት ከፍተኛው የጂዲፒ ድርሻቸው የሚይዘው አገልግሎት ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው፤ ባደጉ ሀገራት ሲታይም ግብርናና ኢንዱስትሪ ያላቸው ድርሻ ከ30 በታች ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ የተሰሩ ስራዎች የአገልግሎት ዘርፉን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል፡፡
በተለይ ብሔራዊ የፋይዳ መታወቂያ የማይነካው ሴክተር ባለመኖሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ በሀገር ውስጥ ካለው ጠቀሜታ በተጨማሪ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ለመከላከል ያለው አስተዋጸኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ባለፉት ሦስት ዓመታት 15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ አግኝተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም ድረስ የዲጅታል መታወቂያ የሚወስደው የሰው ቁጥር ወደ 20 ሚሊዮን ይደርሳል የሚል ግምት እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡
በዓለም ባንክ ጥናት መሰረት የዲጂታል መታወቂያ በአንድ ሀገር ከ3 እስከ 11 በመቶ ጥቅል ገቢ ላይ አወንታዊ ተጽዕኖ እንዳለውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡
በሁለትና ሶስት ዓመት ውስጥ አብዛኛው የኢትዮጵያ ዜጋ ፋይዳ ተጠቃሚ የሚሆን ከሆነ ለሀገራዊ እቅድ፣ ለንግድ፣ ለመተማመንና አሰራርን ለማዘመን ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል መታወቂያ ልምድን ለመውሰድ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ካፒታል ገበያ የአገልግሎት ኢንዱስትሪው አካል መሆኑን ገልጸው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ በካፒታል ገበያው ዘርፍ ጀማሪ ሀገር ብትሆንም በርካታ ሰዎች ስራቸውን እየሰሩ ድርሻቸውን ሸጠው ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው በመሆኑ ለሀገር እድገት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ካፒታል ገበያን ቆየት ብለው የጀመሩ ቻይናና ህንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣታቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያ እንደሆነ መጠቆማቸውን ጋዜጣ ፕላስ ቃለ ምልልሱን ጠቅሶ አመልክቷል።