በኳታራውያን ባለሀብቶች የሚተዳደረው የፈረንሳዩ ሀያል ክለብ ፒኤስጂ በሀገር ውስጥ ያለውን ተደጋጋሚ የበላይነት በአውሮፓ ለማሳየት ከአሰልጣኞች አስከ ስመ ጥር የእግር ኳስ ኮከቦች ወደ ፓሪሱ ቤት ቢኮበልሉም የሚፈለገው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ሊመጣ አልቻለም።
ኔይማርን ከባርሴሎና፤ ኪልያን ምባፔን ከሞናኮ ያስፈረሙት ፒኤስጂዎች በተለይ በኪልያን ምባፔ ላይ ጥገኛ የሆነ ቡድን የተለያዩ አሰልጣኞች ሰርተዋል።
የኪልያን ምባፔ ልብ በተደጋጋሚ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ክለቦች ሲያማትር፤ ፒኤስጂ ምባፔን በእጅ መንሻነት በአውሮፓ ከፍተኛው ተከፋይ አድርጎት እንዲጫወትለት አግባብቶት ነበር።
በእርግጥ ምባፔ በፒኤስጂ ቤት አሰልጣኞች ሲቀያየሩ አቋሙ ሳይለዋወጥ የክለቡን ግብ የማስቆጠር ሀላፊነት በብቃት ሲወጣ ቢቆይም፤ በአውሮፓ መድረክ ከፒኤስጂ ጋር ውጤታማ መሆን አልቻለም።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሪያል ማድሪድን ሲቀላቀል በብዙ ምክንያቶች የፓሪሱ ክለብ ይጎዳል ተብሎ ነበር።
በአንድ በኩል፥ በርካታ ሚሊዮን ፓውንዶች ለምባፔ ሲከፍል የነበረው ፒኤስጂ ተጫዋቹ በነፃ ዝውውር ማድሪድን ሲቀላቀል በፋይናስ በኩል ተጎጂ ነበር።
በሌላ በኩል፥ ምባፔ ላይ ጥገኛ የነበረው ፒኤስጂ እንዴት ያለ እርሱ መጫወት ይችላል የሚለው አሳሳቢው ጉዳይ ነበር።
ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ማፈላለግ ላይ የቆዩት ስፔናዊው ታክቲሺያን ሊዊስ ኤኔሪኬ ምባፔን ተጠባባቂ በማድረግ ጨዋታዎችን ያለ ምባፔ ለመጫወት ሞክረዋል።
ይህ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ምባፔ ማድሪድን ቢቀላቀልም በወጣቶች የተገነባ ውብ እግር ኳስን የሚጫወት ቡድን ገንብተዋል።
ፒኤስጂ የፈረንሣይ ሊግ ‘ኧ’ን ገና በጊዜ ነበር ማሸነፉን ያረጋገጠው። በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ የእንግሊዞቹን ሊቨርፑል፣ አስቶንቪላ እና አርሰናልን በማሸነፍ ለሙኒኩ ፍፃሜ ደርሷል።
ኪልያን ምባፔ በሩብ ፍፃሜው ከማድሪድ ጋር በአርሰናል 5 ለ 1 ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሲሆን፤ የቀድሞ ክለቡ አርሰናልን በደርሶ መልስ 3 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ፍፃሜው አልፏል።
ፒኤስጂ ያለ ኪልያን ምባፔ የሚናፍቀውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ያሳካው ይሆን? ከኢንተር ሚላን ጋር በአልያንዝ አሬና የሚደረገው ጨዋታ ለዚህ መልስ ይኖረዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ EBC SPORT
ኢትዮሪቬውን ከታች ባሉት ማስፈንጠሪያዎች የከተሉ – የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ @ethioreview
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ ethioreview
ኤክስ ፡ twitter